2023-02-12 06:23:36
ዩኒቨርሲቲው ከ(HUMAN BIRDGE) ጋር በመተባበር ለመርዓዊ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ
*************
(የካቲት 4/2015 ዓ/ም፤ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስዊድን ሀገር ከሚገኘው ሂውማን ብሪጅ (HUMAN BIRDGE) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ የህክምና ማሽኖች፤ አልጋዎች እና ልዩልዩ መገልገያ ቁሳቁሶችን በምዕራብ ጎጃም ዞን ለሚገኘው መርዓዊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ እንደገለጹት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራዎች ባሻገር በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የምርምር ስራዎችን በእውቀት ላይ ተመስርቶ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር እሰይ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት፤ በአካባቢ ጥበቃና ግብርና ላይ እንዲሁም በትምህርትና ጤና ተቋማት ላይ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት በስዊድን ሀገር ከሚገኘው ሂውማን ብሪጅ (HUMAN BIRDGE) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ የህክምና ማሽኖች፤ አልጋዎች እና የተለያዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በምዕራብ ጎጃም ዞን ለሚገኘው መርዓዊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተለያዩ ሆስፒታሎች ድጋፍ ማድረጉን ዶ/ር እሰይ ከበደ አውስተዋል፡፡
የሂውማን ብሪጅ (HUMAN BIRDGE) ግብረ ሰናይ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አዳሙ አንለይ በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት ድርጅታቸው ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተለያዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ማለትም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አልጋዎች፤ አልትራሳውንድ፤ የዐይን ቀዶ ጥገና መስሪያ ማይክሮ ስኮፕ፤ የደም ማቆያ ፍሪጅ፤ቁጥራቸው በርከት ያሉ ዊልቸር፤ ክራንቾችና እና ሌሎችም የተለያዩ መገልገያ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍም ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት ዶ/ር አዳሙ ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ ያለው የጤና ፖሊሲ በፊት ከነበረው ለመከላከል ቅድሚያ መስጠት ባሻገር ማከምም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የመርዓዊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ዘሪሁን ሆስፒታሉ በህክምና መሳሪያ እጥረት የነበረበትን ችግር ተረድተው ድጋፍ ላደረጉላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና HUMAN BIRDGE ግብረ ሰናይ ድርጅት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር ጋሹ ክንዱ በክልሉ የጤና ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ ቢሆንም በመንግስት በጀት ብቻ ያለውን የህብረተሰብ ፍላጎት ማሟላት ስለማይቻል የግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ስለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በድጋፍ መርሀ ግብሩ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሀኑ ገድፍና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች፤ የአማራ ክልል የተለያዩ የቢሮ ሃላፊዎችና የጤና ቢሮ እና የጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በተደረገው ድጋፍም ከፍተኛ አስተዋፆ ላደረጉ አካላት የእውቅናና ምስጋና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ
Wisdom at the source of Blue Nile
https://t.me/bahir_dar_university
1.4K views03:23