2022-10-09 20:40:36
ነገ መስከረም 30/2014ዓ/ም ከሚጀመረው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስፈፃሚዎች ጋር ምክክር ተደረገ
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ት ማጠናቀቂያ ፈተና አስፈጻሚዎች ጋር በጥበብ አዳራሽ በበይነ መረም የታገዘ ገለፃ ተደረገ።
በመክፈቻውም የበይነ መረብ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሄድንባቸው ጉዞዎች ሁሉ ፈተናዎች ታልፈው ብዙ የልማት ስኬቶች እንደተመዘገቡ ጠቁመው በዚያው ልክ በትምህርት ጥራት ያልተስተካከሉ ነገሮች ቢኖሩም ፈተና አስፈፃሚዎች ይህን ትልቅ እና አገራዊ ኃላፊነት በትጋትና በታማኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የትምህርት ጥራት ከተበላሸባቸው አንዱ ምክንያት ከአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚመጡ ተማሪዎች የጥራት ማነስ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ይህን ለመቅረፍ በምንሰራቸው ስራዎች ትምህርት በስርቆት በአቋራጭ የሚገኝ ሳይሆን ደክሞ፣ ለፍቶና አጥንቶ የሚገኝ መሆኑን በተማሪዎቻችን ስነ አዕምሮ ላይ መቅረፅ አንዱ እና ትልቁ ስራ ነው ብለን፤ ይህን አድካሚ ስራ ለመስራት በጋራ የገባንበት ነው ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲው 35,822 አካባቢ ተፈታኞች እና ከ1,520 በላይ ፈተና አስፈፃሚዎችን መቀበሉን በመግለፅ ይህን ያህል ቁጥር መቀበል ጫና ቢኖረውም ለስራ በተቋቋመው ግብረ ሀይል ያልተቋረጠ ጥረት አሁን ላይ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመጨረስ የተደረገው ዝግጅቱ ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለማስተባበር የተገኙት ዶ/ር ኢዶሳ ተርፋሳ አሁን የመጣንበት ዋና ዓላማ የፈተና ላይ ስርቆትን በማስቀረት መንግስትን ለማገዝ ነው፡፡ ፈተናውን በማስፈፀም ሂደት ውስጥ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ፈተና ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎችን ከ1 ስዓት በፊት ተፈትሸው መግባታቸውን ማወቅ፣ ተፈታኞች በመፈተኛ ክፍል መታወቂያ እና ሌሎች ደጋፊ መረጃ መያዙን ማረጋገጥ፣ ወደ መፈተኛ ክፍላቸው ሲገቡ የራሳቸው መለያ ኮድ የተጻፈባቸው ቦታዎች መቀመጣቸውን ማወቅ፣ ወደ ፈተና ቦታ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ድምፅ ማሰማት እንደሌለባቸው ማሳወቅ፣ ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ክፍል ሲመጡ እርሳስ፤ላጲስና መቅረጫ ይዘው መቅረባቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በዋናነት ወደ ፈተና ክፍል ከገቡ በኋላ የሚሰጣቸውን ፎርም እንዴት መሙላት እንዳለባቸው ማገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
https://t.me/bahir_dar_university
https://t.me/bahir_dar_university
1.3K viewsedited 17:40