2023-03-03 20:42:58
ገዥ እና ተገዥ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
19፥65 እርሱ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው፡፡ እርሱን በመገዛትም ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን? رَّبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ ۚ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا
በገዢ እና በተገዢ መካከል ያለው መገዛዛት የአገልግሎት መገዛዛት" functional subordination" እና የባሕርይ መገዛዛት" ontological subordination" ተብሎ ለሁለት ይከፈላል፥ ይህንን ነጥብ በነጥብ እስቲ እንይ፦
ነጥብ አንድ
"የአገልግሎት መገዛዛት"
ለምሳሌ ባል የሚስት ራስ በመሆን ገዥ ሲሆን ሚስት ደግሞ ተገዥ ናት፦
1 ቆሮንቶስ 14፥34 ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል "እንዲገዙ" እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና።
የትኛው ሕግ? ስንል "ኦሪት" ማለት "ሕግ" ማለት ሲሆን ኦሪት ዘፍጥረት ላይ ባል የሚስት ገዥ እንደሆነ ይናገራል፦
ዘፍጥረት 3፥16 እርሱም "ገዥሽ" ይሆናል።
ባል እና ሚስት በምንነት ሰው ሲሆኑ አንድ ናቸው፥ በማንነት ግን ሁለት ስለሆኑ ሁለት ሰው ናቸው። በመካከላቸው ያለው መገዛዛት የምንነት ሳይሆን የደረጃ መገዛዛት ነው፦
ኤፌሶን 5፥22 ሚስቶች ሆይ! ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ!
ሚስት ለባሏ የምትገዛው ለክርስቶስ እንደምትገዛው ነው፥ ክርስቶስ ሰው ሲሆን ሚስት ክርስቶስ በመከተል የምትገዛው በደረጃ መገዛዛት ነው። ምክንያቱም ሚስት እና ባል ሰው ሆነው የኤክሌሲያ ክፍል ናቸው፥ ኤክሌሲያ ለክርስቶስ የምትገዛው የደረጃ መገዛት ነው፦
ኤፌሶን 5፥24 ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ።
ባል ሚስቱን ክርስቶስ ኤክሌሲያን የሚገዛው በደረጃ መገዛት ነው፥ ካልሆነ ኤክሌሲያ በሚስት ክርስቶስ በባል መመሰሉ ትርጉም የለውም። “ኤክሌሲያ” ἐκκλησία የሚለው የግሪኩ ቃል ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ቃል ነው፥ እርሱም “ኤክ” ἐκ ማለትም “ከ” ከሚል መስተዋድድ እና “ካሌኦ” καλέω ማለትም “የተጠራ” ከሚል ግስ ነው። በጥቅሉ “ተጠርተው የወጡ” ማለት ነው፥ ይህ ቋንቋዊ ፍቺው ሲሆን ሙያዊ ፍቺው ደግሞ “ጉባኤ” “ማኅበር” “ስብሰባ” ማለት ነው።
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር በሚለው መጽሐፉ ላይ ከሚያበሻቅታቸው መ*ና*ፍ*ቃ*ን አንዱ የእስክንድርያውን አርጌንስ ሲሆን አንድ ምዕራፍ ሰጥቶ በምዕራፍ 7 ላይ ይወርፈዋል፥ ሲደመድምም፦ "ልቡ ደካማ እና ኅሊናው የእንስሳ" በማለት ያብጠለጥለዋል፦
መጽሐፈ ምሥጢር 7፥17 "ልቡ ደካማ እና ኅሊናው የእንስሳ የሆነ የአርጌንስ ተግሳጽ ተፈጸመ"
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የእስክንድርያው አርጌንስን የሚያነውርበት ምክንያት "አብ የወልድ ገዥ ነው፥ ወልድ የአብ ተገዥ ነው" በማለት ዛሬ የፕሮቴስታንት ሥነ-መለኮት የሚቀበለውም የአገልግሎት መገዛዛት" functional subordination" ስላራመደ ነው።
ነጥብ ሁለት
"የባሕርይ መገዛዛት"
ለምሳሌ ሰው በእንስሳት ላይ ሁሉ ገዥ ነው፦
ዘፍጥረት 1፥28፤ እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ "ግዙአትም" የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ "ግዙአቸው"።
የሰው ኑባሬ እና የእንስሳ ኑባሬ አንድ አይደለም፥ ሰው በምንነት ሰው እንጂ ድመት፣ ውሻ፣ በግ፣ በሬ አይደለም። እንስሳን ሲገዛ የሚገዛው በባሕርይ ነው፦
መዝሙር 8፥6 በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥
መዝሙር 8፥7-8 በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።
"ሁሉን" በሚለው ቃል በጎች፣ ላሞች፣ የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች፣ የባሕርንም ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደው ያጠቃልላል፥ ይህ ጥቅስ ስለ ሰው የሚናገር ቢሆንም የዕብራውያን ጸሐፊ ከዚህ ጠቅሶ ለኢየሱስ ይጠቀምበታል፦
ዕብራውያን 2፥8 "ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት" ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም።
አሁን ግን ሁሉ ማለትም በጎች፣ ላሞች፣ የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች፣ የባሕርንም ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደው እንደ ተገዛለት ገና አናይም፥ ግን ዳግም ሲመጣ ሁሉም ከእግሩ በታች ይገዛለታል፦
ኤፌሶን 1፥22 ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት።
1 ቆሮንቶስ 15፥27 ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ "ሁሉ ተገዝቶአል" ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።
አንዱ አምላክ ለክርስቶስ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቷል ሲባለው "ሁሉ" በሚለው ቃል ውስጥ ሁሉን ያስገዛለት አንዱን አምላክ አይጨምርም፥ ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ኢየሱስ ሁሉን ላስገዛለት ለአንዱ አምላክ ይገዛል፦
1 ቆሮንቶስ 15፥28 ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።
በጎች፣ ላሞች፣ የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች፣ የባሕርንም ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደው ለኢየሱስ የሚገዛው የባሕርይ መገዛት ሲሆን ኢየሱስ ፍጡር ስለሆነ ለፈጣሪው የሚገዛው የባሕርይ ነው፦
1 ቆሮንቶስ 11፥3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።
"ክርስቶስ" ማለት "የተቀባ" ማለት ነው፥ ይህንን የተቀባ ሰው የቀባው አንዱ አምላክ ሲሆን ይህ አንዱ አምላክ ለዚህ ሰው "ራስ" ከሆነ ይህ መግዛት የባሕርይ ነው። "ራስ" ማለት "ገዥ" ማለት ነው፦
1 ዜና 29፥11 አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።
ፈጣሪ በፍጡራኑ ሁሉ ላይ ራስ ከሆነ የእርሱ ገዥነት የባሕርይ እስከሆነ ድረስ በኢየሱስ ላይ የባሕርይ ገዥ ነው፥ እንደ ጳውሎስ እሳቤ መሢሑ በስጦታ እና በጸጋ ያገኘውን የመግዛት ሥልጣን ለሰጠው ማንነት ያስረክባል፦
1 ቆሮንቶስ 15፥24 በኋላም "መንግሥቱን" ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ "በሰጠ ጊዜ" አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።
እዚህ ጥቅስ ላይ "በሰጠ ጊዜ" ጊዜ የሚለው ይሰመርበት!! መንግሥትን(መግዛትን) ሲያስረክብ ያኔ እርሱ ራሱ ገዥ ሳይሆን ተገዥ ይሆናል። ኢየሱስ እራሱ የሚገዛው ጌታ ካለው ይህ ጌታ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው። መሢሑ እራሱ የዓለማቱን ጌታ አሏህን ከመገዛት አይጠየፍም፦
19፥65 እርሱ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው፡፡ እርሱን በመገዛትም ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን? رَّبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ ۚ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا
240 views17:42