2023-05-03 19:08:43
ማነው ወፍን የፈጠረው?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው። ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን። የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ፤ ለመላው የአላህ መልዕክተኞች፤ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን።
ሀሰት ሲደጋገም እውነት ይመስላል እንዲሉ ሆነና ከሰብአዊ ፍጡርነት እና ከነቢይነት ውጪ ምንም ድርሻ የሌለውን የመርየምን ልጅ ዒሳን (የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) አምላክ እና ፈጣሪ ለማድረግ የቅጥፈት ዘመቻዎች በየአቅጣጫው እየተደጋገሙ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ወፍን ፈጥሯል” የሚለው ተረት ተረት ነው። እንኳን ወፍን ሊፈጥር ይቅርና ፍጥረተ ዓለሙ እራሱ ቢተባበረውና ቢያግዘው ዝንብ መፍጠር እንኳ አይችልም። ይህ የጌታችን ቃል ነው እንዲህ ይላል።
እናንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ። ለእርሱም አድምጡት። እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው (ጣዖታት) ዝምብን ፈጽሞ አይፈጥሩም። እርሱን (ለመፍጠር) ቢሰበስቡም እንኳ (አይችሉም)። አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከእርሱ አያስጥሉትም። ፈላጊውም ተፈላጊውም ደከሙ (ደካሞች ናቸው)።
ሱረቱል ሐጅ 22፡73
ታዲያ ከምን ተነስተው ነው ዒሳን ወፍ እንደፈጠረ ለማሳመን የሚኳትኑት ከተባለም ቀጣዩን ማስረጃ ይሆነናል ያሉትን ጥቅስ እናቅርበውና ምላሹን አብረን እንከታተል፡-
ወደ እሥራኤልም ልጆች መልዕክተኛ ያደርገዋል። (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ። እኔ ለእናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ። በእርሱም እተነፍስበታለሁ። በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕውር ሆኖ የተወለደን፤ ለምጸኛንም አድናለሁ። ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ። የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ውስጥ በእርግጥ ተዓምር አለበት።
ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡49
እስኪ መጠነኛ ማብራሪውን አብረን እንከታተል።
ሀ. “ወደ እሥራኤልም ልጆች መልዕክተኛ ያደርገዋል።”
ይህ የሚያስረዳን ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) መልዕክተኛ መሆኑንና የተላከውም ወደ ቤተ እስራኤል ብቻ እንደሆነ ነው። ከዚህ መልዕክተኝነት ውጪ ሌላ ሚና የለውም። በሌላም አንቀጽ ላይ እንደተነገረው የእሱ መልዕክተኝነት እንዳለፉት መልዕክተኞች የሆነ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልዕክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልዕክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም። እናቱም በጣም እውነተኛ ናት። (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ። አንቀጾችን ለእነርሱ (ለከሐዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት። ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት።
ሱረቱል ማኢዳህ 5፡75
ለ. “እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ።”
በማለት አላህ የዒሳ ጌታው እና አምላኩ የላከው እንደሆነ መስክሯል። ተዓምርንም ያመጣው ከእሱ ዘንድ እንጂ ከራሱ እንዳልሆነም አብሮ ገልጿል። በአምስት የቁርኣን አንቀጾች ላይ አላህ የእሱም የህዝቦቹም ጌታ እንደሆነና እሱ ብቻ መመለክ እንዳለበት አስተምሯል፡-
እነዚያ “አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው” ያሉ በእርግጥ ካዱ። አልመሲሕም አለ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ።” እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ። መኖሪያውም እሳት ናት። ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።
ሱረቱል ማኢዳህ 5፡72
ሐ. “እኔ ለእናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ።”
ቁም ነገሩ እዚህ ጋር ነው ያለው። አማርኛ ማንበብን ለቻለ ሰው አንቀጹ የሚናገረው ስለ ወፍ ቅርጽ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግተውም። ዒሳ ከጭቃ “እንደ ወፍ ቅርጽ” እፈጥራለሁ አለ እንጂ፤ መች ወፍ እፈጥራለሁ አለ? ጭቃ አምጥቶ የወፍ ቅርጽ መፍጠር ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችል ቀላል ተግባር ነው። ቁም ነገሩ በወፍ ቅርጽ በተሰራው ጭቃ ላይ ህይወትን ዘርቶ የእውነት ወፍ እንዲሆን በማድረግ እንዲበር ማስቻሉ ነው። ታዲያ ዒሳ ይህን አላደረገም ወይ? ከተባለም አንቀጹ ይቀጥልና፡-
መ. “በእርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል።”
በማለት ወፍ አድራጊው የጌታ አላህ ፈቃድና ኃይል እንጂ የዒሳ ችሎታ እንዳልነበር ያሳያል። የታለ ታዲያ ዒሳ ወፍ ፈጠረ የሚለው? የአላህ ፈቃድ ባይኖር ኖሮ ጭቃው ጭቃ እንደሆነ ይቀር ነበር እንጂ መች ወፍ ሆኖ ይበር ነበር? ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ጭቃውን አምጥቶ የወፍ ቅርጽ የሰራው እንኳ በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በጌታው አላህ ፈቃድ እንደሆነ ቅዱስ ቁርኣን በሱረቱል ማኢዳህ ቁጥር 110 ላይ ይናገራል።
ሠ. “በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፤ ለምጸኛንም፤ አድናለሁ። ሙታንንም አስነሳለሁ።”
እነዚህም ተአምራት የተከናወኑት አሁንም በአላህ ፈቃድ እንጂ በዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ችሎታ አይደለም።
ረ. “የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ።”
አንዳንድ ወገኖች ይህን ሀሳብ ይዘው ‘ዒሳ ሁሉን እንደሚያውቅ ቁርኣን መሰከረ’ ይሉናል። ሰዎቹ የሚበሉትንና በቤታቸው ያከማቹትን መናገር ሁሉን ማወቅ ሆነ በቃ? ይህ ዕውቀት በጊዜም፣ በቦታም፣ በአይነትም የተገደበ ዕውቀት እንጂ ሁሉን የማወቅ ስልጣን አይደለም። እንዴት የሚሉ ከሆነም፡-
ከጊዜ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው በእርሱ ዘመን ስለነበሩት ህዝቦቹ እንጂ ከእሱ በፊት ስላለፉት ወይም ወደፊት ስለሚመጡት ትውልዶች አይደለም። በወቅቱ የነበረውን ብቻ የሚመለከት ነው።
ከቦታ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው ነቢይ ሆኖ በተላከበት አካባቢ ለነበሩት እስራኤላውያን እንጂ በሌላ አካባቢ ስላሉት ህዝቦች አይደለም። አሁንም ዕውቀቱ ከቦታ አንጻር ግድብ ነው።
ከአይነት አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እነግራችኋለሁ በማለት እየተናገረ ያለው ስለ መብላቸው ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ስለሌላ ነገር አልተናገረም። ታዲያ በምን መልኩ ነው ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሁሉን ያውቃል ብለን ድምዳሜ የምንሰጠው?
ሰ. “የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።”
በማለት አንቀጹ ይጠናቀቃል። እኛም ምላሻችን፡- አዎ አምነናል! የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ከአላህ ዘንድ በተአምራት የተላክህ የእሱ መልዕክተኛ እንደሆንክ አምነን ተቀብለናል፤ ደግሞም መስክረናል። አምላክ ግን አልነበርክም፣ አይደለህምም፤ ወደፊትም አትሆንም።
ሸ. ወገኖች ሆይ! ኢየሱስ ተአምራትን በራሱ ኃይል ማድረግ እንደማይችል የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የት አድርጋችሁት ነው በእኛ ቅዱስ ቁርኣን ላይ የምትከራከሩን?
ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።
የማቴዎስ ወንጌል 28፡18
ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ በሰማይና በምድር ያሉ ስልጣኖችን ከማን ነው የተቀበለው? አምላክ ይሰጣል ወይንስ ይቀበላል?
እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።
ዮሀንስ ወንጌል 5፡30
436 views16:08