2023-02-21 19:53:03
አምላክን ማየት
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
"እኔን ያየ አብን አይቶአል" የሚለውን ኃይለ-ቃል ይዘው የሐዋርያት ቤተክርስቲያን በተለምዶ ኢየሱስ ብቻ"only Jesus" የሚባሉት፦ "ኢየሱስ አብ ነው" ሲሉ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንግሊካን እና ፕሮቴስታንት ደግሞ፦ "ኢየሱስ አምላክ ነው" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፥ እውን ይህ ኃይለ-ቃል "ኢየሱስ አብ ነው" ወይም "ኢየሱስ አምላክ ነው" ለሚለው ዶክትሪን ድምዳሜ ላይ ያደርሳልን? ጥቅሱን በሰከነ እና በሰላ አእምሮ እንመልከተው፦
ዮሐ14፥7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።
ዮሐ14፥8 ፊልጶስ ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው።
ዮሐ14፥9 አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል።
"እኔን ያየ አብን አይቶአል" ማለት እና "እኔ አብ ነኝ ወይም እኔ አምላክ ነኝ" ማለት አንድ የሚሆነው በምን ሒሣብ ታሥቦ ነው? ኢየሱስ፦ "እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል" ብሏል፥ እና ሐዋርያት ኢየሱስ ናቸውን? ተመሳሳይ ሰዋስው ነው፦
ማቴዎስ 10፥40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
"እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል" ማለት "ሐዋርያትን መቀበል ኢየሱስን እንደ መቀበል ነው" ማለት ከሆነ እንግዲያውስ "እኔን ያየ አብን አይቶአል" ማለት "ወልድን ማየት አብን እንደ ማየት ነው" ማለት ነው፥ "እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል" ማለት "ወልድን መቀበል አብን እንደ መቀበል ነው" ማለት ከሆነ "ወልድን ማየት አብን እንደ ማየት ነው" ማለት ነው። ተመሳሳይ ሙግት እንመልከት፦
ሉቃ10፥16 እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል።
"እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል" ማለት "ሐዋርያትን መጣል ኢየሱስን እንደ መጣል ነው" ማለት ከሆነ እንግዲያውስ "እኔን ያየ አብን አይቶአል ማለት ወልድን ማየት አብን እንደ ማየት ነው" ማለት ነው፥ "እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል" ማለት "ወልድን መጣል አብን እንደ መጣል ነው" ማለት ከሆነ "ወልድን ማየት አብን እንደማየት ነው" ማለት ነው። እንቀጥል፦
ዮሐንስ 5፥46 ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር።
"ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር" ማለት ሙሴ ኢየሱስ ነውን? ወይስ "ሙሴን ማመን ኢየሱስ እንደ ማመን ነው" ማለት ነው? እንዲሁ ኢየሱስን ማየት አብን እንደ ማየት ነው፣ ኢየሱስን ማወቅ አብን እንደ ማወቅ ነው፣ ኢየሱስን መጥላት አብን እንደ መጥላት ነው፦
ዮሐንስ 12፥45 እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።
ዮሐንስ 14፥7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።
ዮሐንስ 15፥23 እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል።
"እኔን" አንደኛ ማንነት "የላከኝ ወይም አባቴ" ሁለተኛ ማንነት፥ ስለዚህ ሁለት ማንነቶችን ቀልጭ አርጎ ያሳያል፦
ዮሐንስ 15፥24 አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል።
ያዩት እና የጠሉት ሁለት ማንነት ነው፥ "እኔን" አንድ "አባቴን" ሁለት። አብን ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል፦
ዮሐንስ 14፥7 ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል" አለው።
"ማየት" ማለት በእማሬአዊ አብን በሥጋ ዓይን መመልከት ሳይሆን በመልእክተኛው ማንነት ውስጥ በፍካሬአዊ "መገንዘብ" ማለት ነው፦
ዮሐንስ 6፥46። አብን ያየ ማንም የለም፥ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር እርሱ አብን አይቶአል።
"ከሆነ" የሚለው ቃል በቅጡ ይሰመርበት! "ከ"-እግዚአብሔር የሆነ መንፈሳዊ ሰው እርሱ አብን አይቷል፥ በሥጋ ዓይን ግን አብን ያየ ማንም የለም፦
ዮሐንስ 5፥37 የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ “መልኩንም አላያችሁም”፤
ዮሐንስ 1፥18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም።
1ኛ ዮሐንስ 4፥12 እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም።
1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥16 አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም።
ከኢየሱስ እርገት በኃላ "እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም" ሲባል ኢየሱስ "አብን አይታችሁትማል" ከሚለው ጋር ለማስማማት የሚቻለው "ወልድን ማየት አብን እንደ ማየት ነው" በሚል ቀመር ብቻ ነው። ብሉይ ኪዳን ላይ መላእክት ሲገለጡ ሰዎች "እግዚአብሔር አይተናል" ይሉ ነበር።
ናሙና አንድ፦
ዘፍጥረት 16፥7 "የእግዚአብሔር መልአክም" በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት።
ዘፍጥረት 16፥13 እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።
ናሙና ሁለት፦
ሆሴዕ 12፥4 "ከመልአኩም" ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው።
ዘፍጥረት 32፥24 ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ "ሰውም" እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር።
ዘፍጥረት 32፥30 ያዕቆብም፦ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች" ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው።
ናሙና ሦስት፦
መሣፍንት 14፥21 ያን ጊዜም ማኑሄ "የእግዚአብሔር መልአክ" መሆኑን አወቀ።
መሣፍንት 13፥22 ማኑሄም ሚስቱን፦ እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን" አላት።
መላእክት መልእክተኞች ሲሆኑ በመላእክት የአምላክ መታየት "አስተርዮተ አምላክ"theophany" ሲሆን ይህም መታየት ፍካሬአዊ እንጂ እማሬአዊ አይደለም፦
ዘጸአት 33፥20 ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡ አለ።
መላእክትን ማየት እግዚአብሔር ማየት ከሆነ መልእክተኛውን "ኢየሱስን ማየት እግዚአብሔር ማየት ነው" ብሎ መረዳት እንጂ መልእክተኛው እራሱ አብ ወይም አምላክ ነው" ብሎ መደምደም የሾቀ ድምዳሜ ነው። የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፦
5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
ኢየሱስን የላከውን አንዱን አምላክ አሏህ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አሏህን ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን! አሚን።
ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
መልካም ቆይታ ከጥሪያችን ጋር
‐‐‐
Follow us on:
‐‐‐
https://fb.me/tiriyachen
https://t.me/tiriyachen
https://tiriyachen.org
https://bit.ly/3eVixKv
https://www.tiktok.com/@tiriyachen
ወሠላሙ ዐለይኩም
232 views16:53