2023-04-03 01:23:01
መንፈስ "ፈጣሪ" ነውን?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
40፥62 ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ ከእምነት ወዴት ትመለሳላችሁ?፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ فَأَنَّىٰ تُؤْفَكُونَ
በባይብል ሁሉንም ሰው የፈጠረ አንድ አምላክ አለ፥ ይህ አንድ አምላክ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፦
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?
ኤርምያስ 51፥19 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ "ያህዌህ" ነው።
ያህዌህ አምላክ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ ይህ አንድ አምላክ ሰው ያበጀውም በእጆቹ ነው፦
ዘፍጥረት 2፥7 ያህዌህ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው።
መዝሙር 119፥73 እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም።
የያህዌህ እጆች ልክ እንደ ያህዌህ እራሳቸውን የቻሉ ማንነት ሳይሆኑ የምንነቱ መገለጫ ባሕርያት ናቸው፥ እነርሱ "ሠሩ" ስለተባሉ በስም መደብ "ሠሪዎች" እንደማይባሉ ሁሉ በተመሳሳይ ያህዌህ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ ስላለበት እና በአፉ እስትንፋስ ስለፈጠረ የአፉ እስትንፋስ "ፈጣሪ" አይደለችም፦
ዘፍጥረት 2፥7 በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት።
ኢዮብ 33፥4 የያህዌህ መንፈስ ፈጠረችኝ፥ የሁሉን ቻዩ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠችኝ። רֽוּחַ־אֵ֥ל עָשָׂ֑תְנִי וְנִשְׁמַ֖ת שַׁדַּ֣י תְּחַיֵּֽנִי׃
በሴት አንቀጽ "ዓሳቴኒይ" עָשָׂתְנִי ተብሎ የተቀመጠው የግሥ መደብ "ፈጠረችኝ" ማለት ነው፥ "የያህዌህ መንፈስ" ማለት "የሁሉን ቻዩ እስትንፋስ" ማለት ነው፥ እስትንፋሱ "ፈጠረች" ስለተባለ "ፈጣሪ" ከተባለች እጆቹ "ሠሩ" ስለተባሉ በስም መደብ "ፈጣሪዎች" ይባሉ ነበር። ቅሉ ግን እስትንፋስ ሆነ እጆቹ መፍጠሪያ እንጂ ፈጣሪዎች አይደሉም። ሌላ ናሙና እንመልከት፦
መዝሙር 8፥3 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ።
መዝሙር 102፥25 ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። וּֽמַעֲשֵׂ֖ה יָדֶ֣יךָ שָׁמָֽיִם׃
የያህዌህ ጣቶች እና እጆች ሰማያትን ስለሠሩ በስም መደብ "ፈጣሪዎች" እንደማይባሉ ሁሉ በተመሳሳይ የያህዌህ መንፈስ ስለፈጠረች "ፈጣሪ" አትባልም። ተጨማሪ ናሙና እንመልከት፦
ኢሳይያስ 48:13 እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች።
የያህዌህ እጅ ምድርን ስለመሠረት እና ቀኙ ሰማያትን ስለዘረጋች በስም መደብ "መሥራቾች" "ዘርጊዎች" ወይም "ፈጣሪዎች" እንደማይባሉ ሁሉ በተመሳሳይ የያህዌህ መንፈስ ስለፈጠረች "ፈጣሪ" አትባልም።
እንግዲህ የያህዌህ መንፈስ ልክ እንደ ያህዌህ ማንነት ካለው የያህዌህ እጆች፣ ጣቶች፣ ቀኙ ብዙ ማንነቶች ሊሆኑ ነው፥ ያ ደግሞ ሥላሴን ከሦስት በላይ ሊያደርግ ነው። ነገር ግን በግሥ መደብ የሚመጣ ድርጊት ባለቤቱ ያህዌህ ስለሆነ "ሠሪ" "ፈጣሪ" "መሥራች" "ዘርጊ" እርሱ ብቻ ነው እንጂ የእርሱን ባሕርይን እየሸነሸንን ማንነት አበጅተን ፈጣሪ አናረጋቸው። ለምሳሌ፦
ኢሳይያስ 1፥20 እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የያህዌህ አፍ ይህን ተናግሮአልና።
"የያህዌህ አፍ ይህን ተናግሮአል" የሚለው ይሰመርበት! የያህዌህ አፍ ስለተናገረ "ተናጋሪ" የሚለው የስም መደብ የምንጠቀመው ለያህዌህ እንጂ ለአፉ አይደለም፥ ሩቅ ሳንሄድ አንድ ሰው በአንደበቱ ስለሚያስተምር አስተማሪ ይባላል እንጂ አፉ "አስተማሪ" አይደለም፦
መዝሙር 37፥30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
አፍ ስላስተማረ "አስተማሪ" እንደማይባል እና አንደበት ስለተናገረ "ተናጋሪ" እንደማይባል ሁሉ እስትንፋስም ስለፈጠረች "ፈጣሪ" በፍጹም አትባልም፥ የሰው አፍ እና አንደበት እንደ ሰው ራሳቸውን የቻሉ ማንነቶች እንዳልሆኑ ሁሉ እስትንፋስም እንደ አምላክ ራሷን የቻለች ማንነት አይደለችም። የመጨረሻ ናሙና እንመልከት፦
ሉቃስ 11፥49 ስለዚህ ደግሞ የአምላክ ጥበብ እንዲህ አለች፦ ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል።
ሲራክ 24፥3 እኔ(ጥበብ) ከልዑል "አፍ ወጣሁ" ምድርንም እንደ ጉም ሽፈንኋት።
ከአምላክ አፍ የምትወጣ የአምላክ ጥበብ ስለምትልክ "ላኪ" እንደማትባል ሁሉ እስትንፋስም ስለፈጠረች "ፈጣሪ" በፍጹም አትባልም። ዕውቀት እና ማስተዋል ከአምላክ አፍ የሚወጡ ባሕርያት ናቸው፥ በማስተዋሉ ሰማያትን አጸና እንዲሁ በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፦
ምሳሌ 2፥6 "ከ-"አፉም" ዕውቀት እና ማስተዋል "ይወጣሉ"።
ምሳሌ 3፥19 ያህዌህ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
ኤርምያስ 10፥12 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።
እንግዲህ እስትንፋስ ማንነት ከሆነች እጆች፣ ጣቶች፣ ቀኝ፣ አፍ፣ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ እውቀት፣ ኃይል ስንት ማንነቶች አሉ? መፍጠሪያውን ፈጣሪ ካረግን ስንት ፈጣሪዎች አሉ? ስለዚህ እንደባይብሉ የአምላክ እስትንፋስ ልክ እንደ ዕውቀት፣ ማስተዋል፣ ጥበብ ከአፉ የምትወጣ ባሕርይ ናት፦
መዝሙር 33፥6 ሠራዊታቸውም ሁሉ "በ-"አፉ እስትንፋስ" ጸኑ። וּבְר֥וּחַ פִּ֝֗יו כָּל־צְבָאָֽם׃
እዚህ አንቀጽ ላይ "እስትንፋስ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሩሓህ" רוּחַ ሲሆን "መንፈስ" ማለት ነው፥ መንፈስ በተለያየ ጊዜ ለተለያየ ሥራ ከአፉ ወይም ከአፍንጫው የሚወጣ እስትንፋስ ከሆነ እራሱን የቻለ ማንነት እና ፈጣሪ በፍጹም አይደለም፦
ዘጸአት 15፥8 በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ። וּבְר֤וּחַ אַפֶּ֙יךָ֙ נֶ֣עֶרְמוּ מַ֔יִם
እዚህ አንቀጽ ላይ "እስትንፋስ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል በተመሳሳይ "ሩሓህ" רוּחַ ነው፥ አፍ እና አፍንጫ ሁለት የተለያዩ ከሆኑ ከሁለቱ የሚወጡትን እስትንፋሶች እየሸነሸንን አካላት የምንሰጥ እና "ፈጣሪዎች" የምንል ከሆነ ሥንት አካሎች እና ፈጣሪዎች ሊኖሩ ነው?
ወደ ቁርኣን ስንመጣ አምላካችን አሏህ አንድ ማንነት እና ምንነት ሲሆን የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፥ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፦
40፥62 ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፥ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም። ታዲያ ከእምነት ወዴት ትመለሳላችሁ?፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ فَأَنَّىٰ تُؤْفَكُونَ
ክርስቲያኖች ሆይ! እንዲህ ተወሳስቦ ከሚያወዛግብ ትምህርት ወጥታችሁ አንዱን አምላክ አሏህን እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
መልካም ቆይታ ከጥሪያችን ጋር
‐‐‐
Follow us on:
‐‐‐
https://fb.me/tiriyachen
https://t.me/tiriyachen
https://tiriyachen.org
https://bit.ly/3eVixKv
https://www.tiktok.com/@tiriyachen
ወሠላሙ ዐለይኩም
243 viewsedited 22:23