2022-11-01 13:05:44
#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አራት)
(ሜሪ ፈለቀ)
«ከዛ ሰውዬ ጋር አብሬው ተኛሁ? ምንድነው ያደረግኩት?» መልሱን ማናቸውም እንደማያውቁት እያወቅኩ ደጋግሜ እጠይቃቸዋለሁ። እነርሱም መልሱን ጠብቄ እንዳልጠየቅኳቸው ስለልገባቸው አይመልሱልኝም። ከዚህ ቀዬ ከወጣሁ በኋላ የተፈጠረውን ነገር ካወቀ ሊያውቅ የሚችለው ኪዳን ብቻ ነው።
እናቴን ካገኘሁ በኋላ ያለፈውን ራሴን የመፈለግ ውጥረቴ ትቶኝ ነበር። አጎቴ ታሪኬን ነግሮኝ ሲያበቃ እንደአዲስ ያቅበጠብጠኝ ጀመር። ምንድነው ያደረግኩት? ምን ዓይነት አቅል መሳት ላይ ደርሼ ነው ያን ሰውዬ ያገባሁት?
«እናቴ? ስለኪዳን የነገርኩሽን የምታስታውሺውን ሁሉ እስኪ ንገሪኝ! ከተመታሁኮ ሁለት ወር አለፈ። እንዴት አይፈልገኝም? እንዴት አይደውልልኝም?»
«እኔ እንጃ ልጄ! ብዙውን ያወራሽኝ ስለመውደድሽ ፤ ጎበዝ ተማሪ ሆኖ በማዕረግ ስለመመረቁ ፣ ፈረንጅ ፍቅረኛ እንዳለችው እና ሰርጉ ሀገሩ እንዲሆን ፈልጎ አንቺ እንቢ ማለትሽን …… እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር ነው የነገርሽኝ እንጂ የምትገናኙበትን መንገድ አላውቅም ልጄ። ከመሞቴ በፊት ባየው ብዬሽ <በህይወት መኖርሽን አያውቅም። እንዴት እንደምነግረው እንጃ ግን እነግረዋለሁ> አልሽኝ።» እያለችኝ ሌላ የምታስታውሰው ነገር መኖሩን የጭንቅላቷን ጓዳ ትበረብራለች
«ለምን እንቢ አልኩት? ማለቴ ሰርጉን?»
«አንቺን ማጥቃት የፈለገ ሰው ሊያጠቃሽ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ እሱ በመሆኑ አንድ ነገር እንደሚያደርጉብሽ ነው የነገርሽኝ። ሁኔታውን ልትነግሪኝ አልወደድሽም እንጂ ከዚህ በፊት በእሱ እንዳገኙሽ ነግረሽኛል።»
ድፍንፍን ያለ ነገር ሆነብኝ። ወደቤቴ መመለስ ፈለግኩ። ፍለጋዬን የት እንደምጀምር ባላውቅም እዛ የሆነ ፍንጭ አላጣም መሰለኝ። ያቺ መልእክት አስቀምጣ የነበረችው እመቤትስ? ያ የደወልንለት ሰውዬ ቃሊቲ እስር ቤት ናት ያላት እመቤት! ማን ያውቃል ለእሷ የሆነ ነገር ነግሬያት ይሆናል። ግን እስር ቤቱጋ ሄጄ በደፈናው እመቤትን ነው የምለው? ምናልባት አንድ ሀገር እመቤት የሚባል ሴት ይኖራል። አላውቅም ብቻ እዚህ ተቀምጬ ሀሳብ ከማመነዥክ መሞከሩ አይከፋም!
ምናልባት ደግሞ ያ ስልባቦት የመሰለ ዳዊት የሚሉት ፍቅረኛዬ! ለእርሱስ ምንም ልነግረው አልችልም ኸረ! ማን ያውቃል ግን? ግን እንዴት ባለ ዘዴ ነው ትውስታዬን ማጣቴን ሳልነግረው ስለኪዳን የሚያውቀው ነገር መኖሩን የማወጣጣው?
እናቴ የቀሯትን ቀናት እዛው መሆን መፈለጓን እኔ እንዳይከፋኝ በማባበል በማስፈቀድ ለዛ ስትጠይቀኝ ግራ ገባኝ። በሽታዋ የማህፀን ካንሰር ነው። ምንም ማድረግ እስከማይችሉበት ሰዓት ድረስ ሀኪሞች ብዙ ትሪትመንት ሞክረውላታል። ያገኘኋት ጊዜ ሀኪም ቤት ካልወሰድኩሽ ብዬ ስነዘንዛት
«ልጄ አንቺው እኮ ነሽ ስታሳክሚኝ የቆየሽው! ከሀገር ውጪ ወጥተሽ ካልታከምሽ ብለሽኝኮ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ሀኪሞቹ ነግረውሽ ነው የተውሽው። አምላክ በታምሩ ይሄን ደስታ ቀምሰሽ ሙቺ ሲለኝ እንጂ እንዲህም መች ትቆያለች ተባልኩ?» ብላኝ ነበር። ሀኪሞቹ ከገመቱት ቀን በላይ መቆየቷ ተዓምር እንደሆነ ሁሉ ብትታከም ድጋሚ ተዓምር ሊፈጠር ይችል ይሆናል ብዬ ላሳምናት ብሞክርም <ደከመኝ> አለችኝ። ማረፍ ብቻ ነው የፈለገችው። መሞትን ሳትፈራው ቀርታ ይሁን ወይስ እንዳይታወቅባት ውጣው ለመሞት የተዘጋጀች ነው የምትመስለው። በመጣ ቀን <እንኳን ደህና መጣህ! ስጠብቅህ ነበር> ብላ የምትቀበለው።
«እሺ!» አልኳት እና ወደጎንጥ ዞሬ «አንተ ነገውኑ ባሻህ ሰዓት ተመለስ! እኔ እዚህ ከእናቴ ጋር እሆናለሁ! » አልኩት
«ማይደረገውን!! እኔ እዚህ መሆኔ ካልከበዳችሁ በቀር ወደየትም የመሄድ መሻት የለኝም!!» (አለ ወደአጎቴ እያየ)
«ኸረ ምን ከብደኸኝ? ባደረገውና እዚሁ በባጀህ! እኔማ የሚያነጋግረኝ አገኘሁ!» አለ አጎቴ።
ከመጣን ጀምሮ ጎንጥ ከዚህ በፊት የሚያውቀው ቤት እና ቤተሰብ ውስጥ የተቀላቀለ ነበር የሚመስለው። እጅጌውን ሰብሰብ አድርጎ እንጨት ለመፍለጥ ሰዓታት አልፈጀም። ሊወድቅ ያዘመመውን የከብቶቹን ቤት ያጋደለውን እንጨት እያስተካከለ ሲተክል በእንግድነት ውሎ አላደረም ነበር። ሱሪውን ሰብስቦ እንደቁምጣ አሳጥሮ የአጎቴን የጓሮ ማሳ ሲያርም …… የኖረበት …. የሚያውቀው እንደሆነ ያሳብቅበት ነበር። አጎቴ በእርሱ መገኘት ደስ መሰኘቱን ለማወቅ ብዙ ሂሳብ አያሰራም።
«እኔ እዚህ ምን እሆናለሁ? እዚህ ጠላት የለኝም ሲገባኝ። ዝምብዬ ነው የምፈራው እንጂ ምናልባትም ማንም እያደባብኝ አይደለም። የሚያስፈልግ ነገር ሲኖር ባይሆን ትመጣለህ።» አልኩት እናቴን ላገኛት የሄድኩ ቀን እንደዛ ተንበጭብጬ ምንም ያለመፈጠሩን እያሰብኩ።
«ህም!! ክፋት የከጀለ ልብ አይደለም እዝህች ሲኦል ከመውረድ የሚያግደው የለም!» አባባሉ ስለእርሱ ያለኝን ጥርጣሬ ቀሰቀሰብኝ። የሆነ ያልነገረኝ የሚያውቀው ነገርማ አለ።
«አይሆንም አንቺም እዚህ አትከርሚም!» አለች እናቴ ጠልቃ ገብታ « ….. በአካል ባልዳብሰው እንኳን የኪዳንን ድምፅ ሰምቼ አንዴ አውርቼው ባልፍ …… ይሄ ባይሆን እንኳን ለወንድምሽ ታስፈልጊዋለሽ። አግኝው!» አለችኝ አሁንም በልምምጧ። ልቤ መሃል ላይ ዋለለብኝ። እሺ የት ብዬ ነው የምፈልገው? እሱን ለማግኘት እኔ ስዳክር እናቴ ብታመልጠኝስ? ምን ያህል እንደሆነ የማላውቀውን የቀረንን ቀን ትቻት እንዴት ነው የምሄደው?
«የእኔ አበባ ? አትከፊብኝ! እዚህ አብረሽኝ ብትሆኝም ሞትን አታስመልጪኝም! ለእኔ አምላክ በእድሜዬ ማታ አንቺን መልሶልኝ ሀሴት ሰጥቶኛል። ወንድምሽን ባላገኘው እንኳን ደህና መሆኑን ማወቄ እረፍት ነው!! ስንት ቀኖች እና ስንት ለሊቶች <ልጆቼን ለየትኛው ጅብ ዳርጌያቸው ይሆን? ምን ዓይነት ህይወት እየኖሩ ይሆን? ትቻቸው ባልሄድ የተሻለ ህይወት ይሆንላቸው ነበር?> እያልኩ በፀፀት ነድጃለሁ መሰለሽ? ያንቺ እናት ስለሆንኩ እኔ እድለኛ ነኝ። ብቻ አንድ ነገር ቃል ጊቢልኝ! ያለፍሽውን ብታስታውሺም ባታስታውሺም ወደቀደመው ህይወትሽ ላትመለሺ ቃል ጊቢልኝ!! ልብሽን ያየ አምላክ ሁለተኛ እድል ሰጥቶሻል። ያለፈውን ለመድገም ሌላ አዲስ ህይወት ባላስፈለገሽ ነበር። አዲስ ህይወትን ገንቢ የእኔ አበባ! ……. » የስንብት የሚመስል ብዙ አለችኝ። ያለእርሷ የኖርኩትን ህይወት እንዴት እንደኖርኩት ባላውቅም አሁን ያለእርሱ የምኖራቸውን ቀናት ሳስብ በረደኝ።
ግማሽ ልቤን እናቴጋ ትቼ፤ ፈጣሪ ትንሽ ቀን ቢጨምርላት፣ ኪዳንን ባገኝላት እና ብትሰማው ወይ ብታየው እየለመንኩ በተከፋች ግማሽ ልቤ ከጎንጥ ጋር ወደቤት መንገዱን ተያያዝነው።
«ይገርማል! የዛን ቀን ሞቼ ቢሆን ኖሮምኮ መሞቴን እናቴም አጎቴም አይሰሙም። በዚህ አይነት ኪዳንም አይሰማም ነበር። ሊቀብረኝ ራሱ የሚመጣ ሰው ይኖር ይሆን?» አልኩኝ
« ህም የሌላውን እንጃ። እኔ የት ሄጄ ነው የማልኖር?»
«ሬሳዬን የሚሸኝ ስለማይኖር ሰብአዊነት ተሰምቶህ እንጂ መቼም <ወየው እትይ!> እያልክ አትቀብረኝም ነበር።» ስለው አይኑን ለአፍታ ከመንገዱ ወደእኔ አዙሮ ፈገግ ብሎ ዝም አለ። በሱው የፈገግታ ለዛ ቀጥዬ «ሆስፒታል እንኳን መጥተህ እየኝ ብዬ ብልክብህ <የቀጠሩኝ ደጆን እንድጠብቅ ነው > ብለህ አልላክብኝም? ዛሬ ቤቱን ጥለህ ገጠር ለገጠር አብረኸኝ ልትንከራተት?»
946 viewsDAVE / PAPI, edited 10:05