Get Mystery Box with random crypto!

«ህም መች ሰው ባሰበበት ይውላል?» አለ ከንፈሩን ብቻ ሸሸት አድርጎ። እኔ አንድ ሀገር አውርቼ ከ | ወግ ብቻ

«ህም መች ሰው ባሰበበት ይውላል?» አለ ከንፈሩን ብቻ ሸሸት አድርጎ። እኔ አንድ ሀገር አውርቼ ከአምስት ቃል ያልዘለለ ነው የሚመልስልኝ። ያለማቋረጥ መለፍለፌ ለራሴ እንኳን እንግዳ አይነት ስሜት ሰጥቶኛል። መልሼ ይሄንንም ያንንም ሳወራ ራሴን አገኘዋለሁ እንጂ። ምናልባት ከእናቴ ጋር የነበረኝ ጊዜ፣ ወይ ደግሞ ያስታወስኩት የትውስታዬ ሽራፊ፣ ወይም ትውስታዬ የመመለስ ተስፋ እንዳለው ማወቄ፣ አልያም አጎቴ ያወራልኝ የህይወቴ ክፍል …… አላውቅም! አንዳቸው ወይም ሁሉም ተደምረው ግን የሆነ ስሄድ ከነበረው ቅልል ያለ ስሜት ስመለስ እንዲኖረኝ አድርገውኛል።

«ከመመታቴ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያደረግኩት ምን ይሆን? ለመጨረሻ ያገኘሁት ሰው ማን ይሆን? ያስቀየምኩት ወይስ በጥሩ የሚያስታውሰኝ ሰው ይሆን?» ያልኩት እንዲመልስልኝ አልነበረም።

«የዚያን እለት ከቤት ወጥተሽ ብዙም ሳትቆዪ ነው የሆነው ነገር የሆነው። በመንገድሽ የገጠመሽ ካልነበረ ለመጨረሻ ያወራሽው እኔን ነው የሚሆን!» አለ ስሜቱን ለማንበብ በሚከብድ ፊት። ያልጠበቅኩት መልስ ሆኖ መሰለኝ ተስተካክዬ ተቀመጥኩ።

«ምንድነው ያወራሁህ? መጥፎ ነገር ነው? ጥሩ?»
«ያለፈውን ከኋላችን እንተወው ተባብለንም የለ?» መመለስ የማይፈልገው ነገር ሲሆን የሚያመልጥበት ዘዴው ነው።
«በናትህ? ለምንድነው ግን ያለፈውን ስጠይቅህ የምትሸሸው? ልቤ የሚነግረኝ ከነገርከኝ በላይ ብዙ የምታውቀውን ነገር እንደደበቅከኝ ነው ግን ዝም ብዬ እያመንኩህ ነው።» ….. ብዬ ጥርጣሬዬን ላስከትል ስንደረደር የሚቀጥለውን ለማስቆም በሚመስል

«ፀያፍ ነገር ነው!! እኔ አሁን የማልደግመውን ፀያፍ ነገር ብለሽኝ ነው የወጣሽ! እንደእውነቱስ አፍሽን ከፈትሽ ነው የሚባል።» አለ እንዲመልስልኝ ስላደረግኩት እየተናደደብኝ።

«እሺ በሙሉ ልቤ እንዳምንህ አስረዳኝ! እንደዛ ፀያፍ ነገር የምናገርህ ሴት ሆኜ እቤቴ ምን አቆየህ? ስራዬ ፣ እንጀራዬ ምናምን ብለህ ልትሸነግለኝ አትሞክር! እኔ የምከፍልህን ደመወዝ ብዙ እጥፍ ከፍሎ የሚያሰራህ ሰው አታጣም ባንተ ብዙ ችሎታ! ሲጀመር የአንድ ቤት ዘበኛ፣ መኪና መንዳት የሚችል፣ ሽጉጥ የታጠቀ ፣ ክብር ሀቅ እውነት እሴቶቹ የሆነ ሰው ……  አፏን የምትከፍትበት ሴት ደጅ ምን ያደርጋል?»

«ውል የሌለው አድርገሽ አትቆጣጥሪውማ! ሹፍርና እሰራ እንደነበርኮ አውግቼሽ ነበር። ወታደር ቤት ስለነበርኩ መሳሪያውም አዲሴ አይደለም። ሽጉጡንም ያስታጠቅሽኝ አንቺው ነበርሽ! ይከው ነው!!» አለ

«አሁን ያልከው በሙሉ ለምን እኔጋ እንደቆየህ አያብራራም! እሺ ንገረኝ እስኪ የት ነው የተገናኘነው? ማለቴ ስራውን እንዴት አገኘኸው? ወይም እኔ እንዴት ቀጠርኩህ?»

ለማውራት አፉን ከመክፈቱ በፊት በረጅሙ ተነፈሰ። ግንባሩ ላይ ያሉት መስመሮች ብዛታቸው ጨመረ። ዞር ብሎ ሳያየኝ

«ሰው ነው ያገናኘን! አንቺ ጠባቂ እንደምትፈልጊ እኔ ስራ እንደሚያስፈልገኝ የሚያቅ ሰው!» አለ በድፍኑ። አጀማመሩ እስከነገ የማያልቅ ታሪክ ሊያወራኝ ነበርኮ የሚመስለው።

«በቃ!? ሰው?» ድምፄን ጨመርኩ።
«ቆይ እኔ የምጎዳሽ አለመሆኔን እንድታምኚ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ?»
«እያወራን ካለነው ጋር ይሄ የሚያገናኘው ነገር የለም! ትጎዳኛለህ ብዬ ባስብማ አብሬህ አልገኝም!! አንተ መናገር ያልፈለግከው ወይም እየደበቅከኝ ያለ ነገር እንዳለ እየተሰማኝ ግን ምንም ሳትጠይቂ በጭፍኑ እመኚኝ ማለት አይዋጥልኝም።» አልመለሰልኝም። አሁንም በረዥሙ ተንፍሶ ዝም አለ። በዝምታችን ውስጥ ከራሴ ሳወራ ለካንስ ምንም ነገር ለእኔ የማስረዳት ግዴታም የለበትም። <የራስሽ ጉዳይ> ብሎ ጥሎኝ ቢሄድስ መብቱ አይደል? ያኔም ለምን አብሮኝ እንደቆየ አሁን ለምን አብሮኝ እንዳለ ምክንያቱን ማወቅ አልችልም። ስለእርሱ የማወቅ መብት እንዳለኝ እንዲሰማኝ ያደረገኝ ራሱ አይደል ግን?

ሀሳብ ሳዛቁል ስልኬ ጠራ። የማላውቀው ቁጥር ነው። ለምን እንደማደርገው ባላውቅም የማላውቀው ስልክ ሲደወል ጎንጥ አጠገቤ ካለ ድምፁን ስፒከር ላይ አደርገዋለሁ። ምናልባት የመጀመሪያ ቀን ስልኬ ሲከፈት ድንብርብሬ ወጥቶ ስንተባተብ እሱ ስልኩን ተቀብሎኝ ስላወራ እንደልምድ ወስጄው ይሆናል። አነስቼ ሀሎ አልኩ።

«እሺ ሜላት!! ሁልጊዜ ጀግና አይኮንም! አንድ ቀን አገኝሻለሁ ብዬሽ አልነበር?» ወፍራም ድርብ የወንድ ድምፅ ነው።
«ማን ልበል?»
«ማን እንደሆንኩማ አሳምረሽ ታውቂዋለሽ!! ዛሬውኑ እስከማታ ድረስ የምልሽን ታደርጊያለሽ!! ህም እመኚኝ ይሄ እንደሌላ ጊዜው ማስፈራሪያ አይደለም። ምንም አይነት ወጥመድ ከጀርባዬ ሸርባለሁ ብትዪ ወንድምሽን 12 ትንንሽ አድርጌ በየተራ እልክልሻለሁ። ……. » ጎንጥ መኪናዋን ሲጢጥ አድርጎ አቆማት። እየሆነ ያለው ነገር በቅጡ ሳይገባኝ ሰውየው ማውራቱን ቀጠለ « …… ልታናግሪው ከፈለግሽ አጠገቤ ነው። ቪዲዮ ላድርግልሽ ከፈለግሽ?» (እያላገጠብኝ ነው የሚያወራው) ይሄኔ ጎንጥ ከመኪናው ፊትለፊት ያለ ወረቀት አንስቶ ከኪሱ እስኪሪብቶ አውጥቶ የፃፈውን አሳየኝ። <ምንድነው የምትፈልገው? በይው።> ሰውየው ይሄን ሲሰማ እንደመደሰት አደረገው።

« የሰውን ስስ ጎን ማግኘት ደስ ሲል።አየሽ  የምትሳሺለት ነገር ሲያዝብሽ እንዲህ ነው የሚያንገበግበው። ከገባሽ! አንደኛ ወለም ዘለም ሳትዪ የቪዲዮን ያሉሽን ቅጂዎች በሙሉ ካስቀመጥሽበት ሰብስበሽ ነይ የምልሽ ቦታ ይዘሽ ትመጫለሽ። ሁለተኛ አንቺን ማመን ስለማይቻል ማስተማመኛ እንዲሆነኝ እዚህ ከመጣሽ በኋላ በይ የምልሽን እያልሽ እንቀርፅሻለን። ይቅርታ እንግዲህ ባላምንሽ … ያለመታመን ልምድሽ አቻ ባይኖረው ነው።» እኔ እሱ የተናገረው ምኑም አልገባኝ እሱ ይገለፍጣል። ጎንጥ ፅፎ ያሳየኛል።

«እኮ ምንድነው እንድቀርፅልህ የምትፈልገው?»
«ቆቅ አልነበርሽ? ይህቺ ትጠፋሻለች? በማስፈራራት ያለፍሻቸውን እዚህም እዛም የሰራሻቸው ህገወጥ ነገሮች ሲሰበሰቡ እድሜ ልክ ዘብጥያ የምትበሰብሺበት ሆኖ አጊንቼዋለሁ። ብዙም እንዳትቸገሪ መረጃዎቹንም ሰብስቤልሻለሁ። አንቺ የሚጠበቅብሽ የሰራሻቸውን ወንጀሎች በመረጃ አስደግፈሽ አምነሽ ቃል መስጠት ነው። ከምታምኛቸው ውስጥ ፌክ የምስል ቅንብር እና መረጃ ሰርተሽ እኔን በማስፈራራት የግል ጥቅም ለማግኘት ያለመታከት መልፋትሽ ይካተትበታል። ያው እዝህችጋ ምንም ያህል የረቀ ሴራ ብትሰሪ እኔ ወደር የሌለኝ ለሀገሬ ታማኝ አገልጋይ መሆኔን አክለሽ ብትጠቅሽም አይከፋኝም። ሃሃሃሃሃ» እኔ ምኑም እየገባኝ ካለመሆኔ እየተነጋገሩ ያሉት ሰውየውና ጎንጥ ናቸው የሚመስሉት

«ኪዳንን አገናኘኝ? ማስረጃ እፈልጋለሁ።» ብሎ ጎንጥ የፃፈልኝን አነበብኩለት

«ምን ችግር። ቆዪማ ቪዲዮ ላድርገው?» ሲለኝ ጎንጥ ስልኩን ዘጋው እና እኔ ላይ አፈጠጠ።

«ወንድምሽን ስታዪው የተደናገጠ ሰው እንዳትመስዪ ፣ ድሮ የሚያውቋትን ሜላት መሆንሽን አሳምኛቸው። ምንም እንደማያውቅ ሰው አትምሰዪ ….. የማታውቂውን ነገር አትጠይቂ!! ምንም ቢፈጠር እንደማታስታውሺ እንዳትናገሪ ….. የምልሽን ብቻ አድርጊ!!» ብሎ በቁጣ እያስጠነቀቀኝ ስልኬን ተቀብሎኝ የሆነ ነገር እንደሚፈልግ ሰው ጣቱን ካመላለሰ በኋላ ከመጡለት ዝርዝሮች የሆነች ቀይ ምልክት ነገር ተጭኖ እየመለሰልኝ ስልኩ ጠራ። ድንብርብሬ ሲወጣ በሁለቱም እጆቹ ትከሻዬን በሁለቱም በኩል አጥብቆ እየያዘ « ታምኚኛለሽ?» ያለኝ ስለምን እንደሆነ ሳይገባንኝ ጭንቅላቴን ወደ ላይ ወደታች ናጥኩ!! «ተረጋጊና ያልኩሽን አድርጊ!!»