2022-10-24 21:29:22
#የመኖር አጋማሽ ..የመ: ሞ : ት ሲሶ ... መንገድ መሃል ..... (ክፍል ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)
'ማናችሁ? ምን ፈለጋችሁ?' ከማለቴ በፊት ከታክሲው ኃላ መቀመጫ ጎትተው አስወጥተው ያበጥሩኝ ጀመር:: .... 'ምን አድርጌያችሁ ነው?' ማለት አፌ ይፈልጋል... በየትኛው ትንፋሽ?... እንኳን የማወራበት... የምተነፍስበት ፋታ ሳይሰጡ ተቀባበሉኝ.... ባለታክሲው ሁለት ቡጢውን ሲያጣጥም መፍጨርጨሩንም ተወው:: ... ሶስተኛ ሲሰልሱት እንዲተውኝ መለመኑንም ተወው! መሬቱ ላይ ወድቄ 'እንካ በእርግጫ' ተባባሉብኝ.... የምቱ ቁጥር ሲጨምር የህመሙ መጠን ቀነሰ... ሰውነቴ የደነዘዘ መሰለኝ.... አንደኛው በጫማው ደሬቴን ሲለኝ... ቁስሌ የተቀደደ አይነት ስሜት ተሰማኝ... ሳያስፈቅደኝ ልቤ ክድት ... ጭልጥ ይልብኝ እና ምቱ ያነቃኛል.... በስልምልምታ ከሩቅ እየቀረበ የመጣ የመኪና ድምፅ እና መብራት የተፈራረቁብኝ ይመስለኛል::..... የሚደልቁኝ ጫማዎች በፍጥነት ጥለውኝ ሲሄዱ ነገር.... ... ልቤ ቅልጥ ብሎ ጥፍት አለብኝ....
የሆነ በርቀት ነገር "እትይ! እትይ!" ... የሚል ጥሪ ይሰማኛል:: ... አይኖቼን ልገልጥ ስሞክር የአይኖቼ ቆቦች ህመማቸው ያሰቃየኛል:: ... ያልታመመ የሰውነት አካል የለኝም:: ... ሀኪም ቤት ተኝቻለሁ::.... ጎንጥ የአልጋዬን ጠርዝ ይዞራል:: ያልተጠቀለለ የሰውነት አካል የለኝም::.... አይኔን መግለጤን ሲያይ
"እትይ ነቁ? ክብር ምስጋና ይግባህ አምላከ ስላሴ!" ብሎ ወደ ሰማይ አየ.... ፊቴ ላይ ሳይቀር በፋሻ ተጠቅልያለሁ!.... እንባዬ ሲወርድ ወደ ጆሮዬ እየሄደ የሚያልፍበት ቆዳ ሁሉ አልኮል እንደተደፋበት ቁስል ያቃጥለኛል::... አንገቴ ቀስሮ በሚይዝ መደገፊያ ተደግፎ ስለታሰረ አይኔን እንጂ አንገቴን ማዞር አልችልም:: አፌን ላንቀሳቅስ ብሞክር የተሰነጠቀ ከንፈሬ ስቃይ ውስጥ ይጥደኛል::...
"እትይ! ግድ የለም እነዚህን ሽንታሞች አገኛቸዋለሁ!!" ይለኛል ጎንጥ እሳት በሚተፋ የንዴት እና የእልህ ትንፋሽ .... በቁጭት አንዱን እጁን በቡጢ ጨብጦ ሌላኛውን ይመታል::
በጥይት ተመትቼ ስነቃ እንዲህ በህመም አልተሰቃየሁም ነበር::.... ተኛኜ እና ጎንጥ እየተፈራረቁ እያስታመሙኝ ሆስፒታል ከረምኩ::.... ከሳምንታት በኃላ የተሰበረ አፍንጫዬ አገገመ.... የተሰነጠቀ ከንፈሬ ቁስል ሻረ... የተሰባበሩት የጎድን አጥንቶቼ ተደጋገፋ... የበለዙ ስጋዎቼ ፈዘዙ..... አንገቴ ያለ ድጋፍ ዞረ.... የዞረ ክንዴ ቦታው ሰገበ... ወደ አንጀቴ የፈሰሰ ደሜ ተቀዳ..... የተቀደደ ቁስሌ ተሰፋ......
"ተሻለሽ?" ሲሉኝ .... "ደህና ነኝ!" እላለሁ! ... የጠየቁኝ የስጋ ቁስሌን እንደሆነ ስለማውቅ...
እኔ ግን አልተሻለኝም!! ደህና አይደለሁም!! ጭራሽ ለደህና የቀረበ ነገር አይደለሁም!! ... ጎንጥ አጠገቤ ሆኖ እጄን ካልያዘኝ እንቅልፍ የማይወስደኝ ፈሪ ሆኛለሁ:: ኮሽ ባለ ቁጥር ከአልጋዬ የማልዘለው እሱ እየጠበቀኝ እንደሆነ ሳውቅ ብቻ ነው:: .... ካለበለዚያ ኮቴ ያስደነግጠኛል:: .... የትንኝ ጥዝታታታ እንኳን ጩሂ ጩሂ ይለኛል:: መጠየቅም መመለስም ተውኩ:: መሞትም መኖርም ፈራሁ!! ... ተናኜ አብራኝ ስትውል.... የቆጥ የባጡን ስትለፈክፍ አልመልስ ስላት!!
"ኸረ እትይ በማርያም እንዲህ አይሁኑ!" ትለኛለች:: ጭንቅ ጥብብ ሲላት ደግሞ
"እትይ? ካልሆነ እብስ ብለው ለምን የሆነ ሀገር አይሄዱም?" ትለኛለች::
"እትይ? እስኪ ትንሽ ነገር ደግሞ ይቅመሱ በማርያም?"
..... አግጯን ደገፍ ታደርግና "ምፅ!" ብላ እንባዋን ትለቀዋለች:: ...
"ምን ልሁን ነው የምትይ?" ይላታል ጎንጥ ማልቀሷን ሲያውቅ:: ....
የዛን ቀን ሹፌሩ የመኪና ታርጋቸውን መዝግቦ ስለነበር ለፖሊስ መረጃ ብንሰጥም ፖሊሶቹ የእኔ ጉዳይ ግድ የሚሰጣቸው አልመሰሉም:: ጎንጥ ብስጭት ብሎ
"በነጋ በጠባ 'ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው! ' ይሉኛል:: ጠብ የሚል ነገር የለም! እንዴት ያለ ህግ ነው?" አለኝ የሆነ ቀን.... አልመለስኩለትም!! .... ቀን ቀን ተናኜ ትውልልኛለች:: ማታ ማታ እሱ ያድራል:: ... ዳዊት አንድ ሁለቴ ሊጠይቀኝ መጥቶ ነበር:: እንዳይመጣ ስለነገርኩት ቀረ!! ....
"እትይ ? ዛሬ ጎንጥ ስለማይመጣ ምሽቱንም እኔ ነኝ የማስተዳድሮት.... እቤት ደረስ ብዬ እራት አበሳስዬ ላምጣ?" አለች በጨነቀው ልምምጥ....
"ለምንድነው ጎንጥ የማይመጣው? " አልኩኝ የወላለቀ ሰውነቴን እየጎተትኩ ተቀምጬ
"አላውቅም እትይ!! የምፈጣጥመው ነገር አለኝ ! ነው ያለው!"
"እሺ ትተሽኝ አትሂጂ.... ከካፍቴሪያ የሆነ ነገር ግዢ" ብያት (የሆስፒታሉ ጊቢ ውስጥ ያለ ካፍቴሪያ ነው) እሷ ልታመጣ ስትሄድ ከፋኝ!! እንደህፃን ልጅ አለቀስኩ:: .... ሆስፒታል ማደር ደክሞት ይሆን??? እኔን መጠበቅ ከነአካቴው ደክሞት ይሆን?? ጠልቶኝ ይሆን?? .... ላይመለስ ትቶኝ ቢሄድ ምንድነው የምሆነው?? ከእርሱና ከተናኜ ውጪ ማንንም እንደማላውቅ እያወቀ ትቶኝ ይሄድ ይሆን?? ይቅር ይበለኝ እና ብር አምጣ ብዬ ከካዝናው ውስጥ ያወጣሁት ብር የት እንዳለ ነግሬዋለሁኮ .... ብሩን ይዞ እኔን ትቶኝ ሄዶ ቢሆንስ? እኔ በወር የምከፍለውን ደመወዝ ከ20 ዓመት በላይ የሚከፍለው ብር ነው..... በስመአብ !! ኸረ እንደሱ አያደርግም!!!
ለሊቱ እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር ነጋ!! ተናኜ ሳለቅስ ካየችኝ ከእኔ ብሳ ታርፈዋለች:: አልጋዬ ስር ፍራሿን ዘርግታ እንቅልፍ እስኪወስዳት ጠብቄ ..... ብዙ አልቅሼ እንባዬ ሁላ ያለቀ መሰለኝ!! ፍርሃት ሆዴን አላወሰው!!! የበር ድምፅ በሰማሁ ቁጥር ልቤ ይርዳል:: ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል::.... ነግቶ ብርሃን ሲሆን እንቅልፍ ጣለኝ:: .... ብርሃን ከክፋት የሚጠብቀኝ ይመስል ሲፈካ ልቤ ይረጋጋል:: ከእንቅልፌ ስነቃ አይኔን ሳልገልጥ በፊት እጄን የያዘኝን እጅ ጨበጥኩ.... አይኖቼን ስገልጣቸው ጎንጥ ለሊት ሲያድር እንደሚያደርገው ወንበር ላይ ተቀምጦ እጄን ይዞኝ ... አንገቱን አልጋው ላይ ደፍቶ ተኝቷል:: .... ደስታ ይሁን መከፋት የማላውቀው ስሜት ናጠኝ::: ህቅታዬ እንዳይረብሸው እየታገልኩ ተንሰቀሰቅኩ:: ... ከደቂቃዎች በኃላ ግን ልያዘውም ብል ፈንቅሎኝ የወጣ ህቅታዬ ቀሰቀሰው.... እንደነቃ ሳየው ይብስ ድምፅ አውጥቼ ማልቀስ ጀመርኩ:: ....
"መድሃንያለም! እትይ? ምን ሆነው ነው?? ኸረ በመድሃንያለም ነፍስያዬን አያስጨንቋት?? " የሚያደርገው ግር ብሎት እጄን ባልጨበጠ እጁ እንባዬን ሊጠርግ ይታገላል::
"የሄ.... ድክ ... መስሎኝ..." ብዬ መጨረስ አቃተኝ:: ህቅ ማለት ቀጠልኩ:: ክፉ ነገር እንደነገርኩት ሁሉ ... ዝግንን ብሎት እጄን እንደጨበጠ ከተቀመጠበት እየተነሳ
"መሄድ ሲሉ?? መሄድ ! መሄድ!? ... ይቅር ይበሎት! ምኑን አሰቡት? እንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ እንዴት ትቼዎት እሄዳለሁ?? እንዴት ያለ ሰው ነው ብለው ነው የሚያስቡኝ?" አለ ቁጣም በቀላቀለው አነጋገር!!
"ይቅርታ አድርግልኝ!! እኔ አላውቅም!! ምን እንደማስብ... ግራ የገባኝ ሰው ነኝ! ካንተ እና ከተናኜ ውጪ ማን ምን እንደሆነ እንኳን አላውቅም!! አንተ ብትሄድ..." ብዬ መጨረስ ቸገረኝ:: ተመልሶ እየተቀመጠ በሚለማመጥ ድምፅ
"የትም አልሄድም! እርሶ አልፈልግህም ብለው እስካላበረሩኝ ድረስ እኔ የትም አልሄድም!!" አለኝ:: ...
3.0K viewsDAVE / PAPI, 18:29