2023-03-12 12:13:42
እንደሃገር ሃብታችን ማህበራዊነታችን ነው የሚለውን መተማመኛ ወደ #ነበር እየለወጥነው ነው?
በኢኮኖሚክስ ትምህርት ውስጥ Zero Price ወይም በነጻ የሚቀርብ አገልግሎትም ሆነ ቁሳቁስ የሚባል ነገር ብዙም የለም! ስለዚህ በኢኮኖሚክስ ምንም የማያመርት እና ሰርቶ ገቢ የማያስገባ ሰው ዋስትና የለውም ማለት ነው! የፍላጎት እና የአቅርቦት ግራፍ ሲሰራ ከዜሮ የማይጀምረው ይህንን ለማሳየት ሲባል ነው፡፡
ነገር ግን ይሄ የኢኮኖሚክስ አመክንዮ ውድቅ እንዲሆን የሚደረገው ሰዎች በመረዳዳት ያላቸውን ተካፍለው ሲጠቀሙ እና ሲኖሩ ብቻ ነው! ሀረር ተወልጄ ሳድግ ቆንጆ ማሳያዎች ነበሩኝ ለሌሎቻችሁም በያላችሁበት ተመሳሳይ ይመስለኛል።
የኢኮኖሚክስ ትምህርት በጥላቻ የተሞላ እና ወደ አንድ ወገን ብቻ ያጋደለ ነው ወይም ስለትርፋማነት ብቻ ነው የሚጨነቀው የሚል የሚያከራክር ሃሳብ አለበት ይሉታል (Economics has Bias!) በደረስንበት ግሎባላይዝ ዓለም ትችቱ እውነትነት ያለው ቢመስልም ታሪካቸውን ባለቀቁ የዓለም ሀገራት ደግሞ እውነታው የተለየ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ::
#ለምሳሌ፡- ለረጅም ዘመናት ኢኮኖሚስቶች የሚያስቡት አንድ ፕሮጀክት፤ ፕሮግራም እና ፕላን ምን ያህል ወጪ አስወጥቶ ምን ያህል ትርፍ ያስገኛል? ሲከፋ አብዛኛውን ሰው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተጀምሮ በጣም ጥቂቶች ብቻ ቢጎዱ ምንም ችግር የለውም (Tolerated Point!)፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እስካመጣ ድረስ የተወሰኑ ግሩፖዎች ከኢኮኖሚያዊው እንቅስቃሴ ተጠቃሚነት ውጪ ቢሆኑም ለግዜው አካሄዱ ኢኮኖሚያዊ እድገትን እስካመጣ ድረስ ምንም ችግር የለውም፤ ወዘተ የሚሉ አስተሳሰቦች ነበሩበት፡፡
ለዚህም ነው ጥቂት ሃብታም ብዙ ድሃ የተፈጠረበት ኢኮኖሚያዊ ደረጃ በብዙ ሀገራት የሚስተዋለው ይህ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ሲወጣ ለዝቅተኛው፤ ለመካከለኛው እና ለከፍተኛ ገቢ ባለቤቶች እየተባለ የሚቀረጸው አስተምሮቱ የፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ነው፡፡ #ለምሳሌ፡- Pro-Poor Program በብዙ ባደጉም ባላደጉም ሀገራት የከፋ ድሃውን ዜጋ ከመካከለኛው ገቢ ባለቤት ጋር የማቀራረቢያ ዘዴ ነው፡፡
#ለምሳሌ፡- ለመሰረተ ልማት ግንባታ ወይም ሰፊ ፕሮጀክት ለማቋቋም በቂ ያልሆነ ካሳ እየከፈሉ የማስነሳት አካሄድ ከነባር ግለሰቦቹ ኑሮ በላይ የፕሮጀክቱ መተግበር ለብዙሃኖች በገቢ፤ በስራ እድል፤ በገጽታ ግንባታ፤ ወዘተ የተሸላ ሚና አለው በሚል መነሻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት አይነት አስተሳሰቦች አሁን ላይ እድገት ሁሉንም አካል እኩል ተጠቃሚ ማድረግ አለበት በሚል አስተሳሰብ፤ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማህበራዊ ሁኔታዎችን ከግምት መክተት አለበት በሚል አስተሳሰብ፤ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ባህልን፤ ሃይማኖትን፤ አካባቢን፤ ወዘተ ሳይጎዳ መከናወን አለበት በሚል አስተሳሰብ አዲስ አይነት አካሄዶች በመምጣታቸው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ይታይበታል የሚባለውን ወገንተኛ አስተሳሰብ መለወጥ ጀምሯል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑት Institutional Economics፤ Welfare Economics፤ Development Economics፤ ወዘተ የሚሉት የኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፎች የሚያራምዱት ሃሳብ ነው፡፡
በኢኮኖሚክስ ትምህርት ውስጥ ሃብት በተለያየ መልኩ ይገለጻል፡- እነሱም መሬት፤ የተፈጥሮ ሃብት (ማዕድን)፤ የተማረ ሰው ሃይል፤ ቁሳቁስ፤ ገንዘብ እና ቴክኖሎጂ ሲሆኑ ከቅርብ ግዜ ወዲህ #አብሮ_የመኖር እና #የመረዳዳት_ባህል እንደ አንድ ሃብት መቆጠር ጀምሯል፡፡
ኢትዮጲያ ለሺህ ዘመናት ከብዙ የዓለም ሃገራት በተሻለ መልኩ እንደልዩነት መፍጠሪያነት ስትጠቀምበት የኖረችበት ዋናው ሃብቷ Social Capital (መረዳዳት፤ አብሮ መኖር፤ መጠያየቅ፤ ወዘተ) ነው፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚፈጥሩት መሬት፤ የተፈጥሮ ሃብት (ማዕድን)፤ የተማረ ሰው ሃይል፤ ቁሳቁስ፤ ገንዘብ እና ቴክኖሎጂ እርስ በርስ ከመረዳዳት በበለጠ መሰረታዊ ተጽኖ ኢትዮጲያ ውስጥ አልነበራቸውም ብል ብዙ አይጋነንም!
ቀጣይ የኢኮኖሚያችን መሰረት መሆን ያለበትም አብሮነት፤ መተማመን እና መረዳዳት ነው፡፡ ማህበራዊ ካፒታል በሰፊው የሚያተኩረው ማህበረሰባዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ማህበራዊ ቡድኖችን ውጤታማ በሆነ መልኩ በማስተባበር ነው፡፡ እነዚህም ማህበራዊ ግንኙነቶች፤ የጋራ ስሜትን፤ የጋራ መረዳት፤ የተጋሩ ደንቦች፤ የተጋሩ እሴቶች፤ መተማመን፤ ትብብር እና የጋርዮሽነት ተግባራት ናቸው፡፡
2.0K viewsWasyhun Belay, 09:13