2023-01-03 20:12:40
ጠቃሚ ዕውቀት
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
96፥5 *ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን*፡፡ عَلَّمَ ٱلْإِنسَٰنَ مَا لَمْ يَعْلَمْ
በሥነ-ዕውቀት ጥናት "መውሡዓህ" مَوْسُوعَة ማለት "መድብለ-ዕውቀት"encyclopedia" ማለት ሲሆን ፍልስፍናን መሠረት ያደረገ የዕውቀት መድብል ነው፥ "ፈልሠፋህ" فَلْسَفَة የሚለው ቃል "ፈልሠፈ" فَلْسَفَ ማለትም "ተፈላሰፈ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ፍልስፍና" ማለት ነው፥ ፍልስፍና የሚፈላሰፍ "ፈላስፋ" ደግሞ "ፈይለሡፍ" فَيْلَسُوف ይባላል። ፍልስፍና "ኢስሙል ኢሥቲፍሃም" اِسْم الاِسْتِفْهَام ማለት "መጠይቅ ተውላጠ-ስም"interrogative pronoun" ያለበት ሲሆን እነዚህም፦
"ማ" مَاْ ማለት "ምንድን"what" ማለት ሲሆን "ምንነትን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"መን" مَنْ ማለት "ማን"who" ማለት ሲሆን "ማንነትን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"መታ" مَتَى ማለት "መቼ"when" ማለት ሲሆን "ጊዜን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"አይነ" أَيْنَ ማለት "የት"where" ማለት ሲሆን "ቦታን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"ከይፈ" كَيْفَ ማለት "እንዴት"how" ማለት ሲሆን "ሁኔታን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"ሊመ" لِمَ ማለት "ለምን"why" ማለት ሲሆን "ምክንያትን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው፣
"ከም" كَمْ ማለት "ምን ያህል"how much" ማለት ሲሆን "መጠንን" የምጠይቅበት መጠይቅ ተውላጠ-ስም ነው።
ፍልስፍና በራሱ ችግር ያለው ነገር ባይሆንም መሬት ላይ የማይተገበር እና በቃላት ተጀምሮ በቃላት የሚያልቅ አየር ላይ የተንሳፈፈ ዕውቀት ሁሉ መዋዕለ ጊዜን እና መዋዕለ ጉልበትን ከማፍሰስ እና ከማባከን ውጪ ለዲንያህ ሆነ ለአኺራ ሕይወት የሚፈይደው አንዳች ነገር እና ቁብ የለም፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 34, ሐዲስ 17
ጃቢር እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"አሏህን ጠቃሚ ዕውቀት ጠይቁት! ከማይጠቅም ዕውቀት በአሏህ ተጠበቁ!"*። عَنْ جَابِرٍ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ " سَلُوا اللَّهَ عِلْمًا نَافِعًا وَتَعَوَّذُوا بِاللَّهِ مِنْ عِلْمٍ لاَ يَنْفَعُ "
የማይጠቅም ዕውቀት የተቆላ ገብስ ነው፥ ሲበሉት ይጣፍጣል ሲዘሩት ግን አይበቅልም። ጠቃሚ ዕውቀት ለእለት ለእለት ሕይወታችን የሚሆን የነቅል ሆነ የዐቅል ዕውቀት ያካትታል። "ነቅል" نَقْل የሚለው ቃል "ነቀለ"نَقَلَ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን ከአሏህ በነቢይ የሚተላለፍ ዕውቀት ነው፥ "ዐቅል" عَقْل የሚለው ቃል ደግሞ "ዐቀለ"عَقَلَ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን በቀለም የሚተላለፍ ዕውቀት ነው። አምላካችን አሏህ ሰውን ያላወቀውን ሁሉ በቀለም ያሳወቀው ነው፦
96፥4 *"ያ በብርዕ ያስተማረ"*፡፡ ٱلَّذِى عَلَّمَ بِٱلْقَلَمِ
96፥5 *ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን*፡፡ عَلَّمَ ٱلْإِنسَٰنَ مَا لَمْ يَعْلَمْ
"ቀለም" قَلَم የሚለው ቃል "ቀለመ" قَلَمَ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ብዕር" ማለት ነው። ከሞት ጋር ሥራዎች ሲያከትሙ ጠቃሚ ዕውቀት ግን ለአኺራም አጅር የሚያስገኝ ነው፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 25, ሐዲስ 20
አቡ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"ሰው በሞተ ጊዜ ከሦስት ነገር ከሶደቀቱል ጃሪያህ ወይም በእርሱ የሚጠቀሙበት ዕውቀት አሊያም ዱዓእ የሚያደርግለት ሷሊሕ ልጅ በቀር ሥራው ያከትማል"*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ " إِذَا مَاتَ الإِنْسَانُ انْقَطَعَ عَنْهُ عَمَلُهُ إِلاَّ مِنْ ثَلاَثَةٍ إِلاَّ مِنْ صَدَقَةٍ جَارِيَةٍ أَوْ عِلْمٍ يُنْتَفَعُ بِهِ أَوْ وَلَدٍ صَالِحٍ يَدْعُو لَهُ "
መልካም ሥራዎች መሠረታቸው ጠቃሚ ዕውቀት ነው። ያለ ዕውቀት ማመን እና መልካም ነገር መሥራት እምነቱም ጭፍን እምነት ነው፥ ሥራውም እዚሁ ዲንያህ ላይ የሚቀር ነው፦
17፥36 *"ለአንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል! መስሚያ፣ ማያም፣ ልብም እነዚህ ሁሉ ባለቤታቸው ከእነርሱ ተጠያቂ ነውና"*፡፡ وَلَا تَقْفُ مَا لَيْسَ لَكَ بِهِ عِلْمٌ ۚ إِنَّ السَّمْعَ وَالْبَصَرَ وَالْفُؤَادَ كُلُّ أُولَـٰئِكَ كَانَ عَنْهُ مَسْئُولًا
"ለአንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል" የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት! ይህንን የዐቅል ሆነ የነቅል ዕውቀት መፈለግ በሁሉም ሙሥሊም ላይ ግዴታ ነው፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 229
አነሥ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው፦ "የአላህ መልእክተኛም"*" አሉ፦ *"ዕውቀት መፈለግ በሁሉም ሙሥሊም ላይ ግዴታ ነው"*። عَنْ أَنَسِ بْنِ مَالِكٍ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ طَلَبُ الْعِلْمِ فَرِيضَةٌ عَلَى كُلِّ مُسْلِمٍ
ይህንን ጠቃሚ ዕውቀት ግዴታ የሆነው ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማሳወቅም ጭምር ነው፥ ማንም ስለ ዕውቀት የሚያውቀውን ተጠይቆ የደበቀ በትንሳኤ ቀን ከእሳት ልጓም ይለጎማል፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 266
አቡ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"ማንም ስለ ዕውቀት የሚያውቀውን ተጠይቆ የደበቀ በትንሳኤ ቀን ከእሳት ልጓም ይለጎማል"*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ " مَنْ سُئِلَ عَنْ عِلْمٍ يَعْلَمُهُ فَكَتَمَهُ أُلْجِمَ يَوْمَ الْقِيَامَةِ بِلِجَامٍ مِنْ نَارٍ "
አምላካችን አሏህ ጠቃሚ ዕውቀት ዐውቀው ከሚያሳውቁ ያድርገን! አሚን።
ሼር
ከኡስታዝ ወሒድ ዑመር
ወሠላሙ ዐለይኩም
---------------------------------------------------------
ተጠራሩ፣ ሼር አርጉ፣ አንብቡ፣ አስነብቡ፣ ሁሉም ቦታ አሰራጩት! ሂዳያህ ያገኘውን ሰው የሚያገኘውን አጅር ከእርሱ ላይ ሳይቀነስ ሳይጨመር ታገኛላችሁ፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 206
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "ማንም ወደ ምሪት የሚጣራ ጠሪ ጥሪውን የተከተሉት ከሚያገኙትን ምንዳ ከእነርሱ ላይ ሳይጓደል ያገኛል"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ قَالَ " مَنْ دَعَا إِلَى هُدًى كَانَ لَهُ مِنَ الأَجْرِ مِثْلُ أُجُورِ مَنِ اتَّبَعَهُ لاَ يَنْقُصُ ذَلِكَ مِنْ أُجُورِهِمْ شَيْئًا " .
319 views17:12