2023-01-08 16:17:36
#ከሕይወት_ገፅ…10
(አብዱልሀኪም ሰፋ)
:
<< ለምንድን ነው እስካሁን ያላገባሽው? ምንድን ነው እንደ ዘልዛላ ሴት የምተሆኚው ሴት ልጅ ከደረሰች የግድ ማግባት አለባት። ለምን በእድሜሽ ትቀልጃለሽ! ትዳር ይዘሽ ለምን አትሰበሰቢም? >>
<< ልክ ነህ አኮ ግን እይ እነዛ ታናናሽ ወንድምና እህቶቼ ናቸው። ልጅነታቸው ብዙ የሚያስቦርቃቸው አየሀቸዋ ሲጫወቱ። እንደምታየን በኑሯችን ደከም ብለን ነው የምንኖረው። አየሀት ይህቺ ቤት ተከራይተን ነው የምንኖርባት። ወላጆቼ ጤና ከራቃቸው ሰንበትበት ብለዋል። እነዚህ ነፍሶች ሁሉ እገዛዬ ያሻቸዋል። ስለነሱ መኖር ነው እያኖረኝ ያለው። ስለኔ መኖር ብጀምር ምን የሚሆኑ ይመስልሀል? ግዴለም ማወቅ አይቻልህም! የተቸገሩ ቤተሰብ ያላትን ሴት እስከነ ቤተሰቧ የሚቀበል ስንቱ ነው? ተወው እሱንም! እሺ የሆነው ይሁን ብሎ ያገባኝ በኋላ ላይ ቤተሰቦቼን አይናችሁ ላፈር ቢል ምንድን ይወጠኛል? የባል ሀቅ ባለመወጣት ልከሰስ ወይስ የወላጆችን ሀቅ በማጉደል ልቀጣ? እውነት ነው ትዳር ያስፈልገኛል! ቤተሰቦቼስ መኖር አያስፈልጋቸውም? ወንድምና እህቶቼስ ተስፋቸውን ማጣት አለባቸው? በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ሴትነቴ ትዳር የሚቀበል ይመስልሀል? >>
<< ግን አኮ…>>
<< ግዴለህም እኔን ሆነህ ኖረህ ስለማታውቅ አትረዳኝም!
ታውቃለህ ለምወዳቸውና ለቤተሰቦቼ ስል ከመከራቸው የሚያላቅቃቸው እስከሆነ ድረስ ወንድ አልመርጥም። ግን የታለ? የምወደውና የማፈቅረው ከዚህ ጭንቀትና መከራ የማይገላግለኝ ከሆነ ምን ይፈይድልኛል? እርግጥ ነው የሚያፈቅሩትና የሚወዱት ማግኘትና መኖር ደስ ይላል። ግን ሕይወት እንደምታስበው ደስታ አይደለም። ከነፍስህ በላይ የምትሳሳለቸው ሰዎች እየተቸገሩ እድሜ ዘላለሙን የሚያፈቅርህ ማግኘት ምን ይፈይድልሀል? ምናልባት ነፍስህ ያን ሰው ባገኘችውና ባሰበችው ቁጥር ትደሰት ይሆናል እንጂ አትረካም። ደግሞም ይበልጥ ያ ሰው እራስ ወዳድ ያደርግሀል። በእድሜሽ ለምን ትቀልጃለሽ አልከኝ አይደል? ምነው በእድሜዬ በቀለድኩና ይሄ ምክርህ ባስደነገጠኝ!
ትዳር ይዘሽ ለምን አትሰበሰቢም አልከኝ አይደል ምናለበት መሰብሰቡ ቀርቶብኝ የምወዳቸው እፎይ ባሉልኝ! >>
የሕይወትን ውጣ ወረዶች በመነፅራችሁ አሾልካችሁ አልያም በሰሚ ሰሚ ሳይሆን ቢያንስ በአይናችሁ ተመልከቱ። በዙርያችን በመሰለኝ ስም እየሰጠናቸው እያቆሰልናቸው ያሉ አሉ። ሁሉንም በልባቸው ችለው፣ ውጠውና ደብቀው እየታገሉ ያሉት ላይ እሾኽ የኾኑ ንግግሮችን ወደ ቁስላቸው አትስደዱ። ግዴላችሁም ሕይወት ለሌሎች እኛ እንደምናስበውና እንደምንገምተው አይነት አይደለም። ሰውን ባትረዱ እንኳ ወደ ውስጥ እንዲያነባ ሰበብ አትሁኑ!
:
@Venuee13
@Venuee13
53 viewsGlamor, 13:17