2023-03-18 08:07:31
የጥናትና ምርምር ቅደም ተከተላዊ ይዘቶች/ደረጃዎች/
በሁሉም የጥናትና ምርምር ዓይነቶች ተቀራራቢ ይዘት/ደረጃዎች/ የሚኖራቸው ቢሆንም የተወሰኑ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡
ነገር ግን በተለይ በተግብራዊ ጥናትና ምርምር ውስጥ
የመጀመሪያው ክፍል መግቢያ /Introduction/ ሲሆን በዚህ ውስጥ የጥናቱን ርዕስ ከመምረጥ
ጀምሮ የጥናቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ ፅንሠ ሀሣባዊና ታሪካዊ ዳራ፣ የጥናቱ ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ የጥናቱ ችግር ምንነትና የጥናቱ ወሰን ወዘተ ይገለጽበታል፡፡
ሁለተኛው ክፍል የተዛማጅ ጽሑፍ ክለሣ ሲሆን በዚህም ከጥናቱ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ጽሑፎች የሚገመገሙበት፣ የሚነፃፀሩበትና ልምድ የሚወስዱበት ክፍል ይሆናል፡፡
3ኛው ክፍል የጥናቱን ዘዴ ( Methodology) የሚገለጽበት ነው፡፡
4ኛው ደግሞ የተሰበሰበው መረጃ የሚተነተንበትና የሚተረጐምበት ሲሆን 5ኛው ማጠቃለያ እና የውሣኔ አስተያየት የሚሠጥበት ክፍል ነው፡፡
ከነባራዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መረዳት እንደተቻለው ብዙ ሰዎች በትምህርት ነክ ችግሮች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
በምን መልክ የምርምር ሥራ መሥራትም እንዳለባቸው ይወስናሉ፡፡ ዋነኛው ችግር ግን ምርምር የሚያደርጉበትን ርዕስ ማወቅና መወሰኑ ላይ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ችግር ምንጭ ነው ተብሎ የሚገመተው ሰዎች መሥራት የሚፈልጉት ጥናት አዲስ፣ ልዩ የሆነ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ምርምር እንዲሆን ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ፍላጐቱና ሃሣቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ የዚህ ዓይነት ሃሣብ ተመራማሪውን በጣም ከባድና መረጃ አልባ ወደሆነ መስክ ይመራውና ችግር ላይ ይጥለዋል፡፡
እዚህ ላይ እንድንረዳው የሚያስፈልገን ዋነኛ ነጥብ ማንኛቸውም የምርምር ፕሮጀክቶች ከማንም አያንሱም፡፡ የሌሎች የምርምር ውጤቶችን ማንበብና ማጤን አዲስ አሠራርን እንድንፈጥር ወይም ለሌሎች አዳዲስ ግኝቶች እንድንጓጓ ወይም ግኝቶችን በተለየና አዲስ በሆነ መልክ ለመጠቀም ምርምር እንድናደርግ ይገፋፋናል፡፡
በአጠቃላይ የምርምርን ርዕስ ለመወሰን በመስኩ ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖር መጣርን ይጠይቃል፡፡ አንድን ጥናት ወይም ምርምር ለማድረግ ከሚገፋፉ ምክንያቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. በአንድ በተወሰነ የጥናት መስክ የታወቀው ነገር ውሱን ሆኖ ሲገኝና ሰፋ ያለ እውቀትና ግኝት እንዲኖር ሲያስፈልግ፣
2. በጥልቀት ያልተጠና ዕውቀት በመኖሩ ጅምር አስተሳሰብን ፍፃሜ ለማድረስና የተሟላ እውቀት ማግኘት አስፈላጊ ሲሆን፣
3. የዕውቀት መረጃዎች ያሉና የታወቁ መስለው ነገር ግን ያልተረጋገጡ ሆነው ይህን መሥራት የግድ ሆኖ ሲገኝ፡፡
4. እየሠራነው ላለው ተግባር ለውጥ/ውጤት ስለመምጣቱ ለማረጋገጥ ስንፈልግ ወይም ለውጥ አለማምጣታችንን ስናረጋጥ ምክንያቱን ለማወቅ ስንፈልግ ፣ ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው የምርምር ዋና ዋናዎቹ ቅደም ተከተላዊ ደረጃዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ነጥብ ስናነሣ የሚከተሉትን ደረጃዎች ማንሣት ይቻላል፡፡
1.7.1. የምርምርን ርዕሰ ጉዳይን በሚገባ መግለጽ/ Statement of the problem/
ከላይ እንደተገፀው ማንም ሰው የምርምር ርዕስ ነው በሚል አስተሳሰብ አንድን ርዕስ እንደመሰለው ማስቀመጥ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በትክክልና በጥልቀት አውጥተው አውርደው በአእምሮ ውስጥ ጉልህ የሆነ ግንዛቤ/ምስል እንዲፈጥር ማድረግ
ካልተቻለ ማንኛውም ርዕስ ለምርምር ብቁ ርዕስ ላይሆንልን ይችላል፡፡ ስለዚህ ምርምር የሚደረግበት ርዕስ ጉልህና አሻሚ ትርጉም የሌለበት ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ማንኛውም ተማራማሪ የምርምሩን ርዕስ በትክክል ለመግለጽ በሚፈልግበት ጊዜ በአጽህኖት ሊያስታውሳቸው የሚገባ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
1.7.2. መላምት /Hypotheses of the study/
መላምት / Hypotheses/ ተመራማሪው ምርምሩን ለመተግባር ሲነሳ በመጀመሪያ አንዳንድ ጥርጣሬያዊ ጥያቄዎችና መልሶች ወይም መፍትሔዎች ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ባቀረብነው ምሳሌ የተማሪውን የሥነ ምግባር ጉድለት መንስኤዎች ብናስታ የቤተሰብ አያያዝ
በትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ማምጣትና ተስፋ መቁረጥ ወዘተ….
የሚሉት ለተማሪው የጠባይ መበላሸት ምከንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በመላምት መልክ የቀረቡ ሃሳቦች ናቸው፡፡ እነዚህም በጥናቱ ውስጥ ሊረጋገጡ ወይም ሊሻሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ መላምት በጥያቄ ወይም በዓረፍተ ነገር መልከ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ለምሣሌ፡ መላምት 1፡ ተማሪውን በጥባጭ ያደረገው የቤተሰብ አያያዝና አስተዳደር መበላሸት ነው ፡፡ /ዓረፍተ ነገር/
መላምት 2፡ በተማሪው ጠባይ ላይ ተጽእኖ ያደረገው የጓደኞቹ ግፊት ይሆን? /በጥያቄ መልክ/
1.7.3. መሠረታዊ ጥያቄዎች /Basic Research Questions/
እነዚህ በጥናቱ ውስጥ በተለያዩ ዘዴዎች መረጃዎችን በማሰባሰብ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዌች ናቸው፡፡ የእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የመላምቶችን እውነተኛነት ወይም ሃሰተኛነት ግልጽ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ የተቀጠሰውን ተማሪ ሁኔታ ብናይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
የትምህርት ውጤቱ ምን ይመስላል የቤተሰቡ አያያዝና አስተዳደር ምን ይመስላል ወዘተ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ተመራማሪው መመለስ ከቻለ ለልጁ ጠባይ መበላሸት መንስኤ የሆነውን ነገር ማግኘት ይችላል፡፡ ስለዚህ በምርምር አለም ተመራማሪው በጥናቱ ሂደት ውስጥ አጥጋቢ ምላሽ ሊያገኝላቸው የሚገባው አብይ ነጥቦችና ጥያቄዎች እንዳሉ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ የተገለፁት ሁለት ጉዳዮች ተመሣሣይ አገልግሎት ያላቸው በመሆኑ አጥኝዎች ከሁለቱ አንዱን ብቻ በመውሰድ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ሰለዚህ እኛም በጥናታችን የሚመቸውን አቀራረብ በምረጥ አንድም በመላ ምት ወይም በመሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ መሠረት አድርገን መነሣት እንችላለን፡፡
1.7.4. የጥናቱ አስፈላጊነት /Significance or Justification of the study/
አንድ ጥናታዊ ምርምር ሲደረግ /በተለይም በተግባር ተኮር ጥናትና ምርምር/ በማንኛውም መልኩ ቢሆን የጥናቱ ዋነኛ ዓላማና ግብ የችግሮችን መፍትሔ ለማግኘት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁም መሠረት እንደ ችግሮቹ አንገብጋቢነት ደረጃ በወቅቱ መፍትሔ ቢሰጣቸው ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን መገለጽ ይኖርበታል፡፡ ገለፃው ከግል፣ ከቡድን፣ ከብሔራዊና ከዓለም አቀፋዊ አኳያ ሊታይ ይችላል፡፡ ከማንኛወም አንፃር ቢሆን ጥናቱና ምርምሩ በውጤቱ ማኀበራዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ተመራማሪ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ምርምር በዘፈቀደ ለሱ እንደተሰማው ሳይሆን የችግሩን አንገብጋቢነት ከማኀበራዊ ጠቀሜታ አኳያ በመገምገምና ስለጥናቱም ያለውን ምክንያት በግልጽ በስቀመጥ መሆን ይኖርበታል፡፡
1.7.5. የጥናትና ምርምር ክልልን መወሰን ( Delimitation)
ከብዙ ጥናታዊ ምርምር ግምገማ መረዳት እንደተቻለው የብዙ ጀማሪ ተመራማሪዎች ችግር የጥናትን ክልል መወሰን አለመቻል ነው፡፡ አንድ ተመራማሪ የምርምር ርዕሱን በሚገባ ከገለፀ በርዕሱ ስለተገለፀው ጉዳይ ከተለያዩ ገጽታዎች አንፃር በአንድ ወቅት በጥልቅ ማየት/ማጥናት/ ይቸግረው ይሆናል፡፡ ወይም የአንድን ጉዳይ ሁለንተናዊ ገጽታ ላጥና ብሎ ቢነሳም ምርምሩ ከጥልቀት ይልቅ ስፋት ብቻ ይኖረውና እያንዳንዱ ነጥብ በተሟላና በጥልቀት ሳይዳሰስ ሊታለፈ ይችላል፡፡
3.2K views05:07