2022-05-16 19:28:53
ዳግማዊ ምኒልክ ካህናትንና ሴቶች ሳይቀሩ ባንድነት አስተባብረው ኢትዮጵያውያንን ባንድ እግር አቁመው በአገር ወራሪ ፊት አሰልፈዋል ቀኑን ሙሉ በማዋጋት ይኸን ዓለም የተዶነቀበትን ድል ባኙበት ማታ ወደ ሰፈራቸው ሲመለሱ : አዲ ፈቂ ጐታ ላይ ወጥተው በእንዳ ሰንበት ቤተክርስቲያን ገብተው ይኸን ድል ለሰጣቸው እግዚአብሔር ምስጋና አቅርበዋል። አዲ ፈቂ በእንዳ ኪዳነ ምሕረት በመነኮሲይቶ ተራራ መካከል የሚገኝ ነው። የአዲ ፈቂም ተራራ ከባሕር ከፍታው 2062 ሜትር ነው። ከሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ወደዚህ መሔድን የመረጡት ምናልባት ጦርነቱ የተደረገው የካቲት 23 ቀን እሑድ ስለሆነ የአዲፈቂ ቤተ ክርስቲያን እንዳ ሰንበት (የሰንበት ቤተ ክርስቲያን) ስለሆነ ዕለተ ሰንበት ‘የለቱ ለት ቀናኝ’ በሚሉ እምነት ይሆናል።
ከዚያ ወርደው ሠራዊቱ “እየገደለ ሰጠው ላሞራ!” እያለ በሆታ እያጀባቸው በደስታና በእልልታ ወደ ሰፈራቸው ደረሱ። ወደ ድንኳናቸው ገብተው በዙፋናቸው እንደ ተቀመጡ ፥ ጦርነቱን እንደ ወንድ በትጋት የተካፈሉት የሚወድዋቸው ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ልማድ ለዠግና ፥ ለገዳይ እንደሚደረገው ሁሉ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ተቀመጡበት ዙፋን ቀርበው እጅ ነሥተው የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን የወርቅ ሎቲ በዦሮአቸው አንጠለጠሉላቸው።
በማግሥቱም ፥ በዓድዋና በአክሱም ዙሪያ ያሉ ካህናት ለድሉ በዓል ተሰብስበው ነበርና ምራቱ በቅድሚያ ለአክሱም ካህናት ስለተሰጠ ካህናቱ ከድጓ ውስጥ “ሞዖ ለሞት ሰዓሮ ለጣኦት ወገብረ ትንሣኤ በሰንበት” (የድጓው ትርጉም “ሞትን አሸነፈ ጣኦትንም ሻረ ፥ በሰንበትም ትንሣኤ አደረገ” ተብሎ ለጌታችን በጳውሎስ የተነረውን ለምኒልክ ለማውረስ ነው። ጢሞቴዎስ ምዕ.1 ቁ.10 ፥ ዕብ.2 ቁ.14) የሚለውን ጥቅስ ገሠው አዜሙ። ምስማክም “እንተ ቀጥቀጥኮ አርእስቲሁ ለከይሲ ወትሁቦሙ ሲሳዮሙ ለሕዝበ ኢትዮጵያ” የሚለው ከዳዊት መዝሙር ተዘመረ።
በአዲስ አበባ ገና የጦርነቱ ወሬ ሳይሰማ ውጊያውና ድሉ በተፈጸመበት ቀን የጊዮርጊስ ለት የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ መምህር ጽጌ የሚባሉት ሊቅ የተቀኙት መወድስ ቅኔ እንዶ ትንቢት ሆኖ ተደንቆ ላቸዋል። ቅኔው ታሪካዊ ስለሆነ እንደሚከተለው አስፍረነዋል።
በሕፅነ ምኒልክ ይረፍቅ ሰማዕተ ልዕልና
ወበሕፅነ ሰማዕት ይትሐወስ አሰረ ምኒልክ ላዕክ
እስመ እም ሮምያ ፈትተ አድባረ ድንጋጼ ወሀውከ
ምኒልክ ንጉሠ አድኅኖ ዘኢዮር መልአክ
ወእግረ ምኒልክ ኢይትሐወክ
እስመ በቅድሜሁ የሐውር ጸያሔ ፍኖት ወልደ አምላክ
ቡርክትሂ ገነተ ጽጌ እስመ ውእቱ ቡሩክ
ዓለመ ምኒልክ ቀዳማዊ ዘይመጽእ ምኒልክ
ወሎቱ ሶርያ ትሰግድ ወታስተበርክ
በጽባህ እስመ ቀርበ ሙስና ሮምያ መሥዋዕተ ሠርክ
በሙሉ ሁሉን መተርጐም ምንም ያህል ስለማይጠቅም ከሙሉው አንዳንዱን ፍሬ ነገር ግዕዝ ለማያውቁ እናብራራለን። አምስተኛውና ስድስተኛው ሐረግ ፥ “ወእግረ ምኒልክ ኢይትሐወክ። እስመ በቅድሜሁ የሐውር ጸያሔፍ—ኖት ወልዶ አምላክ” “መንገድ ጠራጊው ወልደ አምላክ በፊቱ ስለሚሔድ ፥ የምኒልክ እርምጃ አይደናቀፍም” ማለት ነው ወልዶ አምላክ የራስ መኰንን የክርስትና ስም ስለሆነ መኰንን ግንባር ቀደም ጦር አዝማች እየሆኑ በአላጌና በመቀሌ እየተዋጉ ለንጉሠ ነገሥቱ የጦርነት ጉዟቸውን ያቀኑትን ለመጥቀስ ነው።
ከሁሉ የቅኔ ሐረጐች የመጨረሻው መስመር ፥ “በጽባህ እስመ ቀርበ ሙስና ርምያ መሥዋዕተ ሠርክ” “የሮማ ጥፋት እንደ ዕለት መሥዋዕት በጧት ቀርቧል” ያሉት ለባለቅኔው እንደ ደንበኛ ትንቢት ተቆጥሮላቸዋል። በእርግጥም ግንባር ቀደም ሆኖ በጧት ግሥጋሤ ደርሶ የተማረከው የዤኔራል አልቤርቶኒ ጦር የተመታውና የኢጣልያ ጦር ቅስሙ የተሰበረው ከጧቱ ላይ ስለሆነ “በጽባሕ እስመ ቀርበ ሙስና ሮምያ . . .” ብለው የጦርነቱ ዕለት የጦርነቱን ወሬ ሳይሰሙ የተቀኙትና በተግባር የተፈጸመው በትክክል ተገናኝቷል። አዲስ አበባም እንደገቡ ዐፄ ምኒልክ ይኸንኑ ሰምተው ሸልመዋቸዋል ይባላል።
ከ ተክለጻዲቅ መኩርያ
"ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት" መጽሐፍ ላይ የተወሰደ
6.9K views16:28