2022-10-06 09:59:06
«በቤተክርስቲያን የጽጌ ማኅሌት እንጂ የጽጌ ጾም የሚባል ነገር የለም» ይባላልን
━━━━━━━✦༒ ༒✦━━━━━━━
የዛሬ ዓመት ነው፤ እጅ ለመንሳትና ደጅ ለመጥናት የ«ተክልዬ» የክብር ማረፊያ ወደሆነችው የምድር ጌጥ ደብረ ሊባኖስ አቀናሁ። "ተክልዬ"ን በውሥጣቸው እንዳይ ተስፋም እንዳልቆርጥ ለተሠጡኝ አባ ጌታዬ (የመጋቢ ምትክ) እንግዳ ልጃቸው ነኝ።
ወደ እርሳቸው ማልደን እንወጣና ከወንድሞች ጋር ገብተን ቅድመ ቅዳሴ ተምረን፣ ተመክረንና አድምጠን እንወጣለን።
በዚያ ቀን በተለየ መልክ በመጪው "የጽጌ ጾም" ስለሚገኘው በረከት እየነገሩን አባቶች በልዩ ፍቅር ተጠብቀው እንዴት እንደተጠቀሙባት እየነገሩን እንድንዘጋጅ ይመክሩን ጀመር ። በቸኮለ ማቅኛ (ድፍረት በነዳው አንደበት) ድንገት ማረም አማረኝና «በቤተክርስቲያን ወርኃ ጽጌ ፣ ዘመነ ጽጌ ፣ ማኅሌተ ጽጌ እንጂ የጽጌ ጾም የሚባል ነገርኮ የለም አባታችን!» አልኳቸው።
አልተናደዱም ግን አዘኑ። በትካዜ እጅጉን ዝግ ባለ ድምጽ "እንዲያ እያላችሁ ነው ምታስተምሩት? " አሉኝ። "ለምን መሰልዎት አባታችን… " ብዬ ለማስረዳት እኔ የጽጌን ጾም ንቄና አጥቅቼ ሳይሆን የፈቃድ ጾም ስለሆነ እያልኩ ላብራራ ስንደረደር በከንቱ መውተርተሬን ገትተው እንዲህ አሉ "ተወው የኔ ልጅ አባቴ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ብሎሃል «ጾም ታጸምም ኵሎ ፍትወታት ዘሥጋ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና» #ጾም_የሚባል_የሌለው_በዓለ_ሃምሳ_ብቻ_ነው። ቀንበር አለዘብን ብላችሁ ሸክም አታክብዱ፤ መብል ሥጋን ያገዝፋል ጾም ግን ሰውነትን ያቀላል … ዛሬማ ፍቅር በራቀበት፣ ተስፋ በመነመነበት፤ ትውልድ እያለቀ ፣ እምነት እየደረቀ ያለጊዜዋ ምድርን ልታሳልፉ ጾም የለም እያላችሁ መስበክ ጀምራችኋላ? "
ተግሳጹ ከጅራፍ በላይ የሚያም ነበር! ያኔ ኅሊናውን ዋሻ ፣ አንደበቱን ጋሻ አድርጎ ራሱን የሚከላከል «ሰው» በተፈለገው ልክና በተገቢው መንገድ መጥፋቱ እያስጨነቃቸው «ምላሱ የሰላ አእምሮው የላላ» ከልክ በላይ የሚፈነጭ የኔቢጤው በየቦታው "ጾመ ጽጌን" ማውገዙ እጅጉን ሕመም እንደሆነባቸው አስረድተው በአላዋቂነት ስለሰጠሁት ማቅኛ ይቅርታዬን ተቀብለው አለፉኝ።
ከቅዱስ ያሬድ የነገሩኝን እያሰላሰልኩ
ጾመ … ጻመወ … ጸመወ … (ጾመ፣ መከራ ተቀበለ፣ ዝምአለ) የሚለውን ዘር እየቆጠርኩና እያዛመድኩ ጿሚ፣ ጸማዊ፣ ጽምው ለመሆን በመጣር ከጽሙና መንደር ደርሶ መቆጠብ ያለውን ዋጋ እየመዘንኩ ተመለስኩ።
ባለ ብዙ መልእክት ሆኖ "«ጾም ታጸምም ኵሎ ፍትወታት ዘሥጋ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና» አለ አባቴ ቅዱስ ያሬድ" ያሉት በውስጤ ተመላለሰ።
ጾም የሥጋን ፍላጎቶች ሁሉ ጸጥ ታደርጋለች። ለወጣቶችም ዝምታን ታስተምራቸዋለች። (እውነት ነው እርጋታ፣ ዝምታ ፣ ጽሙና… የጾም ውጤት ነው)
በቤተክርስቲያናችን የበዙ የጾም ቀናት አሉን ፤ በዓመት ውስጥ በአጠቃላይ ወደ ፪፻፷ ገደማ ይደርሳሉ ከእነዚህ ውስጥ ወደ ፩፻፹ የሚጠጉ ቀናት ለሁሉም አማንያን እንደ ግዴታ በአዋጅ አጽዋማት ውስጥ ተካትተዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ በካህናቱ እና ሌሎች ምዕመናን በቀኖና ፣ በፈቃድ… የሚጾሟቸው ናቸው። መናንያኑ ግን ከዓመት እስከ ዓመት የዱር ዕፀው ቅጠላ ቅጠል ከውኃ ጋር ሰንበትና በዓለ ፶ እየቀመሱ ከዓመት እስከ ዓመት ይጾማሉ።
【 Ethiopian Christians observe an extraordinary number of fast days, generally reckoned to be about 250. Of these approximately 180 are obligatory for all believers, while the rest are observed by the clergy and other particularly devout individuals. In addition to the organized calendric fasts, throughout the history of the Ethiopian Church there were ascetics renowned for their extreme fasting, often subsisting on little more than wild plants and water.】 ⇝ Sergew Hable Selassie “Worship in the Ethiopian Orthodox Church” & "The Church of Ethiopia: a Panorama of History and Spiritual Life"
✧ ቅዱስ ያሬድ ሌላ ምክርም አለው ፦
⇨ "በፍኖተ ጽድቅ ፍትሑ ለእጓለ ማውታ ወአነሂ እትመየጥ ኀቤክሙ ለሣህል ከመ ፈለገ ሰላም ዛቲ ጾም በቍዔት ባቲ ትፈሪ ጽድቅ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ወታበጽሕ ውስተ አዕምሮ ዚአሁ"
➺ በእውነት መንገድ ለድሃ-አደግ ፍረዱ (የተቸገረውን እርዱ) እኔም ወደእናንተ ለይቅርታ እንደ ሰላም ወንዝ እመለሳለሁ፤ ጥቅም የሚገኝባት ይህች ጾም ጽድቅን የምናፈራባት ለወጣቶች እርጋታን የምታስተምር እርሱን ወደማወቅ የምታደርስ ናት ።
✧ የተዋህዶ ዓይን የኢትዮጵያ ብርሃን ቅዱስ ያሬድ ሌላም ምዕዳን ይጨምራል
⇨ ጾም ቅድስት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ተመጠወ ሙሴ ሕገ እግዚአብሔር ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ኤልያስ ዓርገ ውስተ ሰማያት ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ዳንኤል ድኅነ እምአፈ አናብስት ጾም ቅድስት ሶስና ድኅነት እምዕደ ረበናት ጾም ቅድስት ዓቀመ ኢያሱ ፀሐየ በገባዖን ጾም ቅድስት ጳውሎስኒ ይቤ ትግሁ እንከ አኃውየ በጾም ወበጸሎት ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ጾም ቅድስት ትሚህሮሙ ለወራዙት ጽሙና።
➺ ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች። ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች በተቀደሰችዋ ጾም ሙሴ የአምላኩን ሕግ ተቀበለባት፤ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች ቅድስት ጾም ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገባት ፤ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች ቅድስት ጾም ዳንኤል ከአንበሶች አፍ ዳነባት በዚህች ቅድስት ጾም ሶስና ከመምህራኑ ክስ ተርፋለች በዚህች ቅድስት ጾም ኢያሱ በገባዖን ፀሐይን አቆመ ። ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት! ጳውሎስ እንዲህ አለ ‘ እንግዲህ ወንድሞቼ በጾምና በጸሎት ትጉ’ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች።
✧ ደራሲውም እንዲህ ሲል መክሮናል
… ማርያም ታቦት ጽላተ ኪዳን ሐዲስ፣
ቅብዕኒ ርጢነ ጾም እስከ ሰኮና እግር ወርእስ፣ እስመ ጾም ትፌውስ ሕማማ ለነፍስ።
➺ ለሐዲስ ኪዳን ጽላት ታቦቱ ፡ ማርያም አንቺ ነሽና የጾም መድኃኒቱን ቀቢኝ ፡ ከራስጠጉር እስከ እግር ሰኮና
የነፍስ ሕመም የሚፈወስ ፡ በጾም «በጸሎት» ነውና።
እንግዲህ ከአባቴ ይኼን ያዝኩላቸው
በቤተክርስቲያናችን ጾም የሌለው ለበዓለ ሃምሳ ብቻ ነው። ይልቅ ሰውን በማንጠቅምበት አልፎም ለማያድንም ምክንያት ጾመ ጽጌን አንንቀፋት።
"ወዝኬ ዘሰ ዘይሜህር ዘእንበለ ይኅሥሡ እምኔሁ ወዘእንበለ ምክንያተ ድልወት ለበቁዔተ ሰማእያን ውእቱኬ አብድ ወአኮ ጠቢብ ➺ ይኸውም አስተምረን ሳይሉት እና ሰሚዎቹን የሚጠቅምበት ምክንያት ሳይኖረው ላስተምራችሁ የሚል ሰው አላዋቂ ነው እንጂ አዋቂ አይባልም፡፡ ሰነፍ እንጂ ጠቢብ አይባልም" (ፊልክስዩስ)
እንኳን ለጽጌ ጾም አደረሰን አደረሳችሁ። በማኅሌት የታጀበውን ተወዳጁን ዘመነ ጽጌ ወርኃ ጾም ተደርቦበት የበረከት ዋጋና በጎ ምላሽ የሚያሰጠን ያድርግልን።
ቴዎድሮስ በለጠ ፳፮/፩/፳፻፲፬
@Ethiopian_Orthodox
1.3K views06:59