2022-12-02 11:21:24
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰሩ እናቶች የህፃናት ማቆያ ስራ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገለፁ
===========
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ:- ህዳር 23/2015 ዓ.ም ( ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የስራ ክፍሎች የሚሰሩ ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ስራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለማከናወን ያመች ዘንድ ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም የህፃናት ማቆያ በማዘጋጀት ከ6 ወር አስከ 3 ዓመት ዕድሜ የሚሆናቸው ህፃናት ተቀብሎ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በማዕከሉ ላይ ተግኝተው ሀሳባቸውን የሰጡት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ወጣቶች እና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላም መክብብ እንደገለጹት ሴት ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ተረጋግተው ስራቸውን እንዲሰሩ ለማድረግና በስራቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ ልጆቻቸውንም ማጥባትና መጎብኘት በሚፈልጉበት ሰዓት በቅርበት እንዲጎበኙ ለማድረግ በማሰብ 4 የሞግዚት እና 3 የጽዳት ባለሙያዎችን በድምሩ 7 ሰዎችን በመቅጠር 25 ለሚሆኑ ህፃናት አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በማዕከሉ ከሴት ሰራተኞች በተጨማሪ ሚስቶቻቸው በስራ ምክንያት ሩቅ ቦታ ለሚኖሩባቸው አባቶችም ልጆቻቸውን በማቆያ ማዕከሉ በማስገባት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲያችን ከKG እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለማስተማርያ የሚሆን የማህበረስብ ት/ቤት በመገንባት ላይ ይገኛል። በቅርብም ወራትም ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ከዚህ በበለጠ የህፃናትንና የባለሙያዎችን ቁጥር በመጨመር አገልግሎቱ እንደሚሰጥ አክለው ገልፀዋል። በመጨረሻም በዚህ ማዕከል ውስጥ ህፃናትን ልክ እንደወላጅ ሆነው እየተንከባከቡ ንፅህናቸውንና ደህንነታቸውን ለሚጠብቁ ባለሙያዎች ምስጋና ይድረሳቸው በማለት ሀሳባቸውን አጠናቀዋል፡፡
በህፃናት ማቆያ ማዕከሉ ውስጥ በሞግዚት ባለሙያነት ስታገለግል ያገኘናት እንይሽ ሽቴ እንዳለችው የዚህ ማዕከል መከፈቱ የስራ እድል ፈጥሮልናል፤ ህይወታችንን እየመራንበት እንገኛለን ፤ በስራችንም በጣም ደስተኛ ነን ፤ ከዚህ በተጨማሪ ከህፃናት ጋር መዋል ልዩ ስሜትና ደስታን ይፈጥራል፤ እኛ ባንወልዳቸውም እንኳ እንደወላጅ በመሆን ለህፃናት ልዩ እንክብካቤ በማድረግ ለወላጆቻቸው እናስረክባለን። ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲ ለባለሙያዎች የንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ግብዓቶችን እንዲሟሉ ጠይቃለች፡፡
በሌላ በኩል በህፃናት ማቆያ ልጆቻቸውን ሲያስገቡ ያገኘናቸው ወ/ሮ ይታይሽ መኩሪያውና የዝና ነጋሽ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለሰራተኞቹ ልጆች ይህን የህፃናት ማቆያ በማዘጋጀት ልጆቻችን በማቆያው እንዲውሉ በማድረጉ ከልብ እንደሚያመሰግኑና ከተለያየ ወጭም እንደታደጋቸው ስራቸውንም በጥሩ ስነ ልቦና እንዲሰሩ እንዳገዛቸው ገልፀዋል። "ልጆቻቸውንም ማየት ስንፈልግ በቅርበት እንድንከታተል አድርጎናል ካሉ በኋላ በመጨረሻም በማዕከሉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ልጆቻችንን በጥሩ ሁኔታ እንደራሳቸው ልጆች እየተንከባከቡ በመያዛቸው ከልብ እናመሰግናለን፤ ይህ የህፃናት ማቆያ ከዚህ የበለጠ እንዲያድግና አገልግሎቱን በስፋት እንዲሰጥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
2.3K views08:21