2022-08-09 19:10:05
@Bemnet_Library
የፍቅር ምትሃታዊ ጨረር መንፈሴን በመዳበስ ዐይኖቼን የከፈተልኝ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜዬ ነበር፡፡ መንፈሴን በውበቷ ያነቃቃችውና ወደ ፍቅር አፀድ የመራችኝ ሴት ደግሞ ሰልማ ካራሚ ነበረች። ውበትን አመልክ ዘንድ ራሷን ምሳሌ በማድረግ የፍቅርን ሀሁ ያስተማረችኝ ሰልማ ካራሚ ናት፡፡ የእውነተኛ ሕይወትን ግጥም ለመጀመሪያ ጊዜ ያዜመችልኝም እርሷ ነበረች፡፡
ማንም ወንድ የመጀመሪያ ፍቅሩን አይረሳም። የትውስታው ሕመም ልቡን እየጎዳው እንኳን የመጀመሪያ ፍቅሩን መላልሶ ያስታውሳል፡፡ የእያንዳንዱን ወንድ ብቸኝነት ወደሙሉ ሐሴት የምትቀይር "ሰልማ" በሁሉም ሕይወት ውስጥ አለች፡፡ የወጣቱን ቀዝቃዛ ልብ በፍቅሯ በማሞቅ የደነዘዘ ምሽቱን በሙዚቃ የምትቀይር 'ሰልማ' በሁሉም ሕይወት ውስጥ አንዴ ትከሰታለች።
የቅዱስ መጽሐፍትን ምሥጢር ለመረዳት አእምሮዬ በተወጣጠረበት ወቅት ነበር የሰልማ ውብ ከንፈር ለጆሮዬ ፍቅርን ሹክ ያሉት፡፡ ሕይወቴ ባዶ ነበር-ልክ አዳም በገነት እንደነበረው! ከዚያም ሰልማን እንደ ብርሃን ማማ ከርቀት አየኋት፡፡ እርሷ የልቤ ሄዋን ናት፡፡ ልቤን በአስደናቂ መረዳት ሞልታ የሕይወትን ትርጉም አሳየችኝ፡፡ የመጀመሪያዋ ሄዋን በራሷ ፍላጎት አዳምን ከገነት አስወጥታዋለች። የእኔዋ ሰልማ ግን በጣፋጭ ፍቅሯ አማካኝነት በራሴ ፍላጎት ወደገነት እንድገባ አደረገችኝ፡፡ ሆኖም የመጀመሪያውን ሰው የገጠመው እኔንም ገጥሞኛል፡፡ አዳምን ከገነት ያስወጣው እሳት የሆነ ቃል እኔንም ሳላጠፋና የተከለከለውን ፍሬ ሳልቀምስ ከገነት አባረረኝ፡፡
ዛሬ ከዓመታት በኋላ የቀረኝ ነገር ቢኖር የዚያ ውብ ሕይወት የሚያሳምም ትውስታ ብቻ ነው፡፡ ልቤን በሃዘን ፤ ዐይኖቼን በእንባ እየሞላ ያሰቃየኛል፡፡ የእኔዋ ውድ ሰልማ ሞታለች፡፡ የተሰበረ ልቤና በጥድ ዛፍ የተከበበ መቃብሯ ብቸኛዎቹ መታወሻዎቿ ሆነዋል፡፡ የሰልማ ምስክር ሆነው የቀሩትም ባዶው ልቤና መቃብሯ ናቸው፡፡
መቃብሯን የሚጠብቀው አስፈሪ ፀጥታ የሳጥኗን ውስጥ ምሥጢር ለፈጣሪ እንኳን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ በሥራቸው አካሏን መጠው የሚመገቡት የዛፍ ቅርንጫፎችም ምሥጢሯን አይተነፍሱትም፡፡ የልቤ ሲቃ ብቻ ነው ፍቅር ፣ ውበትና ሞት የሠሩትን ድራማ የሚገልፀው፡፡ በቤሩት የምትኖሩ ወጣት ጓደኞቼ ሆይ - በመቃብሩ ሥፍራ ስታልፉ የእግራችሁ ዳና እንዳይረብሻት በዝግታ ተራመዱ። የሰልማ መቃብር ጋር ስትደርሱም አቅፎ ላስተኛት መሬት እንዲህ በሉልኝ፦
"በባህር ማዶ የፍቅር እሥረኛ የሆነው የጂብራን ተስፋዎች በሙሉ እዚህ አርፈዋል፡፡ እዚች ቦታ ላይ ደስታውን አጣ ፤ እንባውን አደረቀ ፤ ፈገግታውንም ረሳው፡፡" የጂብራን ሃዘን ከመቃብሩ ጎን ካሉት ዛፎች ጋር ያድጋል፡፡ መንፈሱም ከፍ ብሎ ከዛፎቹ በላይ የሰልማን መሞት በሃዘን ያስታውሳል፡፡ ትናንትና ውበትን የዘፈኑት የሰልማ ከንፈር ዛሬ ከምድር በታች የተሸሸጉ ምሥጢራት ሆነዋል፡፡
"ኦ - ወዳጆቼ! ባፈቀራችኋቸው ሰዎች ስም እለምናችኋለሁ፡፡ በዚህ ስታልፉ ለተረሳችው ፍቅሬ አበባ አስቀምጡላት፡፡ አንድ አበባ ማኖር በፅጌሬዳ ላይ እንደምትፈጠር የማለዳ ጤዛ የንጋት አብሳሪ ነውና።"
#ካህሊል_ጂብራን
THE BROKEN WINGS
ቢኒያም አበራ እንዳጋራው
ማጋራት መተሳሰብ ነው!
@Bemnet_Library
3.7K viewsBemni, 16:10