2022-12-07 23:06:39
የመጽሐፍ ርዕሰ = በእንተ ሚስጢረ ሥጋዌሁ ለእግዚእነ {The sacrament of the incarnation of our lord}
ጸሐፊ= ቅዱስ አምብሮስ ዘሚላን
የተጻፈበት ጊዜ = ፫፻፹፩{፫፹፪}{381{382}} ዓ/ም
ይዘት = ነገረ ክርስቶስ
#መግቢያ
፧
፩.፩ የመጽሐፉ ስያሜ
የመጽሐፉ ጸሐፊ ቅዱስ አምብሮስ "Mystery of our lord's incarnation"{De incarnationis dominicae sacramento} ብሎ ሲጠራው [፩]
የቅዱሱን ታሪክ የጻፈው ጳውሊኖስ እና ቄሳዴሮስ "The incarnation of our lord" ሲሉት ሌሎች ደግሞ "Against apollinarsts" {መድፍነ አቡሊናርዮሳውያን} ይሉታል [፪] እንዲህም ያሉት መጽሐፉ ለአቡሊናርዮስን [፫] ምንፍቅና ምላሽ ስለሰጠ ይሆናል።
፧
፩.፪ ምክንያተ ጽሑፍ
መጽሐፉ ከOn the faith {De fide} On the Holyspirit {De Spiritusancto} በኋላ ሦሥተኛ የዶግማ ሥራው ነው {ስለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ያብራራበት} መጽሐፍ ነው።
፧
"ነገርግን ምንላርግ? በየቀኑ አዳዲስ ጥያቄዎች ይመጣሉ... ለተቃውሞ ገደብ {ልክ} ከሌለው ለምላሽስ እንዴት ገደብ {ልክ} ሊኖረው ይችላል?" [፬] በማለት ሊቁ ይህን መጽሐፍ እንዲያዘጋጅ ያደረገው አምስት ጥራዝ ባለው በOn the faith{ De fide}መጽሐፍ ምላሽ የሰጣቸው የመድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ፍፁም አምላክነት ለሚክዱት ለአርዮስ ተከታዮች የማያባራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ምእመናነ ክርስቶስን በእምነት ለማፅናት ነው።
፧
አንድም ታሪኩን ያዘጋጀው ጳውሊኖስ ስለ መጾሐፉ መዘጋጀት ምክንያት የንጉሥ ግራትያን ዘቦች {እልፍኝ ከልካይ} የሆኑ ሁለት አርዮሳውያን ስለ ጌታችን ሥጋዌ ጥያቅ ጠየቁ በበነገታውም በቤተክርስቲያን ተገኝተው ቅዱሱ ምላሽ እንዲሰጣቸው እና በትምህርቱ ለመሳተፍ ቃል ገብተው ስለ ነበር ለእነርሱ ምላሽ ለመስጠት መጽሐፉ እንደተጻፈ ይናገራል።
ነገርግን ሊቁ ቃሉን አክብሮ በሚስጢረ ሥጋዌ ላይ ትምህርት ሰጥቶ በመጽሐፍ መልክ ቢጻፍም [፭] አርዮሳውያኑ ግን ቃላቸውን ሽረው በትምህርቱም ሆነ የጠየቁትን ጥያቄ ምላሽ ለመስማት አልተገኙም[፮] ነበር በዘመኑ አርዮሳውያን በእነ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ በእርሱም ላይ መከራዎችን አድርሰውበታል።
የተለያዩ የስም ማጥፋት ወሬዎችንም በእርሱ ላይ ይነዙ ነበር።
፧
፩.፫ አጠቃላይ የመጽሐፉ ባህርይ
መጽሐፉ የሚያጠነጥነው በነገረ ክርሰቶስ ለተነሱ ምንፍቅናዎች ምላሽ መስጠት ላይ ነው።
መልስ ከተሰጣቸው የምንፍቅና አይነቶች ውስጥ አርዮሳዊነት እና አቡሊናርዮሳዊነት ሰፊውን ቦታ ሲወስዱ መንፈቀ{ተረፈ} አርዮሳዊነት[፯] አውጣኪያዊነት እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል።
፧
በቅዱሱ ዘመን አርዮሳዊነት እና መንፈቀ{ተረፈ} አርዮሳዊነት ያየለበት እና ቤተክርስቲያንን የፈተነበት ስለነበር አብዛኞቹ የቅዱሱ የዶግማ ጽሑፎቹ ለእነርሱ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው።
በመጽሐፉ ውስጥ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግረ መንገዳቸውን አብረው ተተርጉመዋል።
የቅዱሱ የአመላለስ ዘዴም በመጀመሪያ የመናፍቃኑን ሀሳብ ካነሳ በኋላ ምላሹን ከመጽሐፍ ቅዱስ በማምጣት በአመክንዮ አስደግፎ ማስቀመጥ ነው።
፧
ሊቁ የግሪክ ቋንቋ የተማረ ላቲናዊ ቢሆንም በዚህ መጽሐፍ በግሪክ ቃላት ያሉ የነገረ መለኮት መግለጫ ቃላትን {Theological terminologies} ያብራራል ይተነትናል።
፧
፪.የመጽሐፉ የውስጥ ክፍል በጥቂቱ ሲተነተን
መጽሐፉ አስር ምዕራፍ ያለው ሲሆን የእያንዳንዱን ምዕራፍ ሀሳብ በስሱ ለማየት እንሞክራለን።
፧
ምዕራፍ ፩
ይህን የመጽሐፉን ክፍል መግቢያ {introduction} ማለት ይቻላል።
በዚህ ክፍል ቅዱሱ የአቤል እና የቃየንን መሥዋዕት መሠዋት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኅብረ አምሳላዊ ትርጓሜን ይተረጉማል።
የቃየንንም መሥዋዕት ከመናፍቃን ጋር ያገናኘዋል የቃየን መሥዋዕት እግዚአብሔርን አላስደሰተውምና ነው ይህንንም ሊቁ እንዲህ ያብራራዋል "ቃየን መሥዋዕቱ እግዚአብሔርን እንዳላስደሰተ አወቀ እግዚአብሔርም “መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች — ዘፍጥረት 4፥7 አለው ግን የቱ ጋር ነው ወንጀሉ? ጥፋቱ የቱ ነው? በመሥዋዕቱ አይደለም ነገርግን የመሥዋዕቱ መባእ የቀረበበት የእዕምሮ ሁናቴ ነው።" ይላል [፰]
፧
ማለትም እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ያልተቀበለለት መሥዋዕቱን ንቆት አልነበረም ነገርግን መሥዋዕቱ የቀረበበትን መንገድ ነው ማለቱ ነው።
የቃየን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ሞገሥን እንዳላገኘ እንዳላስደሰተ ከቤተክርስቲያን ኅብረት የተለዩ የመናፍቃንም ሃይማኖት እግዚአብሔርን አያስደስተውምና።
የመናፍቃን አገልግሎት እምነት በቤተክርስቲያን ውስጥ አይደለምና ነው።
፧
ምዕራፍ ፪
በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ለቃየን የተናገረው የግሳጼ ቃል ማለትም {“መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች
— ዘፍጥረት 4፥7} አስተምህሮአቸውን ከተለያዩ የፍልስፍና ትውፊቶች ለቃረሙት በግብር ቃየንን ለመሰሉት ለአውናምዮሳውያን {መንፈቀ{ተረፈ}አርዮሳውያን} ለሰባልዮሳውያን፣ለጸረ-መንፈስቅዱስ{Pneumatomachi {ለመቅደንዮሳውያን}}፣የክርስቶስን አካል ቤተክርስቲያንን ለከፈሉ ለብናጥስ{ኖቫትያን} እና ዶናተስ [፱] እንዲሁም ለአቡሊናርዮሳውያን እና መሰል መናፍቃን እንደሚገባ ይናገራል።
፧
መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ፫፡፬{3፡4}ን ዋቢ በማድረግም እንዲህ ይላል "ስለዚህ ማንም ከዘላለማዊ ንጉሥ መኖሪያ ከእናት ቤተክርስቲያን እቅፍ እንዳይለየን እንጠንቀቅ ልክ በመኃልየ መሓልይ እንዳለችው ነፍስ"[፲]
፧
ምዕራፍ ፫
በዚህ ክፍል ላይ የዮሐንስ ወንጌል ፩፡፩{1፡1}ን የሚያብራራበት {የሚተረጉምበት} ክፍል ነው።
ወንጌላዊው እንደ አሳ አጥማጅነት ሳይሆን እንደ ሰው አጥማጅነት {ሐዋርያት አሳ ማጥመድ ትተው ሰው ያጠምዱ{ነፍሳትን ወደ ክርስቶስ ያቀርቡ ዘንድ}በጌታ እንደተሾሙ ልብ ይላል} በመንፈስቅዱስ ተቃኝቶ መናገሩን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መናፍቃን የልብ ጆሯቸውን ዘግተው እንደሚሰሙት እና ተጨማሪ ጉዳዮችን ይዘረዝራል።
878 views20:06