Get Mystery Box with random crypto!

...ክፍል ፪                           ምዕራፍ ፬ በዚህ ምዕራፍ ሊቁ ቀደሞ | የጥያቄዎቻችሁ መልስ

...ክፍል ፪

                          ምዕራፍ ፬

በዚህ ምዕራፍ ሊቁ ቀደሞ በምዕራፍ ሦሥት ላይ የተረጎመውን የዮሐንስ ወንጌል ፩፡፩{1፡1}ን ቃል ከመለኮት ባህርይ አውጥተን መተርጎም እንደሌለብን ያስረዳል የእርሱን {የክርስቶስን} መለኮታዊ ማንነት እና ሰዋዊ ማንነት በሚገባ ለይተን ካላወቅን¹ ለቃየል የተነገረው ቃል {ዘፍጥረት ፬፡፯{4፡7}ሊቁ ይህን ቃል ከመናፍቃን ጋር አገናኝቶ ይተረጉመዋል ክፍል ፩ን ይመልከቱ} ለእኛም አነደሚገባ ይናገራል።
በመቀጠልም ክርስቶስ የሰውን ሥጋ አልነሣም የሚለውን የማኒን አስተምህሮ ይቃወማል ክርስቲያኖችም በእርሱ {በማኒ} አስተምህሮ ቢያምኑ "የቤተክርስቲያን ልጆች መሆን እንዳልጀመሩ"² አበክሮ ይናገራል።

አስከትሎም በማቴዎስ ወንጌል {፲፮፡፲፭{16፡15}} ላይ ሐተታ {ትርጓሜ} ይሰጣል።
በሐተታው ያነሳቸውን ነጥቦች በሁለት ማየት ይቻላል

፩. በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ጌታችን ኢየሱስ "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" "ብሎ ሐዋርያትን ሲጠይቃቸው ሐዋርያትም አንዳንዶቹ ኤርምያስ አንዳንዶቹ ኤልያስ አንዳንዶቹ ከነብያት አንዱ ነህ ይሉሀል ብለው መለሱለት እርሱ ግን ለአንዱም መልስ እውቅና አልሰጠም ትክክል ነው አላለም “እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።” ባላቸው ጊዜግን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽ ሰጠ ምክንያቱም እርሱን የሚመለከት እና የእርሱን ማንነት የሚገልጽ ነበርና ለእርሱ ምላሽ ብቻ እውቅና መስጠቱን ከአምላክነቱ አንፃር ማለትም አምላክ መሆኑን የሚገልጽ ነው ብሎ ተርጉሞታል {መጽሐፉ ለአርዮሳውያንም ምላሽ እንደሚሰጥ ልብ ይሏል} እንዲያውም አርዮሳውያንን እንዲህ ብሎ ይጠይቃቸዋል "አርዮሳውያን ሆይ ዮሐንስ እና ጴጥሮስ ያላመኑ ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁን?"³ በማለት ይጠይቃቸዋል ምክንያቱም ይህ ቃል የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት ወልደ እግዚአብሔር መሆኑ የተገለጸበት ስለሆነ አርዮሳውያን ደግሞ ከዚህ ቃል አፈንግጠው በራሳቸው ሀሳብ ፍልስፍና ወድቀው ከቤተክርስቲያን አካልነት ተነጥለዋልና!
ቃሉን ሲተረጉምም ከዚህ አንፃር ይተረጉመዋል።

፪. የጴጥሮስ ምላሽ "በመጀመሪያ ያለህ" "ፍጡር የሆንኽ" የሚል ሳይሆን "የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ"  የሚል ነበር ይህ ቃል የውሸተኛዋ ቤተክርስቲያን የአርዮሳውያን ኅብረት መሠረት አይደለም ነገርግን ክርሰቶስ በደሙ የመሠረታት የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መሠረቷ ነው በዚህም አርዮሳውያን የእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ልጆች አለመሆናቸውን አሳወቁን ምክንያቱም በዚህ ቃል መሠረትነት አልተማሩምና ነው
ሊቁ በዚህ አውድ ማሳየት የፈለገው ጉዳይ ይህ ቃል መሠረታችን መሆኑን ነው {በዚያውም ለአርዮሳውያን መሠረት አለመሆኑንም ማሠየት አንዱ አውዱ ነው እንዲህ ከሆነ ደግሞ አርዮሳውያን የእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን አካላት አለመሆናቸውን ያርጋግጣልና!}ይህ ቃል እንዴት መሠረታችን እንደሆነ ሲያብራራም እንዲህ ይላል "መሠረት ተብሎ ተጠራ ነገርግን የሁላችንም {የቤተክርስቲያን} መሠረት ነው ምክንያቱም እርሱ ራሱን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መጠበቅ ያውቃልና ነው።
ክርስቶስም ከእርሱ ጋር ተስማማ አብም ገለጠለት።"⁴

                          ምዕራፍ ፭
"መሠረተ ቤተክርስቲያን የተባለው እምነቱን እንጂ ሥጋውን አይደለም የጴጥሮስን ሥጋ አልነበረም ነገርግን እምነቱን የገሀነም ደጆች አይችሉትም {ሊቆጣጠሩት አይችሉም} ነገርግን የእርሱ ምስክርነት ገሀነምን ይቆጣጠራል።
ቤተክርስቲያንም ልክ እንደ መልካም መርከብ በብዙ ማዕበል {ምንፍቅና} ትመታለች የቤተክርስቲያን መሠረት ሁሉንም ምንፍቅናዎች ተቃውሞ ያሸንፋልና ይህ ምስክርነት በምንፍቅና አይሸበርም!"⁵

እንዲህ በማለት ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበትን የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ያጸናል።
እንዲሁም በዚህ የመጽሐፉ ክፍል ወልደ እግዚአብሔርም ወልደ ማርያምም እርሱ እንደሆነ፤ምስጢረ ሥጋዌ ሁለቱን አካላት {ሥጋ እና መለኮትን}አንድ እንዳደረገ፤ሁለቱ ማንነቶች አንድ {የእርሱ ገንዘቦች}፤እንዲሁም በዚህ ሁለት ማንነቶች ሳይሆን አንድ ክርስቶስ ተብሎ እንደሚጠራ ያብራራል።

በዚህም ይህ የመጽሐፉን ክፍል ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምር ቃለ ውግዘት ጋር አዋህደን ማየት እንችላለን ሊቁ እንዲህ ይላል "ዓለም ሳይፈጠር የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ሌላ ነው፤ከማርያም የተወለደው ሌላ የሚል ዓለም ሳይፈጠር የነበረው እርሱ ራሱ ቀዳማዊ ደኃራዊውም ያው አንዱ ብቻ እንደሆነ እንደተጻፈ በኋላ ዘመንም ከማርያም ሥጋን የነሣው እርሱ ራሱ እንደሆነ የማያምን የተወገዘ ይሁን"⁶

አክሎም የአንዱን ሥግው ቃል {The one incarnated word} ባህርይ ሲያብራራም የታመመው ያልታመመውም ያው እርሱ ነው፤የሞተውም ያልሞተውም ያው እርሱ ነው {መለኮት በባህርይው ሞት አይስማማውምና ለሥግው ቃል ሞት ሲነግርለት በሥጋው ነው የሚባልለት}፤የተቀበረውም ያልተቀበረውም ያው እርሱ ነው፤ከሞት የተነሣው ያልተነሣውም {ለመለኮት መነሣት መውጣት መውረድ የለበትምና!} ያው እርሱ ነው አንዱን ክርስቶስ ሳንነጣጥል መረዳት እንዳለብን እና እነዚህ ሁሉ ግብራት የአንዱ ሥግው ቃል ግብራት እንደሆኑ ያስረዳል።

በመቀጠልም አንዱ በመዝሙር {፳፩፡፩{21፡1}} ላይ ያለውን ቃል ማለትም “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።”
የሚለውን ቃል በመስቀል ላይ ሳለ ከምን አንፃር እንደተናገረ ያብራራል እንዲህም ይላል "በሥጋ ብቸኛ {Forsake} ይሆናል በመለኮቱ ግን ሊጎዳም ሆነ ብቸኛ ሊሆን አልቻለም።"⁶

የመለኮት እና የሥጋ ተዋሕዶ ያለ መጠፋፋት፣ያለ መለወጥ፣ያለ መቀላቀል እና ያለ መለየት የተደረገ የተደረገ ከመሆኑ ጋር አገናዝቦ ማየት ይቻላል።
"ኢየሱስ ክርሰቶስ አንድና ተመሳሳይ ነው እንላለን ቢሆንም የባህርያቱን {የሥጋና የመለኮትን} ልዩነት እርስ በእርስ አለመቀላቀል {አለመምታታት} እውቅና እንሰጣለን።"⁷
እንዲል ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ቅዱስ አምብሮስም ይህን ቅርጽ እና መንገድ ለማብራራት ተጠቅሞቀታል።
ይህንም ክፍል እንዲህ በማለት ያጠቃልላል "ሥጋው በባህርይው ታሟል እንዲሁም የመለኮት ባህርይ በሕማሙ ባህርይው አልተለወጠም ትንሣኤያችን በእውነት ነው የክርስቶስ ሕማምም በእውነት ይሰበካል።"⁸

                             ምዕራፍ ፮
በዚህ ምዕራፍ ሊቁ የክርስቶስ መገለጥ ምትሐት ነው ያሉ {በእውነት ሰው አልሆነም እውነተኛ ሥጋን ከቅድስት ድንግል ማርያም አልነሣም የሚሉ} ቫለንቲኑስን እና ማኒን እንዲህ በማለት ይቃወማቸዋል "ብዙዎች እንደሚሉት ክርስቶስ በምትሐት አልታመመም ምክንያቱም በባህር ላይ በምትሐት አልተራመደምና!"⁹
ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም ብል መከፋፈል መለያየት እንደማይገባ ንስጥሮሳዊ የሆነውን ትምህርት በድጋሚ ይቃወማል ያስተምራልም ማመን የሚገባን በአንዱ በሥግው ቃል በኢየሱስ ክርሰቶስ እንጂ በሁለት ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳይደለ በአጽንኦት ያስረዳል።