2022-08-25 09:41:43
የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት በምሥጢር በአካል በመገናኘት ተነጋግረው እንደነበር ተገለጸ
አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ነሐሴ 19፣ 2014 ― የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት በምሥጢር በአካል ተገናኝተው እንደነበር የገለጹት ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ ሊቀመንበሩ ይህን የገለጹት ለተለያዩ አካላት በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡
ዶክተር ደብረጽዮን ማክሰኞ ነሐሴ 17፣ 2014 ለ12 አካላት በጻፉት ደብዳቤ ለሁለት ጊዜያት በተደረገው የምሥጢር ግንኙነት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተኩስ ለማቆም እና በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመቀጠል መግባባት ላይ ደርሰው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የዶክተር ደብረጽዮን ደብዳቤ የፌዴራል መንግሥት እና የሚመሩት ሕወሓት ባለሥልጣናት የት እና መቼ እንደተገናኙ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ከባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር አንስቶ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ሁለቱ አካላት ያለፉትን አምስት ወራት ጦርነቱን ጋብ አድርገው ለመደራደር ዝግጁ እንደሆኑ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ባለሥልጣኖቻቸው በተለያዩ አገራት መገናኘታቸውን የሚያመለክቱ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች ቢወጡም የፌዴራል መንግሥቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል አስተባብሏል፡፡
ሁለቱ አካላት ጦርነቱን ጋብ ባደረጉበት በተለይ ባለፉት ሳምንታት የሰላም ንግግሩ ፍሬ እያሳየ መሆኑን ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን በአሸማጋይነት የመደበው የአፍሪካ ኅብረት ገልጾ ነበር፡፡ ሌላኛዋ አደራዳሪ አሜሪካም በባለስልጣናት በኩል ድርድሩ ከአስር ቀናት በፊት ከተካሄደው የኬንያ ምርጫ በኋላ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንዳላት ገልጻ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ ባለበት ትላንት ረቡዕ ነሐሴ 18፣ 2014 ንጋት ላይ ዳግም ጦርነቱ ተጀምሯል፡፡ ጦርነቱን ማን ጀመረው በሚለው ላይ መረጃውን ቀድሞ ያወጣው ሕወሓት፤ የፌዴራል መንግሥቱ ኃይሎች ጥቃት ከፍተውብኛል ቢልም፤ እኩለ ቀን አካባቢ መግለጫ ያወጣው መንግሥት ሕወሓት ለተኩስ ቀዳሚ ነው ሲል ወንጅሏል፡፡
ከጦርነቱ ዳግም መጀመር በኋላ ዋንኛው አደራዳሪ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአሜሪካ እና ብሪታንያ ባለሥልጣናት ውጊያው ቆሞ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ትላንት ምሽት ባወጡት መግለጫ፤ በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል ዳግም ውጊያ መቀስቀሱ በጥልቅ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሁለቱን ኃይሎች እንዲያሸማግሉ የሾሙት ሊቀመንበሩ፤ ተኩስ ቆሞ ሁለቱ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ንግግር እንዲጀምሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እንዲሁ በኢትዮጵያ ዳግም ውጊያ በመጀመሩ መደናገጣቸውን እና ማዘናቸውን ገልጸዋል። ውጊያ ቆሞ ሁለቱ አካላት የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ ጥሪ ያቀረቡት ጉቴሬዝ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን በበቂ ተሰቃይተዋል›› ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ማገርሸት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል መግከጫ ያወጣችው አሜሪካ ደግሞ እንደ አዲስ ያገረሸው ግጭት እና በአዲስ አበባ እና በመቐለ መካከል የሚታየው የቃላት መወራወር፤ በአገሪቱ አካታች የፖለቲካ ሂደት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያዘገይ አስታውቃለች፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሚኒስትሩ አንቶንዮ ብሊንክን የሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች ወደ ውጊያ መመለስ፤ የኢትዮጵያን ዜጎች ለመጠነ ሰፊ ስቃይ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ እና ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ፈተና እንደሚዳርግ አስጠንቅቀዋል።
1.0K views06:41