2022-08-27 13:20:43
የአማራ ክልል የጫት ተጠቃሚነትን ለመቀነስ የቀረጥ ጭማሪ አደረገ
አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ነሐሴ 21፣ 2014 ― የአማራ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የጫት ተጠቃሚነትን ለመቀነስ የቀረጥ ጭማሪ አድርጓል፡፡ የክልሉ መንግሥት አዲስ ባደረገው የቀረጥ ጭማሪ መሠረት ነጋዴዎች በአንድ ኪሎ ግራም ጫት 30 ብር እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡
ከነሐሴ 12፣ 2014 ጀምሮ መተግበር የጀመረው አዲሱ ታክስ፤ በክልሉ እየጨመረ የመጣውን ይህን አነቃቂ ቅጠል ተጠቃሚነት ለመቀነስ የተደረገ መሆኑን መመሪያው አመልክቷል፡፡ አዲሱ መመሪያ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ለሚደረገው የጫት ዝውውር የቀረጥ ክፍያ የሚጥል ነው፡፡
አነቃቂ የሆነው የጫት ቅጠል የጤናና ማኅበራዊ ቀውሶች በማስከተል፤ የዜጎች ምርታማነት እንደሚቀንስ እና ቤተሰባዊ መስተጋብርን እንደሚያዛባ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ይናገራሉ፡፡
የአማራ ክልል አስተዳደር መቀመጫ ባህር ዳር ከተማ በገቢዎች ጽሕፈት ቤት በኩል 2010 ሚያዝያ ወር ላይ በተመሳሳይ በአንድ ኪሎ ግራም 30 በመቶ ወይም 30 ብር ቀረጥ በጫት ላይ ጥሎ ነበር፡፡
በአንጻሩ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ገበሬዎች አገሪቱ በስፋት ትታወቅ የነበረውን የቡና መሬታቸውን ወደ ጫት ማሳነት በመቀየር ጫት ማብቀልን መምረጣቸው ይነገራል፡፡
እንደ መረጃዎች ከሆነ ባለፈው የምርት ጊዜ በአማራ ክልል በዘርፉ የተሰማሩ ከ235 ሺሕ በላይ ገበሬዎች በ10 ሺሕ 886 ሔክታር መሬት ላይ ከ68 ሺሕ ኩንታል በላይ ጫት አብቅለዋል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ፤ የጫት ተጠቃሚነት በጨመረበት የአማራ ክልል ገበሬዎች የጫት ምርታቸውን በሌሎች ሰብሎች እንዲተኩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል፡፡
ጫት በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ቀዳሚ አምስት ምርቶች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 392 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች በጫት ምርት የኦሮሚያ ክልል ቀዳሚን ደረጃ ሲይዝ፤ በክልሉ የሚገኙ ገበሬዎች 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ጫት ያበቅላሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት ከአንድ ኪሎ ጫት ሦስት ብር ይሰበስባል፡፡
880 views10:20