Get Mystery Box with random crypto!

✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

የቴሌግራም ቻናል አርማ abweldmenfeskidus1amlak — ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️
የቴሌግራም ቻናል አርማ abweldmenfeskidus1amlak — ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️
የሰርጥ አድራሻ: @abweldmenfeskidus1amlak
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 192
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ድህረ መዋያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና አስተምህሮ የሚተላለፍበት፤ ቅዱሳን ሰማዕታት የሚታወሱበት (የሚዘከሩበት)፤ የተዋሕዶ ልጆች የምንማማርበት ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መልካም ፍቃዱ ሆኖ÷ እነሆ በእናታችን በቅድስተ ቅዱሳን በንፅህተ ንፁሃን በቅድስት ድንግል ማርያም ዕለት በ ፳፩/፲፩/፳፻፲፪ ተከፈተ::
የጻድቃን ሰማዕታት : የቅዱሳን በረከት ይደርብን፤ አሜን!

Ratings & Reviews

3.00

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-07-16 21:35:35 ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን! †††

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፲ (10)

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

" ቅዱስ ናትናኤል "

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር::

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ) አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::

ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር:: በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል::

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል::

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ: ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

" አባ ብስንዳ "

ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ አባ ብስንዳ ይታሠባል::
አባ ብስንዳ በዘመነ ጻድቃን ምድረ ግብጽ ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱን ከገድሉ ጽናት የተነሳ መላእክት በእጅጉ ይወዱት ነበር:: "እኔ ልሸከምህ - እኔ ልሸከምህ" እያሉ ይሻሙበት: በተራ በተራም ተሸክመውት ይውሉ ነበር:: እርሱም ለበርካታ ዓመታት ውኃ የሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይጸልይ ነበር::

እንደ እሳት በሚባላው በረዶ ውስጥ ገብቶ መጸለዩ የፈጣሪውን ሕማማት ለመሳተፍ እና ለኃጥአን ምሕረትን ይለምን ዘንድ ነው:: ሁሌም በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ተሠብስበው ይመጡና በብርሃን ሠረገላ ይሸከሙታል:: ከመሬትም ዘጠኝ ክንድ ከፍ ያደርጉት ነበር::
ከብዙ ዓመታት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሒዷል::

††† እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ከሐዋርያው እና ከጻድቁ አባ ብስንዳ በረከትም አይለየን:: አሜን!


ሐምሌ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ታላቁ አባ ብስንዳ ጻድቅ
3.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት

ወርኀዊ በዓላት

1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

ንባብ

"ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእሥራኤል ንጉሥ ነህ' አለው::" (ዮሐ. ፩፥፵፰-፶፩)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
10 views18:35
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-15 19:34:57 ✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፱ (9)

እንኩዋን ለጻድቅ አባ_ኅልያን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

" አባ ኅልያን ገዳማዊ "

ጻድቁ ተወልዶ ያደገው ዐይነ ፀሐይ በምትባል የቀድሞ የግብፅ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወላጆቹ ዲስጣና ካልሞና ይባላሉ:: እነርሱ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩና ገና በልጅነት ይህንኑ አጥብቀው አስተምረውታል:: ቅዱሱ #ኅልያን ጾምን: ጸሎትን ብቻ ያይደለ በሥጋዊ ሙያውም የተመሰገነ አንጥረኛ ነበር::

+በወዙ በላቡ ሠርቶ ያገኘው ሃብት ነበረው:: በተለይ ወርቅና ብር እየሠራ ይተዳደር: ከገቢውም ነዳያንን ያስብ ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ሳለ አንድ ቀን ፈተና መጣበት:: አንዲት ዐረባዊት ሴት መጥታ የጀሮ ጌጥ (ጉትቻ) እንዲሠራላት ትጠይቀውና እርሱም ከወርቅ ይሠራላታል:: የጀሮ ጌጡን ከሰጣት በሁዋላ ግን "ዋጋውን አልሠጥህም" ትለዋለች::

+እርሱም "ምነው እህቴ! የደከምኩበትን ለምን አትከፍይኝም?" ሲላት ገላዋን አጋልጣ "ሴትነቴን ልስጥህ" ብላ ለዝሙት ጠየቀችው:: ድንግሉ ኅልያን ከአነጋገሯና ከድርጊቷ የተነሳ በጣም ደነገጠ:: ከፊቷ ላይ አማትቦ: ገስጿት ወደ ቤቱ ሔደ:: ሙሉ ሌሊት ሲያዝን አደረ:: ሊነጋጋ ሲል በልቡ ወሰነ:: ይሕችን ዓለም ሊተዋትም ቆረጠ::

+በወጣት ጉልበቱ ደክሞ ያፈራው ሃብቱ: ንብረቱ: ቤቱ: መሬቱ: ወርቁ: ብሩ አላሳሳውም:: ነዳያንን ሁሉ ወደ ቤቱ ጠርቶ ሙሉ ንብረቱን አካፈላቸው:: የተረፈችው የለበሳት ልብስ ብቻ ነበረችና ፈጽሞ ደስ እያለው ከተማውን ጥሎ ወደ በርሃ ተሰደደ:: ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና 3 #ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት::

+ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው: የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሰው: የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት:: እየመሩም ወስደው በግራና በቀኝ ውሃ ከሚፈስባት: ደኗ ለዐይን ደስ ከምታሰኝ ዱር አደረሱት:: አካባቢው እንኩዋን ሰው እንስሳትም አልነበሩበትም:: 3ቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ ፈጣሪ እንስገድ" አሉት::

+ሰግዶ ቀና ሲል ግን 3ቱም በአካባቢው አልነበሩም:: ተሠውረዋልና:: #አባ_ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ አለቀሰ::

+ተጋድሎውን ግን በጾምና በጸሎት: በስግደትም አጠነከረ:: ቅዱሱ የሚመገበው: የሚለብሰውም ቅጠል ነበር:: በእርሱ ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም:: ምክንያቱም ያቺ ዘንግ ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው::

+መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው: ጐዳናውንም ታሳጥርለት ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት ከሰው ተለይቶ ኖረ:: አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት:: ግን አልቻሉትም:: አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው: በሰው አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ:: ነገር ግን ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት አልቻሉም::

+#እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውሃ ጥም ሊያልቁ ሆነ:: ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው:: ባሕሩን ያለ ታንኩዋ እየረገጠ ደረሰላቸው:: ከዱር ፍሬ አብልቶ: ንጹሕ ውሃም አጠጥቶ ሸኛቸው::

+እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዛ በፊት የተሠወሩ 3 ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት:: በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ:: 3ቱ ቅዱሳንም ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት:: ዜና ሕይወቱንም ጽፈው አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ::

=>የቅዱሳን አምላክ ለእኛም የአባቶችን ረድኤት ይላክልን:: ከጻድቁም በረከትን ይክፈለን:: አሜን!


ሐምሌ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አባ ኅልያን ገዳማዊ
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (ዘሐምስቱ አሕጉር)
3.ቅዱስ ታውድሮስ ሰማዕት
4.ሰማዕታት ሉክዮስና ድግናንዮስ (በንስሃ ለክብር የበቁ የጦር አለቆች)

ወርሐዊ በዓላት

1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

ንባብ

" ጌታ ኢየሱስም "አትግደል: አታመንዝር: አትስረቅ: በሐሰት አትመስክር: አባትህንና እናትህን አክብር: ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ" አለው:: ጐበዙም "ይህንማ ሁሉ ከሕጻንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ:: ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?" አለው:: ጌታ ኢየሱስም "ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ:: መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ:: መጥተህም ተከተለኝ" አለው:: " (ማቴ. 19:18)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
16 views16:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-14 20:46:18 ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን! †††

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፰ (8)

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን ወከዋክብተ ገዳም አቡነ ኪሮስ: አባ ብሶይ እና አባ ሚሳኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

" አቡነ ኪሮስ ጻድቅ "

የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው: ክቡር ነው:: በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል::

#አቡነ_ኪሮስ የተወለዱት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው:: ተወልደው ባደጉባት ሃገር #ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል:: ወንድማቸው (ታላቁ #ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው: አሕጉር አቋርጠው ወደ ግብፅ ( #ገዳመ_አስቄጥስ) መጡ::

እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም:: ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ #ገብረ_ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ:: "የቅኖች ትውልድ ይባረካል" እንዳለ #ቅዱስ_ዳዊት:: አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው:: አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ #አቡነ_በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል::

ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ:: "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለ40 ዓመታት አልቅሰዋል:: በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል:: ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል:: አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል::

አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ:: ሱባዔ ገብተው: ፍጹም አልቅሰው: ከጌታም አማልደው: የዛን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም ባንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ::

ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት አልቅሰው: ሙታኑን አስነስተው: ንስሃ ሰጥተው: ገዳሙን የጻድቃን: ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል:: ጻድቁ #እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በስዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር:: እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር::

ከዚህ በሁዋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለ57 ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ:: ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና) በየቀኑ ይጐበኛቸው: ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ጌታ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን: ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ::

#ቅዱስ_ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው: በበገናው እየደረደረላቸው: ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ጌታችንም ታቅፎ: ስሞ ይዟቸው አረገ:: ሥጋቸውን #አባ_ባውማ ቀበሩት:: የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ: ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር:: እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም::


" የበርሃው ኮከብ አባ ብሶይ "

ታላቁ አባ ብሶይ (ቢሾይ):-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ
¤በመላእክት መሪነት የመነኑ
¤የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ባልንጀራ
¤የአባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር የነበሩ
¤በአጭር ጊዜ የብዙዎች አባት የሆኑ ሰው ናቸው::

††† እንቅልፍን የማያውቁ
¤በ40 ቀን ብቻ እህል የሚቀምሱ
¤የጌታችንን እግር በየቀኑ እያጠቡ የሚመገቡ
¤ፈጣሪያቸውን በጀርባቸው ያዘሉ (ነዳይ መስሎ አግኝተውት)
¤በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጉ
¤በርካታ ጻድቃንን የወለዱ ታላቅ የፍቅር ሰው ናቸው::

በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሰርተው: #ቤተ_ክርሰቲያንን በንጽሕናቸው አስደስተው: ሐምሌ 8 ቀን ዐርፈዋል:: ግብፅ ውስጥ የሚገኘው ገዳማቸው ዛሬም ቤተ አበው: ተአምራት የማይለዩትና ተወዳጅ ነው:: ቦታው #መካነ_ሱባዔ_ወመንክራት ነውና::


" አባ ሚሳኤል ነዳይ "

መቼም ያ ዘመን (4ኛውና 5ኛው ክ/ዘመን) እጅግ የተባረከ ነው:: ቅዱሳኑ በብዛት የባለጸጐችና የነገሥታት ልጆች ናቸው:: አባ ሚሳኤልም የኬልቄዶን ንጉሥ ልጅ ሳሉ መንነው በበርሃ ለ65 ዓመታት ተጋድለዋል:: በመጨረሻ ግን በደዌ ምክንያት ወደቁ:: ለ5 ዓመታት መነኮሳቱ ሲጠይቁዋቸው ቆይተው ሰለቹ::

ከዛም ለ15 ዓመታት ላበታቸው በግንባራቸው እየተቀዳ: ያለ ምንም ምግብ እያቃሰቱ በበዓታቸው ወድቀው ኑረዋል:: ቸሩ አምላክ ግን 4ቱን ሊቃነ መላእክት ( #ሚካኤል: #ገብርኤል: #ሩፋኤልና #ሳቁኤልን) አዞላቸው ሲጠብቁዋቸው ኑረዋል::

በዚህች ቀንም #አቡነ_ኪሮስ መጥተው አጽናንተው: ጌታችንንም ጠርተው እንዲያርፉ አድርገዋል:: መላእክት እያጠኑና እየዘመሩ ጻድቁ ቀብረዋቸዋል:: በመቃብራቸውም ላይ ፈውስ የሆነ ጸበል ፈልቁዋል::

††† እግዚአብሔር የእኛን ያይደለ የጻድቃኑን ቅድስና አስቦ ይራራልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን:: አሜን!


ሐምሌ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አቡነ ኪሮስ ጻድቅ (አረጋዊና ገዳማዊ)
2.አባ ብሶይ ጻድቅ (ኮከበ ገዳም)
3.አባ ሚሳኤል ነዳይ (ጻድቅ)
4.አባ ቢማ ሰማዕት
5.አባ በላኒ ሰማዕት
6.ቅዱሳን አቤሮንና አቶም (ሰማዕታት)

ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
4.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

ንባብ 1

"በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው:: የኃጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሠቢያ ለበረከት ነው::"
(ምሳ. 10:7)

ንባብ 2

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::"
(መዝ. 36:28-31)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዝክረ ቅዱሳን
20 views17:46
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-13 19:58:46 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፯ (7)

" እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ እና ለቅዱሳን
አበው አብርሃም: አባ_ሲኖዳ እና አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫ
ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ "

" ሥሉስ_ቅዱስ "

በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት)
የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ
#እግዚአብሔር ነው:: #አብ : #ወልድ : #መንፈስ_ቅዱስ
በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት: በባሕርይ: በሕልውናና
በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ
ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት " #ቅድስት_ሥላሴ "
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው
ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል
በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
#ቅዱስ_አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን
በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል:: ሥላሴ
አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው:: ነገር ግን በፍቅር
ለሚሻው በፍቅር ይመጣል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ
ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!)
ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው
ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት:: #ቅድስት_ሣራ ሳቀች::
እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም:: ደስታና ጉጉት
የፈጠረው እንጂ:: ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ"
ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው " #ይስሐቅ" የተባለው::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ #አብ
ለአጽንኦ: #መንፈስ_ቅዱስ ለአንጽሖ: #ወልድ በተለየ አካሉ
ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::


" ታላቁ_አባ_ሲኖዳ "

የባሕታውን ሁሉ አለቃቸው ታላቁ ቅዱስ ሲኖዳ:-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ
¤በእናቱ ማሕጸን ሳለ መላእክት በሰይፈ እሳት ይጠብቁት የነበረ
¤የታላቅነት ትንቢት የተነገረለት
¤ገና ሳይወለድ ሥውራን አበው የሰገዱለት
¤በሕጻን ሰውነቱ ጾምና ጸሎትን የጀመረ
¤የልጅነት ቁርስና ምሳውን ለነዳያን ያካፍል የነበረ
¤በ9 ዓመቱ ወደ በርሃ የመነነ
¤የአባ አብጐል ደቀ መዝሙር የሆነ አባት ነው::

+ሲመነኩስም በእግዚአብሔር ትእዛዝ #የሠለስቱ_ደቂቅ
አስኬማ: #የኤልያስ ቆብዕ እና የመጥምቁ #ዮሐንስ ቅናትን
(መታጠቂያ) ከያሉበት መላእክት አምጥተውለት የመነኮሰ
¤ዓለምን በሙሉ በጸሎቱ ይጠብቅ የነበረ
¤የግብፅን በርሃ በብርሃን የሞላ
¤በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ
¤ያለ ማቇረጥ በየቀኑ ከ100 ዓመታት በላይ ከጌታችን ክርስቶስ ጋር የተነጋገረ
¤ደመናትን ተጭኖ ይሔድ የነበረና
¤ያለ ዕረፍት ለ111 ዓመታት ከ2 ወራት ፈጣሪውን ያገለገለ አባት ነው::

+በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ገዳማውያን ሁሉ እየሰሙ
እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ:: "ሲኖዳ ተሠይመ
#አርሲመትሪዳ " (ሲኖዳ አርሲመትሪዳ ሆኗል:: ማለትም
ለባሕታውያን ሁሉ አለቃ ሁኖ ተመርጧል ማለት ነው:: )

+ቅዱሱ የጌታችንን እግር እያጠበም ይጠጣ ነበር::
+በዚህች ዕለት በ120 ዓመቱ ጌታችን ወርዶ ሲያሳርገው
#አቡነ_ኪሮስ "ታላቅ ምሰሶ (ታላቅ ዛፍ) ወደቀ" ብለው
አልቅሰዋል:: #ሲኖዳ ማለት "ደግ ሰው" ማለት ነው::


" አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ "
( #GIYORGIS_OF_SEGLA )

ታላቁ ኢትዮዽያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ #ጋስጫ
ውስጥ በ1358 ዓ/ም ነው:: ከልጅነቱ ትምሕርት አልገባሕ
ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር:: መምሕሩ
"ትምሕርት አይገባውምና ውሰዱት" ቢላቸው "የእግዚአብሔር
ነውና ያገልግላችሁ" ብለው መለሱት:: መገፋቱን የተመለከተ
#አባ_ጊዮርጊስ #እመቤታታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና
ይማጸናት ገባ::

+ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ: እሕል ሲፈጭና ሲከካ: ላቡንም
ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር:: ድንግል
እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና #ቅዱስ_ዑራኤልን አስከትላ
መጣችለት:: በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው::
"ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል:: ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው
ተሠወረችው::

+ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ:: በጽድቁ
ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ:: ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው:
መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ:: የተረጐማቸውና
ያተታቸውን ሳይጨምር 41 ድርሰቶችን ደረሰ:: (መጽሐፈ
ሰዓታት: መጽሐፈ ምሥጢር: አርጋኖን: ኆኅተ ብርሃን: ውዳሴ መስቀል: ወዘተ . . . የእርሱ ድርሰቶች ነበሩ)

+ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር:: ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢ/
ኦ/ተ/ቤ እንዲህ ትጠራዋለች:-
1. #ሊቀ_ሊቃውንት
2. #በላዔ_መጻሕፍት
3. #ዓምደ_ሃይማኖት
4. #ዳግማዊ_ቄርሎስ
5. #ጠቢብ_ወማዕምር

+ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በ60 ዓመቱ በ1418 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ 7 ቀን ነው::

=>የሥላሴ ቸርነት: የአብርሃም ደግነት: የአበው አባ ጊዮርጊስና አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን::አሜን!


ሐምሌ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱሳን አብርሃምና ሣራ (ሥላሴን ያስተናገዱ)
2.ብሥራተ ልደተ ይስሐቅ
3.ታላቁ አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን ሁሉ አለቃ)
4.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ሊቀ ሊቃውንት: ኢትዮዽያዊ
የሃይማኖት ምሰሶ)
5.ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (ምጥው ለአንበሳ)
6.አባ መቃቢስ
7.አባ አግራጥስ

ወርሐዊ በዓላት

1.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
2.አባ ባውላ ገዳማዊ
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

ንባብ 1

" እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:-
'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ'
ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ::
እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ:: "
(ዕብ. 6:13)

ንባብ 2

" የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር:
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: " (ቆሮ. 13:14)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
30 views16:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-12 20:43:19 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፮ (6)

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

" ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ "

ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ60ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

" ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ "

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት አካባቢ የነበረ
¤እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

††† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

††† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን:: አሜን!


ሐምሌ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
5.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

ንባብ

"እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ::" (፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
30 views17:43
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-11 19:13:17 https://vm.tiktok.com/ZMNPFcFvg/?k=1

እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ::

ሐምሌ ፭ (5), ፳፻፲፬ (2014)

ጴጥሮስ ወጳውሎስ
30 viewsedited  16:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-11 18:49:04 ✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፭ (5)

እንኩዋን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ዼጥሮስ ወዻውሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

ፍጡር ቢከብር ከእመ ብርሃን ቀጥሎ የእነዚህን
ቅዱሳን ያህል የሚከብር አይኖርም:: ለቤተ ክርስቲያን
ያልሆኑላት ምንም ነገር የለምና እርሷም "ብርሃኖቼ:
ዐይኖቼ: ዕንቁዎቼ" ብላ ትጠራቸዋለች::

" ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት "

የዮና ልጅ ስምዖን ዼጥሮስ (ኬፋ) የተባለው በጌታችን
ንጹሕ አንደበት ነው:: ይሔውም ዓለት (መሰረት) እንደ
ማለት ነው::
¤በቤተ ሳይዳ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሳ በማጥመድ አድጐ

¤ሚስት አግብቶ ዕድሜው 56 ሲደርስ ነበር ጌታችን
የተቀበለው:: በዕድሜውም ሆነ በቅንዐቱ:
በአስተዋይነቱም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ተብሏል::
ለሐዋርያትም አለቃቸው ሆኗል:: (ማቴ. 16:17, ዮሐ.
21:15)

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ለሰራው
ስሕተት ንስሃ ገብቶ ምሳሌም ሆኗል:: ቅዱስ ዼጥሮስ
እንደ እረኝነቱ ሐዋርያትን ጠብቆ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ
ሲያበቃ ከበዓለ ሃምሳ በሁዋላም ለሁሉም ሃገረ ስብከት
አካፍሏል:: ምንም የርሱ ክፍል ሮሜ ብትሆንም አርድእትን
ስለ ማጽናት በሁሉም አሕጉራት ዙሯል::

+በስተእርጅናው ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል:: አሕዛብ
ግብራቸው እንደ እንስሳ ነውና በአባታችን ላይ ቀልደዋል::
እርሱ ግን ሁሉንም ታግሷል:: የቅዱሱን ታሪክ ለመናገር
ከመብዛቱ የተነሳ ይከብዳልና ልቡና ያለው ሰው
ሊቃውንትን ሊጠይቅ እንደሚገባ እመክራለሁ::

+ቅዱስ ዼጥሮስ መልካሙን ገድል ተጋድሎ በ66 ዓ/ም
የኔሮን ቄሳር ወታደሮች ሲሰቅሉት ለመናቸው::
"እባካችሁን? እኔ እንደ ጌታየ ሆኜ መሰቀል አይገባኝም"
አላቸው:: እነሱም ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል:: በበጐ
እረኝነቱም የማታልፈውን ርስት ከነመክፈቻዋ ተቀብሏል:: በሰማዕትነት ሲያርፍም ዕድሜው ወደ 88 አካባብ ደርሶ
ነበር::

=>የቅዱስ_ዼጥሮስ መጠሪያዎች:-

1.ሊቀ ሐዋርያት
2.ሊቀ ኖሎት (የእረኞች / ሐዋርያት አለቃ)
3.መሠረተ ቤተ ክርስቲያን
4.ኰኩሐ ሃይማኖት (የሃይማኖት ዐለት)
5.አርሳይሮስ (የዓለም ሁሉ ፓትርያርክ)

" ቅዱስ_ዻውሎስ_ሐዋርያ "

የቤተ ክርስቲያን መብራቷ ቅዱስ ዻውሎስን እንደ ምን
ባለ ዐማርኛ እንገልጠዋለን?
¤ስለ እርሱ መናገርና መጻፍ የሚችልስ እንደ ምን ያለ
ሰው ነው?
¤የዓለምን ነገር ሲጽፍ በኖረ እጄስ እንደ ምን
እጽፈዋለሁ?
¤ይልቁኑስ የርሱን 14ቱን መልዕክታትና ግብረ ሐዋርያትን
መመልከቱ ሳይሻል አይቀርም::

+ቅዱስ_ዻውሎስ ከነገደ ብንያም #ሳውል የሚባል
የጠርሴስ ሰው ሲሆን ምሑረ ኦሪት: ቀናተኛና ፈሪሳዊ
ነበር:: ጌታ በደማስቆ ጐዳና ጠርቶ በ3 ቀናት ልዩነት
ምርጥ ዕቃ አደረገው:: ይህ የሆነው በ42 ዓ/ም: ጌታ
ባረገ በ8ኛው ዓመት ነበር:: ከዚያማ ብርሃን ሆኖ አበራ::

ጨው ሆኖ አጣፈጠ::

+ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም: ከእንግሊዝ እስከ እልዋሪቆን
(የዓለም መጨረሻ) ወንጌልን ሰበከ:: ስለ ወንጌል
ተደበደበ: ታሠረ: በእሳት ተቃጠለ:: በድንጋይ ተወገረ:
በጦር ተወጋ:: ባፍም በመጣፍም ብሎ አገለገለ::
በየቦታውም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ሠራ:: ለ25 ዓመታት
ቀንና ሌሊት ያለ መታከት ወንጌልን ሰበከ::

+እርሱን የመሰሉ: እርሱንም ያከሉ ብዙ አርድእትን አፍርቶ:
በ67 ዓ/ም በኔሮን ቄሳር ትእዛዝ አንገቱ ተቆርጧል::
ከ14ቱ መልዕክታቱ ባሻገር ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን ሲጽፍ
አግዞታል:: ልክ ቅዱስ ዼጥሮስ ማርቆስን እንዳገዘው
ማለት ነው::

= >የቅዱስ ዻውሎስ መጠሪያዎች:-

1.ሳውል (ከእግዚአብሔር የተሰጠ)
2.#ልሳነ_ዕፍረት (አንደበቱ እንደ ሽቱ የሚጣፍጥ)
3.#ልሳነ_ክርስቶስ (የክርስቶስ አንደበቱ)
4.#ብርሃነ_ዓለም
5.#ማኅቶተ_ቤተ_ክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መቅረዝ)
6.#የአሕዛብ_መምሕር
7.#መራሒ (ወደ መንግስተ ሰማያት የሚመራ)
8.#አእኩዋቲ (በምስጋና የተሞላ)
9.#ንዋይ_ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ)
10.#መዶሻ (ለአጋንንትና መናፍቃን)
11.#መርስ (ወደብ)
12.#ዛኅን (ጸጥታ)
13.#ነቅዐ_ሕይወት (የሕይወት ትምሕርትን ከአንደበቱ
ያፈለቀ)
14.#ዐዘቅተ_ጥበብ (የጥበብ ምንጭ / ባሕር)
15.#ፈዋሴ_ዱያን (ድውያንን የፈወሰ) . . .

=>ጌታችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ብርሃን ያብራልን::
ከበረከታቸውም ያድለን:: አሜን!


ሐምሌ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.ቅዱሳን 72ቱ አርድእት (ዛሬ ሁሉም ይታሠባሉ)
4.ቅዱስ ሳቁኤል ሊቀ መላእክት
5.ቅድስት መስቀል ክብራ (የቅዱስ ላሊበላ ሚስት)
6.ቅዱሳን ዘደብረ ዓሣ
7.ቅዱሳት አንስት (ዴውርስ: ቃርያ: አቅባማ: አቅረባንያና
አክስቲያና-የቅዱስ ዼጥሮስ ተከታዮች)

ወርሐዊ በዓላት

1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
2.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
3.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
4.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

ንባብ 1

" ጌታ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው:: "የዮና
ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና
ደም ይሕንን አልገለጠልህምና ብጹዕ ነህ:: እኔም
እልሃለሁ:: አንተ #ዼጥሮስ ነህ:: በዚህችም ዓለት ላይ
ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ:: የገሃነም ደጆችም
አይችሏትም:: የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች
እሰጥሃለሁ:: በምድር የምታሥረው ሁሉ በሰማያት የታሠረ
ይሆናል:: በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ
ይሆናል:: " (ማቴ. 16:17)


ንባብ 2

" በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት
ይሠዋልና:: የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል:: መልካሙን
ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖትን
ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት #የጽድቅ_አክሊል ተዘጋጅቶልኛል::
ይሕንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ
ያስረክባል:: " (2ጢሞ. 4:6)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
31 views15:49
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-10 21:25:59 ✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፬ (4)

እንኳን ለአባቶቻችን ቅዱሳን 12ቱ ደቂቀ ነቢያት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

✞" 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት "✞

ነቢይ ማለት ከእግዚብሔር ተመርጦ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን): መጻዕያትን (ለወደፊቱ የሚደረገውን) የሚያውቁ ሰዎች ሲሆኑ ሕዝቡን እንዲመሩ: እንዲገስጹም ይላካሉ:: ሕይወታቸውም በቅድስና የተለበጠ ነው:: ነቢያትን በቁጥር መግለጽ ከባድ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እንድንረዳቸው እንዲህ ትከፍላቸዋለች::

=>በኩረ ነቢያት_አዳም
=>ሊቀ ነቢያት_ሙሴ
=>ርዕሰ ነቢያት_ኤልያስ
=>ልበ አምላክ_ዳዊት
=>15ቱ ነቢያት (ከአዳም ጀምሮ እስከ ሳሙኤል)

=>4ቱ ዐበይት ነቢያት (ኢሳይያስ: ኤርምያስ: ሕዝቅኤልና ዳንኤል)

=>12ቱ ደቂቀ ነቢያት ደግሞ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ናቸው::
+በዚህች ቀን ታዲያ 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት በአንድነት ይታሠባሉ:: እነዚህም:-

1.ቅዱስ ሆሴዕ (ኦዝያ)
2.ቅዱስ አሞጽ
3.ቅዱስ ሚክያስ
4.ቅዱስ ኢዩኤል
5.ቅዱስ አብድዩ
6.ቅዱስ ዮናስ
7.ቅዱስ ናሆም
8.ቅዱስ እንባቆም
9.ቅዱስ ሶፎንያስ
10.ቅዱስ ሐጌ
11.ቅዱስ ዘካርያስ እና
12.ቅዱስ ሚልክያስ ናቸው::

+ቅዱሳኑ ደቂቀ ነቢያት የተባሉት
1.የነቢያት ልጆች በመሆናቸው
2.የጻፏቸው ሐረገ ትንቢቶች በንጽጽር ከዐበይቱ (ከነኢሳይያስ) ስለሚያንስ ነው::

+በምግባር: በትሩፋት: በአገልግሎት ግን ያው ናቸው:: ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እሊህን ነቢያት "እለ አውኀዙ ተነብዮ በእንተ ስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ" ይሏቸዋል:: ( ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መውረድ: መወለድና የማዳን ሥራ የትንቢት ጐርፍን ያፈሰሱ እንደ ማለት ነው :: )

+ቅዱሳኑ ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ባሻገር ዓለማችን ላይ ከነበሩበት ዘመን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሊደረጉ ያላቸውን ነገሮችም ተናግረዋል:: የነበሩበት ዘመን በአማካኝ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ900 እስከ 500 ነው:: በትንቢት ደረጃም እንደነ ሆሴዕና ዘካርያስ 14 ምዕራፎችን: እንደነ አብድዩም አንዲት ምዕራፍ ብቻም የጻፉ አሉ::

+በሕይወታቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያሻቸው ናቸውና በየጊዜው ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ የእርሱን ድምጽ ለእሥራኤል (አንዳንዴም ለአሕዛብ) ያደርሱ ነበር:: ፊት አይተው የማያዳሉ ናቸውና ሕዝቡንም ሆነ ነገሥታቱን ስለ ኃጢአታቸው ይገሰጹ ነበር:: በዚህም ምክንያት ከነገሥታቱና ከሕዝቡ አለቆች መከራ ደርሶባቸዋል:: አልፎም ያለ አበሳቸው ሕዝቡ በኃጢአቱ ሲማረክ አብረውት ወርደዋል::

+በመጨረሻ ሕይወታቸውም አንዳንዶቹን ክፉዎች ሲገድሏቸው አንዳንዶቹ ደግሞ በመልካም ሽምግልና ዐርፈዋል:: ዛሬ ነቢያት ከእነርሱ ባሕርይ በተገኘችና ብዙ ትንቢትን በተናገሩላት በእመቤታችን ምክንያት ክርስቶስ ድኅነትን ፈጽሞላቸው በተድላ ገነት ይኖራሉ:: ስለ እኛም ይማልዳሉ::

=>" ናጥሪ እንከ ትሕትና ዘምስለ ንጽሕና"
(እንግዲህ እንደ ነቢያት ትሕትናን ከንጽሕና ጋር ገንዘብ እናድርግ)
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ"
(ነቢያት መንፈስን ንጹሕ በማድረግ እግዚአብሔርን አይተውታልና: ፊት ለፊትም ተያይተዋልና)
/ቅዳሴ ማርያም/

=>ከአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት በረከት ይክፈለን::


ሐምሌ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1."12ቱ" ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት
2.ቅዱስ ሶፎንያስ ነቢይ (ዕረፍቱ)
3.ቅዱሳን ሰማዕታት አቡቂርና ዮሐንስ (ቅዳሴ ቤታቸው)

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ /ወንጌላዊው/
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ /ሰማዕት/

ንባብ

" ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት:: በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በሁዋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሠከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር:: " (1ዼጥ. 1:10)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
31 views18:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-09 21:21:21 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፫ (3)

እንኳን ለዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

" ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ "

ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን " ዓምደ_ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ_ቴዎፍሎስ እህቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል:: ገና በልጅነቱ ወደ አባ_ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በጾም: በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር::

ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው:: መንፈስ_ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኩዋን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም:: ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ::

ከዚያም በ412 ዓ/ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ዻዻሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ:: የእስክንድርያም 24ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ ቤተ_ክርስቲያን አበራች:: በቅድስናው: በሊቅነቱ: በስብከቱ: በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት::

በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን "2 አካል: ባሕርይ ነው" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ 2 የከፈለው እመቤታችንንየአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: (ላቲ ስብሐት!)

ነገሩን ቅዱስ_ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ:: ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ431 ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና 200 ቅዱሳን_ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በሁዋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል_ማርያምም ወላዲተ_አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

††† ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም " ታኦዶኮስ(የእግዚአብሔር እናቱ) ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን:-
¤የአምላክ እናት:
¤ዘላለማዊት ድንግል:
¤ፍጽምት:
¤ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::
ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለ32 ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ: ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ: ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ444 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከድርሰቶቹም ቅዳሴው: ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን:: ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን:: አሜን!


ሐምሌ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
2.ቅዱስ ክልስቲያኖስ ዘሮሜ (ታላቅ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት)
3.አባ ሉቅያስ ኤዺስ ቆዾስ

ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

ንባብ

"የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ:: የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ: እስከ ዘለዓለምም ያው ነው:: ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምሕርት አትወሰዱ:: ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም:: በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና::" (ዕብ. 13:7)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዝክረ ቅዱሳን
28 views18:21
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-07-08 21:08:28 ✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፪ (2)

እንኩዋን ለሐዋርያው ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

" ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ "

ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን:: አሜን!


ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

ንባብ

" ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: " (ማር. 10:23-28)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን
26 views18:08
ክፈት / አስተያየት ይስጡ