Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን! ወርኃ ሐምሌ ቀን ፯ (7) ' | ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፯ (7)

" እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም ሥላሴ እና ለቅዱሳን
አበው አብርሃም: አባ_ሲኖዳ እና አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫ
ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ "

" ሥሉስ_ቅዱስ "

በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት)
የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ
#እግዚአብሔር ነው:: #አብ : #ወልድ : #መንፈስ_ቅዱስ
በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት: በባሕርይ: በሕልውናና
በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ
ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት " #ቅድስት_ሥላሴ "
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው
ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል
በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
#ቅዱስ_አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን
በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል:: ሥላሴ
አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው:: ነገር ግን በፍቅር
ለሚሻው በፍቅር ይመጣል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ
ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!)
ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው
ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት:: #ቅድስት_ሣራ ሳቀች::
እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም:: ደስታና ጉጉት
የፈጠረው እንጂ:: ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ"
ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው " #ይስሐቅ" የተባለው::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ #አብ
ለአጽንኦ: #መንፈስ_ቅዱስ ለአንጽሖ: #ወልድ በተለየ አካሉ
ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::


" ታላቁ_አባ_ሲኖዳ "

የባሕታውን ሁሉ አለቃቸው ታላቁ ቅዱስ ሲኖዳ:-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ
¤በእናቱ ማሕጸን ሳለ መላእክት በሰይፈ እሳት ይጠብቁት የነበረ
¤የታላቅነት ትንቢት የተነገረለት
¤ገና ሳይወለድ ሥውራን አበው የሰገዱለት
¤በሕጻን ሰውነቱ ጾምና ጸሎትን የጀመረ
¤የልጅነት ቁርስና ምሳውን ለነዳያን ያካፍል የነበረ
¤በ9 ዓመቱ ወደ በርሃ የመነነ
¤የአባ አብጐል ደቀ መዝሙር የሆነ አባት ነው::

+ሲመነኩስም በእግዚአብሔር ትእዛዝ #የሠለስቱ_ደቂቅ
አስኬማ: #የኤልያስ ቆብዕ እና የመጥምቁ #ዮሐንስ ቅናትን
(መታጠቂያ) ከያሉበት መላእክት አምጥተውለት የመነኮሰ
¤ዓለምን በሙሉ በጸሎቱ ይጠብቅ የነበረ
¤የግብፅን በርሃ በብርሃን የሞላ
¤በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ
¤ያለ ማቇረጥ በየቀኑ ከ100 ዓመታት በላይ ከጌታችን ክርስቶስ ጋር የተነጋገረ
¤ደመናትን ተጭኖ ይሔድ የነበረና
¤ያለ ዕረፍት ለ111 ዓመታት ከ2 ወራት ፈጣሪውን ያገለገለ አባት ነው::

+በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ገዳማውያን ሁሉ እየሰሙ
እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ:: "ሲኖዳ ተሠይመ
#አርሲመትሪዳ " (ሲኖዳ አርሲመትሪዳ ሆኗል:: ማለትም
ለባሕታውያን ሁሉ አለቃ ሁኖ ተመርጧል ማለት ነው:: )

+ቅዱሱ የጌታችንን እግር እያጠበም ይጠጣ ነበር::
+በዚህች ዕለት በ120 ዓመቱ ጌታችን ወርዶ ሲያሳርገው
#አቡነ_ኪሮስ "ታላቅ ምሰሶ (ታላቅ ዛፍ) ወደቀ" ብለው
አልቅሰዋል:: #ሲኖዳ ማለት "ደግ ሰው" ማለት ነው::


" አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ "
( #GIYORGIS_OF_SEGLA )

ታላቁ ኢትዮዽያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ #ጋስጫ
ውስጥ በ1358 ዓ/ም ነው:: ከልጅነቱ ትምሕርት አልገባሕ
ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር:: መምሕሩ
"ትምሕርት አይገባውምና ውሰዱት" ቢላቸው "የእግዚአብሔር
ነውና ያገልግላችሁ" ብለው መለሱት:: መገፋቱን የተመለከተ
#አባ_ጊዮርጊስ #እመቤታታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና
ይማጸናት ገባ::

+ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ: እሕል ሲፈጭና ሲከካ: ላቡንም
ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር:: ድንግል
እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና #ቅዱስ_ዑራኤልን አስከትላ
መጣችለት:: በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው::
"ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል:: ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው
ተሠወረችው::

+ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ:: በጽድቁ
ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ:: ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው:
መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ:: የተረጐማቸውና
ያተታቸውን ሳይጨምር 41 ድርሰቶችን ደረሰ:: (መጽሐፈ
ሰዓታት: መጽሐፈ ምሥጢር: አርጋኖን: ኆኅተ ብርሃን: ውዳሴ መስቀል: ወዘተ . . . የእርሱ ድርሰቶች ነበሩ)

+ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር:: ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢ/
ኦ/ተ/ቤ እንዲህ ትጠራዋለች:-
1. #ሊቀ_ሊቃውንት
2. #በላዔ_መጻሕፍት
3. #ዓምደ_ሃይማኖት
4. #ዳግማዊ_ቄርሎስ
5. #ጠቢብ_ወማዕምር

+ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በ60 ዓመቱ በ1418 ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል:: አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ 7 ቀን ነው::

=>የሥላሴ ቸርነት: የአብርሃም ደግነት: የአበው አባ ጊዮርጊስና አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን::አሜን!


ሐምሌ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱሳን አብርሃምና ሣራ (ሥላሴን ያስተናገዱ)
2.ብሥራተ ልደተ ይስሐቅ
3.ታላቁ አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን ሁሉ አለቃ)
4.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ሊቀ ሊቃውንት: ኢትዮዽያዊ
የሃይማኖት ምሰሶ)
5.ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (ምጥው ለአንበሳ)
6.አባ መቃቢስ
7.አባ አግራጥስ

ወርሐዊ በዓላት

1.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
2.አባ ባውላ ገዳማዊ
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

ንባብ 1

" እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:-
'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ'
ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ::
እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ:: "
(ዕብ. 6:13)

ንባብ 2

" የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር:
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: " (ቆሮ. 13:14)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን