Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን! ወርኃ ሐምሌ ቀን ፮ (6) | ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፮ (6)

እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

" ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ "

ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ60ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

" ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ "

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት አካባቢ የነበረ
¤እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

††† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

††† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን:: አሜን!


ሐምሌ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
5.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

ንባብ

"እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ::" (፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን