Get Mystery Box with random crypto!

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞ ወርኃ ሐምሌ ቀን | ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፭ (5)

እንኩዋን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ዼጥሮስ ወዻውሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

ፍጡር ቢከብር ከእመ ብርሃን ቀጥሎ የእነዚህን
ቅዱሳን ያህል የሚከብር አይኖርም:: ለቤተ ክርስቲያን
ያልሆኑላት ምንም ነገር የለምና እርሷም "ብርሃኖቼ:
ዐይኖቼ: ዕንቁዎቼ" ብላ ትጠራቸዋለች::

" ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት "

የዮና ልጅ ስምዖን ዼጥሮስ (ኬፋ) የተባለው በጌታችን
ንጹሕ አንደበት ነው:: ይሔውም ዓለት (መሰረት) እንደ
ማለት ነው::
¤በቤተ ሳይዳ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሳ በማጥመድ አድጐ

¤ሚስት አግብቶ ዕድሜው 56 ሲደርስ ነበር ጌታችን
የተቀበለው:: በዕድሜውም ሆነ በቅንዐቱ:
በአስተዋይነቱም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ተብሏል::
ለሐዋርያትም አለቃቸው ሆኗል:: (ማቴ. 16:17, ዮሐ.
21:15)

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ለሰራው
ስሕተት ንስሃ ገብቶ ምሳሌም ሆኗል:: ቅዱስ ዼጥሮስ
እንደ እረኝነቱ ሐዋርያትን ጠብቆ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ
ሲያበቃ ከበዓለ ሃምሳ በሁዋላም ለሁሉም ሃገረ ስብከት
አካፍሏል:: ምንም የርሱ ክፍል ሮሜ ብትሆንም አርድእትን
ስለ ማጽናት በሁሉም አሕጉራት ዙሯል::

+በስተእርጅናው ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል:: አሕዛብ
ግብራቸው እንደ እንስሳ ነውና በአባታችን ላይ ቀልደዋል::
እርሱ ግን ሁሉንም ታግሷል:: የቅዱሱን ታሪክ ለመናገር
ከመብዛቱ የተነሳ ይከብዳልና ልቡና ያለው ሰው
ሊቃውንትን ሊጠይቅ እንደሚገባ እመክራለሁ::

+ቅዱስ ዼጥሮስ መልካሙን ገድል ተጋድሎ በ66 ዓ/ም
የኔሮን ቄሳር ወታደሮች ሲሰቅሉት ለመናቸው::
"እባካችሁን? እኔ እንደ ጌታየ ሆኜ መሰቀል አይገባኝም"
አላቸው:: እነሱም ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል:: በበጐ
እረኝነቱም የማታልፈውን ርስት ከነመክፈቻዋ ተቀብሏል:: በሰማዕትነት ሲያርፍም ዕድሜው ወደ 88 አካባብ ደርሶ
ነበር::

=>የቅዱስ_ዼጥሮስ መጠሪያዎች:-

1.ሊቀ ሐዋርያት
2.ሊቀ ኖሎት (የእረኞች / ሐዋርያት አለቃ)
3.መሠረተ ቤተ ክርስቲያን
4.ኰኩሐ ሃይማኖት (የሃይማኖት ዐለት)
5.አርሳይሮስ (የዓለም ሁሉ ፓትርያርክ)

" ቅዱስ_ዻውሎስ_ሐዋርያ "

የቤተ ክርስቲያን መብራቷ ቅዱስ ዻውሎስን እንደ ምን
ባለ ዐማርኛ እንገልጠዋለን?
¤ስለ እርሱ መናገርና መጻፍ የሚችልስ እንደ ምን ያለ
ሰው ነው?
¤የዓለምን ነገር ሲጽፍ በኖረ እጄስ እንደ ምን
እጽፈዋለሁ?
¤ይልቁኑስ የርሱን 14ቱን መልዕክታትና ግብረ ሐዋርያትን
መመልከቱ ሳይሻል አይቀርም::

+ቅዱስ_ዻውሎስ ከነገደ ብንያም #ሳውል የሚባል
የጠርሴስ ሰው ሲሆን ምሑረ ኦሪት: ቀናተኛና ፈሪሳዊ
ነበር:: ጌታ በደማስቆ ጐዳና ጠርቶ በ3 ቀናት ልዩነት
ምርጥ ዕቃ አደረገው:: ይህ የሆነው በ42 ዓ/ም: ጌታ
ባረገ በ8ኛው ዓመት ነበር:: ከዚያማ ብርሃን ሆኖ አበራ::

ጨው ሆኖ አጣፈጠ::

+ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም: ከእንግሊዝ እስከ እልዋሪቆን
(የዓለም መጨረሻ) ወንጌልን ሰበከ:: ስለ ወንጌል
ተደበደበ: ታሠረ: በእሳት ተቃጠለ:: በድንጋይ ተወገረ:
በጦር ተወጋ:: ባፍም በመጣፍም ብሎ አገለገለ::
በየቦታውም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ሠራ:: ለ25 ዓመታት
ቀንና ሌሊት ያለ መታከት ወንጌልን ሰበከ::

+እርሱን የመሰሉ: እርሱንም ያከሉ ብዙ አርድእትን አፍርቶ:
በ67 ዓ/ም በኔሮን ቄሳር ትእዛዝ አንገቱ ተቆርጧል::
ከ14ቱ መልዕክታቱ ባሻገር ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን ሲጽፍ
አግዞታል:: ልክ ቅዱስ ዼጥሮስ ማርቆስን እንዳገዘው
ማለት ነው::

= >የቅዱስ ዻውሎስ መጠሪያዎች:-

1.ሳውል (ከእግዚአብሔር የተሰጠ)
2.#ልሳነ_ዕፍረት (አንደበቱ እንደ ሽቱ የሚጣፍጥ)
3.#ልሳነ_ክርስቶስ (የክርስቶስ አንደበቱ)
4.#ብርሃነ_ዓለም
5.#ማኅቶተ_ቤተ_ክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መቅረዝ)
6.#የአሕዛብ_መምሕር
7.#መራሒ (ወደ መንግስተ ሰማያት የሚመራ)
8.#አእኩዋቲ (በምስጋና የተሞላ)
9.#ንዋይ_ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ)
10.#መዶሻ (ለአጋንንትና መናፍቃን)
11.#መርስ (ወደብ)
12.#ዛኅን (ጸጥታ)
13.#ነቅዐ_ሕይወት (የሕይወት ትምሕርትን ከአንደበቱ
ያፈለቀ)
14.#ዐዘቅተ_ጥበብ (የጥበብ ምንጭ / ባሕር)
15.#ፈዋሴ_ዱያን (ድውያንን የፈወሰ) . . .

=>ጌታችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ብርሃን ያብራልን::
ከበረከታቸውም ያድለን:: አሜን!


ሐምሌ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.ቅዱሳን 72ቱ አርድእት (ዛሬ ሁሉም ይታሠባሉ)
4.ቅዱስ ሳቁኤል ሊቀ መላእክት
5.ቅድስት መስቀል ክብራ (የቅዱስ ላሊበላ ሚስት)
6.ቅዱሳን ዘደብረ ዓሣ
7.ቅዱሳት አንስት (ዴውርስ: ቃርያ: አቅባማ: አቅረባንያና
አክስቲያና-የቅዱስ ዼጥሮስ ተከታዮች)

ወርሐዊ በዓላት

1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
2.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
3.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
4.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

ንባብ 1

" ጌታ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው:: "የዮና
ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና
ደም ይሕንን አልገለጠልህምና ብጹዕ ነህ:: እኔም
እልሃለሁ:: አንተ #ዼጥሮስ ነህ:: በዚህችም ዓለት ላይ
ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ:: የገሃነም ደጆችም
አይችሏትም:: የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች
እሰጥሃለሁ:: በምድር የምታሥረው ሁሉ በሰማያት የታሠረ
ይሆናል:: በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ
ይሆናል:: " (ማቴ. 16:17)


ንባብ 2

" በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት
ይሠዋልና:: የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል:: መልካሙን
ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖትን
ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት #የጽድቅ_አክሊል ተዘጋጅቶልኛል::
ይሕንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ
ያስረክባል:: " (2ጢሞ. 4:6)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን