Get Mystery Box with random crypto!

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞ ወርኃ ሐምሌ ቀን ፪ | ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞

ወርኃ ሐምሌ
ቀን ፪ (2)

እንኩዋን ለሐዋርያው ቅዱስ_ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

" ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ "

ቅዱሳን_ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ3 ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤እንደ ዮሐንስ_ወንጌላዊ ያሉት በ20ዎቹ ውስጥ:
¤ቅዱስ_ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ30ና በ40ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤እነ ቅዱስ_ዼጥሮስ ደግሞ በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

+ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

+ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ:
¤ከ12ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤በዕርገቱ ተባርኮ:
¤በበዓለ ሃምሳም 71 ልሳናትን ተቀብሎ:
¤#ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

+ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

+ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: 2ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

+ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

+እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

+ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ ቅዱስ_ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

+አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት 3 ጊዜ አሳልፎታል::

+ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" (ማር. 10:23) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

+ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

+ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን:: አሜን!


ሐምሌ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

ንባብ

" ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: " (ማር. 10:23-28)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን