2022-06-30 20:08:45
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን! ✞✞✞
❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖
ወርኃ ሰኔ
ቀን ፳፬ (24)
በዚች ዕለት የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
" ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) "
ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው
ቅዱሳን መካከል አንዱ ኢትዮዽያዊው አባ ሙሴ ጸሊም
ነው:: በእኛ ኢትዮዽያውያን ግን ይቅርና በወርኀዊ በዓሉ (በ24) በዓመታዊ በዓሉ እንኩዋ ሲከበር ብዙም አይታይም::
=>ቅዱሱ ሰው በትውልዱ ኢትዮዽያዊ
ሲሆን ያደገውም እዚሁ ሃገራችን ውስጥ እንደሆነ
ይታመናል:: ገና በወጣትነቱ አገር የሚያሸብር ሽፍታ ነበር::
ሙሴ ጸሊም
ወደ ግብጽ የሔደበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም
መምለክያነ ጣዖት (ፀሐይን ከሚያመልኩ ሰዎች) ጋር
ይኖር ስለ ነበር:: ምናልባት እነርሱ ወስደውት ሊሆን ይችላል::
+ቅዱስ_ሙሴ በምድረ ግብጽም በኃይለኝነቱ ምክንያት የሚደፍረው
አልነበረም:: ፀሐይን ያመልካል: እንደ ፈለገ ቀምቶ
ይበላል: ያሻውን
ሰው ይደበድባል:: ነገር ግን በኅሊናው ስለ እውነተኛው
አምላክ ይመራመር ነበርና አንድ ቀን ፀሐይን "አምላክ
ከሆንሽ አናግሪኝ?" አላት:: እርሷ ፍጡር ናትና ዝም አለችው::
+ቅዱስ ሙሴ ምንም አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ፈጣሪን
መፈለጉን ግን ቀጥሏልና አንድ ቀን ተሳካለት:: መልካም
ክርስቲያኖችን
አግኝቶ . . . ወደ ገዳመ_አስቄጥስ ቢሔድ በዛ ያሉ መነኮሳት ወደ እውነት እንደሚመሩት ነገሩት:: እርሱም ሰይፉን እንደታጠቀ ወደ ገዳም ገባ::
መነኮሳቱ ፈርተውት ሲሸሹ ታላቁ አባ_ኤስድሮስ ግን ተቀብለው አሳረፉት::
+"ምን ፈለግህ ልጄ?" አሉት:: "እውነተኛውን አምላክ ፊት
ለፊት ማየት እፈልጋለሁ" የሙሴ ጸሊም መልስ ነበር:: አባ
ኤስድሮስም "የማዝህን ሁሉ ካደረግህ ታየዋለህ" ብለው
ወደ መነኮሳት አለቃ ቅዱስ_መቃርስ_ታላቁ ወሰዱት:: መቃሬም ክርስትናን አስተምረው አጠመቁትና
ለአባ ኤስድሮስ መለሱላቸው::
+ከዚህ ሰዓት በሁዋላ ነበር የአባ ሙሴ ጸሊም ሕይወት
ፍጹም የተለወጠው:: በጻድቁ እጅ ምንኩስናን ተቀብሎ
ይጋደል ጀመር:: በጠባቧ በር ይገባ ዘንድ ወዷልና ያ በሽፍትነት የሞላ አካሉን በገድል አረገፈው:: ከቁመቱ በቀር ከአካሉ አልተረፈለትም:: ወገቡን በአጭር ታጥቆ መነኮሳትን አገለገለ:: አጋንንት በቀደመ ሕይወቱ በሕልም: አንዳንዴም በአካል እየመጡ ይፈትኑት ነበር::
+እንዳልቻሉት ሲረዱ ተሰብስበው መጥተው በእሳት
አለንጋ ገርፈው አቆሳስለውት ሔዱ:: እርሱ ግን ታገሰ::
በበርሃ ለሚኖሩ
አበው መነኮሳት ሁሉ ብርሃን በሆነ ሕይወቱ ሞገስ ሆነላቸው:: ለኃጥአን ደግሞ መጽናኛ
ሆነ::
<< በተራራ ላይ ያለች ሃገር ልትሠወር አይቻላትምና ስም
አጠራሩ በመላው ዓለም ተሰማ:: ሁሉም "ሙሴ_ጸሊም ይል ጀመር ፡፡ >>
+በየበርሃው ያሉ አበው ብቻ ሳይሆነ ዓለማውያን
መኩዋንንት ሳይቀሩ ሊያዩት ይመኙ ነበር:: እርሱ ግን
ራሱን "አንተ
ጥቁር ባሪያ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ" እያለ ይገስጽ:
ከውዳሴ ከንቱም ይርቅ ነበር:: ከቆይታ በኋላም
በመነኮሳት ላይ
እረኛ (አበ ምኔት) ሆኖ ተሾመ:: እንደሚገባም አገለገለ::
የበርካቶችን ሕይወት ጨው በሆነ ሕይወቱና ምክሩ
አጣፍጦ:
ድርሳናትንም ደርሶ እያረጀ ሔደ::
+ከቁመቱ መርዘም የጽሕሙ ነጭነትና አወራረዱን ያዩ
ሁሉ ሲያዩት ያደንቁት ነበር:: በመጨረሻም በ375 ዓ/ም
በርበረሮች
(አሕዛብ) ገዳመ አስቄጥስን ሲያጠፉ ሌሎች መነኮሳት
ሸሹ:: እርሱ ግን አልሸሽም ብሎ ከ7 ደቀ መዛሙርቱ ጋር
በዚሕች ቀን ተሰይፎ በሰማዕትነት አልፏል::
=>ቅዱስ ሙሴ ጸሊምን ለርስቱ ያበቃ ጌታ ለእኛም ዕድሜ
ለንስሃ: ለዘመን ለፍስሃን አይንሳን:: ከበረከቱም ፈጣሪው
ያድለን:: አሜን!
ሰኔ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
2."7ቱ" ቅዱሳን መነኮሳት (ደቀ መዛሙርቱ)
3.አባ ኤስድሮስ ታላቁ
ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
2፡ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3፡ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
4፡ ቅዱስ አጋቢጦስ
5፡ ቅዱስ አብላርዮስ
6፡ አቡነ ዘዮሐንስ ዘክብራን
7፡ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ
ንባብ
" መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና
ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ
ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል:: ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ "የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ" ይላቸዋል::
እላችሁአለሁ: እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል:: " (ሉቃ. 15:3-7)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ተወሰደ:- ዝክረ ቅዱሳን
28 views17:08