Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን! ወርኃ ሰኔ ቀን ፳፱ (29) | ✝የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ⛪️ቤተ ክርስቲያን 📖ሥርዓት እና 📜አስተምህሮ (Ethiopian Orthodox Tewahdo church Ethics & Teaching ☑️

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ:: አሜን!

ወርኃ ሰኔ
ቀን ፳፱ (29)

እንኩዋን ለቅዱሳን ነገሥታት "ማርቆስ እና ቴዎድሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ::

=>ማንኛውም ሰው
¤ቢጾም ቢጸልይ
¤መልካም ቢሠራ
¤ለእግዚአብሔር ቢገዛ
¤አልፎም ቢመንን ይደነቃል:: ይሕንን ሥራ ንጉሥ ሆነው ስለ ሠሩትስ ምን እንላለን? ማድነቅ የሚለው ቃል የሚገልጸው አይመስለኝም::

¤ወርቅና ብር በእግር እየተረገጠ
¤የሚበላውና የሚጠጣው ተትረፍርፎ ሳለ
¤አገር ምድሩ እየሰገደላቸው
¤ሁሉ በእጃቸው
¤ሁሉም በደጃቸው ሳለ...
ይህንን ሁሉ ስለ #ክርስቶስ ፍቅር የተውትን ጻድቃን ነገሥታት የክብር ክብር ይገባቸዋል:: ከእነዚህ መካከል ዛሬ የሚከበሩትን 2ቱን እናዘክር::

" ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም "

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቅዱስ ጻድቅ: የዋህ: ንጹሕና ገዳማዊ ብላ ትጠራዋለች:: ሮም እንደ ዛሬ ጠባብ ከተማ ሳትሆን ዓለምን በክንዷ ሥር ቀጥቅጣ የምትገዛ ኃያል ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ማርቆስ የልዑላኑ ቤተሰብ ነውና በሮም ተወልዶ በእመቤታችን ቤተ መቅደስ ውስጥ አድጉዋል::

+የየዕለት ሙያው ጾምና ጸሎት: መጻሕፍትንም መመልከት ነበር:: ነባሩ ንጉሥ ሲሞት መሣፍንቱ ቅዱስ ማርቆስን በድንግልናው ገና ወጣት ሳለ በዚያች ታላቅ ሃገር ላይ አነገሡት:: ንጉሥ ቢሆንም ሙሉውን ሌሊት በእመቤታችን ፊት ሲጸልይና ሲያለቅስ ያነጋ ነበር::

+ስለ ፍቅርም ድንግል ማርያም ተገልጻ "ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለችው:: ቅዱስ ማርቆስም "ለሕዝቡ ፍቅር አንድነትን ሰላምን ስጪልኝ:: እኔ በማስተዳድርበት ቦታ ሁሉ ጠብ ክርክር ይጥፋልኝ:: ፍቅር ይንገስልኝ" ሲል መለሰላት:: ድንግል እመቤታችንም "እንደ ቃልህ ይሁን" ብላ አጋንንት ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ ከለከለችለት:: በዚህም ቅዱስ ማርቆስ ከነገሠ ጀምሮ ለ5 ዓመታት ጠብ ክርክር: ክፋትና ችግር አልነበረም:: ሁሉም ተፋቅሮን ያጸና ነበር እንጂ::

+ከ5 ዓመታት በሁዋላ ግን ሕዝቡና ሹማምንቱ ተሠብስበው አንድ ነገርን መከሩ:: #ቅዱስ_ማርቆስን አጋብተው ለብዙ ጊዜ እንዲመራቸው ማለት ነው:: ምክንያቱም አኗኗሩ እንደ መነኮሳት ነውና ጠፍቶ እንዳይሔድ በመስጋታቸው ነው:: ከዚያም የሕዝቡ አለቆች ተመርጠው ሃሳባቸውን አቀረቡለት:: እርሱ ግን ጭንቅ ሆነበት:: ጭራሹኑ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መጥቶበት አያውቅም::

+"እስኪ በጸሎት ላስብበት" ብሎ መለሳቸው:: እነርሱ ግን ወደውታልና ድጋሚ ተሰብስበው ሌላ ነገርን መከሩ:: እርሱ ሳያውቅ መልካም ሴት መርጠው: ሥርዓተ ተክሊል አዘጋጅተው: ድግሱንም አዘጋጅተው በግድም ቢሆን ሊያጋቡት ቆረጡ:: ቅዱስ ማርቆስ የተደረገውን ሁሉ ፈጣሪ ገልጦለት በጣም ደነገጠ::

+ፈጥኖ ወደ #እመ_ብርሃን ስዕል ቀርቦ አለቀሰ:: "#እመቤቴ! እኔ ካንቺ ጋር እንጂ ከዚህ ዓለም ጋር መኖር አልችልም" አላት:: እመ ብርሃን ከሰማይ ወደ እርሱ ወርዳ "የምነግርህን ስማኝ:: በሌሊት ተነስተህ ወደ ማሳይህ በርሃ ሒድ" ብላው ተሠወረች:: ቅዱስ ማርቆስ ደስ እያለው የንግሥና ልብሱን ጥሎ: ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ በሌሊት ከቤተ መንግስቱ ወጣ::

+ወደ ሁዋላ አልተመለከተም:: እመቤታችን እየመራችው #ደብረ_ቶርማቅ የሚባል በርሃ ውስጥ ባሕር ተከፍሎለት ገባ:: ሕዝቡ መልካም እረኛ መሪን አጥቷልና በሮም ከተማ ታላቅ ለቅሶና ሐዘን ተደረገ:: ቅዱስ ማርቆስ ግን በደብረ ቶርማቅ በጾም: በጸሎትና በተጋድሎ ማንንም ሳያይ ለ60 ዓመታት ኖረ::

+በዚህች ቀንም ዐርፎ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሒዷል:: ሥጋውን የሚቀብር አልነበረምና ከሰማይ 12ቱ ሊቃነ መላእክትና 12ቱ ሐዋርያት ወረዱ:: በዝማሬ ሲገንዙትም በድኑ ከመሬት 5 ክንድ ከፍ ብሎ ተንሳፈፈ::
መላእክቱና ሐዋርያቱም በማሕሌት እዚያው ደብረ ቶርማቅ ውስጥ ቀብረውታል::

"ቅዱስ_ቴዎድሮስ ንጉሠ ኢትዮዽያ "

በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት #ጻድቁ_ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል:: በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን (1845-1860) ነው:: በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው::

+ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ #ዐፄ_ዳዊት (#ግማደ_መስቀሉን ያመጡት) እና የተባረከችው ሚስታቸው #ፅዮን_ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ #ዘርዐ_ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው::

+በኢትዮዽያ ለ3 ዓመታት (ከ1396-1399) ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን
¤ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል: ፍርድ እንዳይጉዋደል ይታትር የነበር:
¤ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር:
¤ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ:
¤ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር::

+ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር:: በነገሠ በ3 ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል:: ከመቃብሩም ላይ ጸበል ፈልቁዋል::

=>ቸር አምላክ መልካም መሪ ለሃገራችን: በጐ እረኛንም ለነፍሳችን ያድለን:: ከቅዱሳን ነገሥታቱም ጸጋ በረከትን ይክፈለን:: አሜን!


ሰኔ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም (ጻድቅ: ንጹሕና ገዳማዊ)
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ኢትዮዽያዊ (ፍልሠቱ)
4."7ቱ" ቅዱሳን መስተጋድላን (አባ አብሲዳ: አባ ኮቶሎስ: አባ አርድማ: አባ ኒኮላስ: አባ ሙሴ: አባ እሴይ: አባ ብሶይ)
5.ቅዱሳን አባ ሖር: አባ ብሶይ: አባ ሖርሳና እናታቸው ቅድስት ይድራ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት

1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

ንባብ

" አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::
በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል::
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው::
የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም::
በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::
ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ::
ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም::
ለረጅም ዘመን ለዘለዓለሙ::
በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: " (መዝ. 20:1-5)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ቅዱሳን