2022-02-07 19:26:19
ሐዋርያው ጳውሎስ እርግማን / Anathema / ανάθεμα የሚለውን ቃል በተለያየ መልኩ የተጠቀመበት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ይመስሉኛል - በተለይ በወንጌል አገልጋዮች ዘንድ።
#አንድ
ገላትያ 1 ፡ 8
ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
ይሄ “እርግማን” የሚያሳየን ሐዋርያው ጳውሎስ ለሚያገለግለው ወንጌል ምን ያህል እርግጠኛና አይበገሬ እንደሆነ ነው፡ ሌሎች ሰዎች ቢሆኑ ወይም እኛው ራሳችን ተመልሰን ሌላ ወንጌል ብንሰብካችሁ፣ ካስፈለገም ከሰማይ መልአክ አንዱ እኛ አስቀድመን ከነገርናችሁ ወንጌል ያፈነገጠ ቢነግራችሁ “የተረገመ” ይሁን ይላል።
የሚሰብከው ወንጌል ከሌሎች፣ ከራሱም፣ እንዲሁም ከሰማይ መልአክት ሁሉ የሚበልጥ ነው።
ወንጌል ዛሬ በመድረኮቻችን ላይ እንዴት ነው?
#ሁለት
ሮሜ 9 ፡ 3
በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና።
ይሄኛው “እርግማን” የራሱን የጳውሎስን በስጋ ዘመዶቹ ስለ ሆኑት ስለ እስራኤላውያን ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽ ነው፡ እነርሱ ይድኑ ዘንድ እኔ ከክርስቶስ ተለይቼ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበር ነው የሚለው፡ This was not his wishful thinking. He literally prayed that he may be accursed.
የሚያገለግለው ወንጌል ከተለመደውና ከምናውቀው የተለየ ፍቅር ውስጥ የሚወጣ ነበር፡ የሚያገለግለው ሰሞነኛ ስለሆነ ሳይሆን ከፍቅር በመነጨ ልብ ነበር፣ ለዛውም የሌሎችን እርግማን ለመሸከም እስኪመርጥ ድረስ።
የወንጌል አገልግሎታችንና ቅናታችን ዘንድሮ ከየት ነው የሚመነጨው?
What is our driving force today to proclaim the gospel?
#ሦስት
1ኛ ቆሮ 16 ፡ 22
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን።
ለጳውሎስ እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደድ የለም፣ ይህን ጌታ የማይወድ ሁሉ “የተረገመ” ይሁን ነው የሚለው፡ ለዚህ ጌታ ያላደረና ያልተገዛ ከእርግማን በታች ይውደቅ ነው የሚለው፡ ኢየሱስን ከማንምና ከምንም በላይ አድርጎት ነበር ያገለገለው፡ ሰዎች እርሱን እንዲወዱት ሳይሆን የሚያበረታታቸው ሁሉም ጌታ ኢየሱስን እንዲወዱ ነበር የሚጋብዘው።
በመድረኮቻችን ላይ የምናገለግላቸው ሰዎች ማንን እንዲያስቡ፣ እንዲከተሉና እንዲወዱ ነው የምናደርገው?
#ማጠቃለያ፡-
ጳውሎስ ግድ የሚሰኝበትን ወንጌል ሰዎችን በመውደድና ሰዎችም ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲወዱ በመጋበዝ ነበር ያገለገለው።
እውነት ለመናገር ያስፈራል፣ ምክንያቱም እንዲህ ለማለት ማናችንም አቅም ያለን አይመስለኝም።
የወንጌል አገልጋይ ሆኖ ይህን ለማስተማር ወይም ለመተንተን
ሳይሆን በእውነት ከልቡ ለማለት አቅም ያለው ሰው ብጹዕ ነው።
መድረኮቻችን በዚህ እውነት ሲፈተሹ እንዴት ይሆኑ?
#እንጸልይ፦
አቤቱ ለአንተና ለሰዎች ካለን ፍቅር ያልሰረጸ አገልግሎት
ቤተክርስቲያንን ታደጋት
አቤቱ ለታይታና የራስን ስም ለመትከል ከሚደረግ ሩጫ
ቤተክርስቲያንን ሰውራት
አቤቱ በንግግር ችሎታ እንጂ በፍቅር ካልታጀበ የመድረክ ትወና ቤተክርስቲያንን አድን
___
yilu danu
| @nAZRAWI_tUBE || @nAZRAWI_tUBE |
| @nAZRAWI_tUBE || @nAZRAWI_tUBE |
192 views16:26