2022-12-05 00:00:24
+++ እርሷ መድኃኒታችሁ ናትና!!" +++
(በትዕግሥት ሆነው ያንብቡት፣ ለሌላውም በማጋራት ሃይማኖታዊ ግዴታዎን ይወጡ)
ከጻድቁ አቡነ ተክለሃማኖት በረከት ያሳትፈን!!
ላለመማርና ላለማወቅ አእምሯቸውን አሳልፈው የሰጡ ኦርቶዶክሳዊነትንና ኦርቶዶክሳውያንን አምርረው የጠሉ ሰዎች "ድንግል ማርያም ምክንያተ ድኂን እንጂ መድኃኒት አትባልም" ሲሉ ለይቶላቸው ጸረ ማርያም የሆኑቱ ደግሞ ጥቅሶችን ከዓውድና ከተነገሩበት ዓላማ ውጭ በመጥቀስ "ማርያምን መድኃኒት ቤዛ አድኝን" አትበሏት ብለው በአፍም በመጽሐፍም ይናገራሉ:: ኦርቶዶክሳውያን ድንግል ማርያምን "መድኃኒት፣ ቤዛ" ብለን ስንጠራት በውስጥም በአፋ ያሉ ብዙዎች ባልተረዱት ባላወቁት ባልመረመሩት ነገር እርሷን ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያተካከልናት በእርሱ የማዳን ዙፋን ያስቀመጥናት አድርገው ያስባሉ ይናገራሉም:: ከዚያም አልፈው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ የተንሸዋረረ እውቀትና እምነት እንዳለን አድርገው በሌሎች ዘንድ ያጠለሹናል:: ኦርቶዶክሳውያን ያዳነን ማን እንደሆነ ከምን እንዳዳነን ለምን እንዳዳነንና በማዳኑም ሥራ ውስጥ ማዳኑ የተፈጸመለት የሰው ልጅ ሱታፌና ድርሻ ምን መሆን እንደሚገባው ቤተክርስቲያን ታስተምረናለች:: ድንግል ማርያምና ቅዱሳኑን በመንቀፍና በመጥላት ስለ እነርሱም ላለመናገር ዳተኛ በመሆን ለክርስቶስ ያለኝን "ፍቅር" እገልጻለሁ ብሎ መድከም ምንኛ አለመታደል ነው ? ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች የ"ፓስተሮቻቸውን የ"መጋቤዎቻቸውን" የ"ነቢያቶቻቸውን" የ"ያድናሉ" መልእክት በፖስተር በብሮሸርና በትላልቅ " ባነሮች" እየለጠፋ ወደ የመስብሰቢያ አዳራሾቻቸው ሰዎችን ይጋብዛሉ : በየጉባኤዎቻቸውም የሚያምኑበትን የራሳቸውን ትምህርት ከማስተማር ይልቅ ኦርቶዶክሳዊነትን እያጨለሙና እያጠለሹ የሌለ ስም እየሰጡ ይሰብካሉ :: ኢየሱስ ክርስቶስ ከምንና ለምን አዳነን? እርሱ ካዳነን ከእኛ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ሀሳቦች ማየቱ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ለጊዜው አቆይተነው ወደ ነጥባችን እንመለስ :-
+++ ድንግል ማርያም መድኃኒት አትባልምን ? +++
መልሱ ግልጽ ነው::መድኃኒት ትባላለች:: እርሷ መድኃኒት ማለታችን ግን ከክርስቶስ ጋር አስተካከልናት ማለት አይደለም ሊሆንም አይችልም::በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ብርሃን ተብሏል ቅዱሳንም ብርሃን ተብለዋል:: (ማቴ 5:14 ዮሐ 5:38፣ 8:12) እናስተውል እርሱን ብርሃን ስንለውና እነርሱን ብርሃናት ስንላቸው አንድ አይደለም:: እርሱን ብርሃን ስንለው ቃሉ እንደ አምላክነቱ ይረቃል ይመጥቃል ይረቃልም:: እነርሱን ብርሃናት ስንላቸውም እንደ ማዕረጋቸው እንደ ቅድስና ደረጃቸው ነው። (ማቴ 13: 8 1ቆሮ 15:41) ያ ባይሆን ቅዱስ መጽሐፍ ክርስቶስንም ብርሃን አገልጋዮቹንም ብርሃን በማለቱ እርሱንና ቅዱሳኑን አፎካከረ ያሰኝ ነበር:: ወዳጆቹን ብርሃናት ማለት የእርሱን ብርሃንነት መካድ አይደለም:: እርሱ እንደውም የብርሃናት (የቅዱሳን) አባት ተብሏል:: (ያዕ 1:17) ይህን እንደ መነሻ ካልን እርሷ መድኃኒት መባል እንደሚገባት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን በንጽጽር እንመልከት::
+++ ቤዛ እስራኤል ቤዛዊተ ዓለም +++
በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣ በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ ለሕዝቡ ቤዛ የሆነ ጠላቶቻቸውን የጣለ እርሱ እግዚአብሔር ነው::እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ሲያወጣ ነፃ ካወጣቸውም በኋላ የነፃነት ጉዞ ሲያደርጉ መላእክት ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን እንደሚመራቸው ተነግሯቸው ነበር:: (ዘጸ 14:19 ዘጸ 23:20) በዚህ ነጻ የመውጣት ጉዞ ውስጥ ታላቅ ሚናና ድርሻ የነበረው ሰው መስፍኑ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነበር :: ሕዝቡን ይመራና ያስተዳድር ስለእነርሱም ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ነበር:: (ዘጸ 32:32) በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር የሆኑት እስራኤላውያን "የሙሴ ሕዝብ" ሲባሉ ሙሴም በፈጣሪው "የሕዝቡ ነፃ አውጪ" ተብሏል:: (ዘጸ 32:7-8) እስራኤል እግዚአብሔርን ባሳዘኑት ጊዜ ሙሴ ስለ እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ነበር:: (መዝ 105:23) ከዚህ ሁሉ የተነሳ እግዚአብሔር ሙሴን ምክንያት አድርጎ ሕዝቡን ከባርነት ነጻ ስላወጣቸው ሙሴ "የእስራኤል ነፃ አውጪና ቤዛ" ተብሏል:: (ዘጸ 32:7-8፣ የሐዋ 7:35) ይህንም መጽሐፍ ሲመሠክር " ይህ ሰው (ሙሴ) በግብጽ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው" ብሏል :: (የሐዋ 7:36)
እስቲ ጥያቄ እናንሣ እስራኤልን ነፃ ያወጣ ማነው? ሙሴ እንዴት ነፃ አውጪ ተባለ? የእስራኤል ቤዛ ማነው? ሙሴ እንዴት የእስራኤል ቤዛ ተባለ? እስራኤል የማን ሕዝብ ናቸው? የእግዚአብሔር የሆኑት ሕዝቡ እንዴት የሙሴ ሕዝብ ተባሉ? ሙሴ በሕዝቡ መካከል ድንቅና ምልክት ካደረገ "ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ድንቅና ምልክቶችን አድርጋለች።" ተብሎ ሲነገር "ይህማ አይሆንም!" ብሎ ሽንጥ ገትሮ መከራከርን ምን አመጣው? (ማር 16:17 ዮሐ 14:15 ::) በሐዲስ ኪዳን ግብጽ የሲኦል እስራኤላውያን የምእመናነ ሐዲስ ጉዟቸው የጉዟችን የገጠሟቸው ፈተናዎች የፈተናዎቻችን ምሳሌዎች እንደሆኑ ተነግሮናል:: (1ቆሮ 10:1-5) በሙሴ ምስፍና እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ነፃ እንዳወጣ ከእርሷ ከድንግል ማርያም በነሳው (በተዋሐደው) ሥጋ እኛን ከሰይጣን አገዛዝ ከሲኦል ባርነት ነፃ አውጥቶናል:: (ዕብ 2:14-16 1ጴጥ 3:19 ዮሐ 1:14-15) በሙሴ ተልእኮ እስራኤል ከግብጽ ወጡ ከድንግል በነሳው ሥጋ ዓለም ከሲኦል ነፃ ወጣ:: በሙሴ ተልእኮ ፈርኦን ተሸነፈ ከድንግል በተዋሐደው ሥጋ በፈጸመው የማዳን ሥራ ዲያብሎስ አፈረ በመስቀሉም ተጠረቀ:: (ቆላ 2:14-16) እስራኤል ከሥጋ ባርነት ከፈርኦን አገዛዝ ነፃ ከወጡበት መንገድ ዓለም ከነፍስ ባርነት ከሰይጣን አገዛዝ የዳነበት መንገድ ይበልጣል :: በእርሱ ምክንያት በተፈጸመው እስራኤልን ነጻ የማውጣት ጉዞ ሙሴ ቤዛ ነጻ አውጪ ከተባለ በድንግል ማርያም በተፈጸመው የማዳን ሥራ ቤዛዊተ ዓለም ብትባል ምን ያንስባታል? እራሷ " ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ ( ማዳኑን ) አድርጓልና።" እንዳለች (ሉቃ 1:49-50)
+++ እርሷ መድኃኒታችሁ ናት +++
በተአምረ ማርያም መቅድም ከሠፈሩ እመቤታችንን እንድንወዳት ከሚያስገነዝቡን ኃይለ ቃላት አንዱ "ውደዷት እርሷ መድኃኒታችሁ ናት" ይላል:: እንግዲህ ይህን አንብበው ነው ሰዎቹ ለምን እንዲህ ትላላችሁ ብለው እንደ ጥህሎ ሊውጡን እንደ እንቀት ሊጠጡን የሚነሥሡብን ሳይመረምሩና ሳይገነዘቡም የሚተቹን :: እነዚህ ክፍሎች እርሷን እንዴት መድኃኒት ትሏታላችሁ? ብለውም ጉንጭ አልፋ መከራከርያ ያነሣሉ:: እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት አዳኝ ነው:: ማዳን የባሕርይው የሆነ እርሱ የወደዳቸውን በፍጹም ልባቸው ያመለኩት ወዳጆቹን ምክንያት አድርጎ በልዩ ልዩ መንገድ ማዳኑን ስለገለጠባቸው መድኃኒት አዳኝ እንዲባሉ ፈቀደ ያድኑም ዘንድ የማዳኑን ጥበብ ገለጠላቸው ኃይሉንም አስታጠቃቸው መንገዳቸውንም አቃና:: እስቲ የሚከተሉትን ለግንዛቤ እንመልከት
42 viewsMIKIYAS DANAIL, 21:00