2022-08-05 00:02:52
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የነገረ መለኮት መግቢያ
የመጽሐፉ አዘጋጅ፦ መምህር ግርማ ባቱ
የመጽሐፉ የገጽ ብዛት፦ 290
የመጽሐፉ ዋጋ፦ 170 ብር
የኅትመት ዘመን፦ 2012 ዓ.ም
መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች የተዘጋጀ ነው። የመጽሐፉን መቅድም ያዘጋጀው በመጻሕፍት መቅድም እና መግቢያ ላይ የማናጣው መምህር ብርሃኑ አድማስ ነው። መምህር ብርሃኑ በመቅድሙ ላይ "መልካም ነገር እነሆ" በሚል ርእስ በማቴዎስ ወንጌል 19፥16-17 ያለውን ኃይለ ቃል በማንሳት ስለመልካምነት ካብራራ በኋላ የመጽሐፉን መልካምነት እንዲህ ሲል ያውጃል፦ "የመምህር ግርማ መጽሐፍ፣ በምንጩ፣ በትምህርቱና በምሥጢሩ መልካምነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በአቀራረቡ ደግሞ በዘመናችን ያለውን የጥናት ወይም የምርምር መንገድ የተጠቀመ መሆኑን መርሣት ተገቢ አይደለም።"
የመጽሐፉ መግቢያ የተዘጋጀው የመጽሐፉ ጸሐፊ በሆኑት በመምህር ግርማ ባቱ ነው። መምህር ግርማ በመግቢያቸው ነገረ መለኮት የምሥራቅ እና የምዕራብ እየተባለ የሚከፈል መሆኑን እና ከምሥራቁ ወገን እኛን ኦሪየንታሎችን ጨምሮ እነ ግሪክ፥ ሩሲያ እና የመሳሰሉት ሲገኙበት በምእራቡ ወገን የሮማ ካቶሊክና እና ልጇ ፕሮቴስታንት እንደሚገኙ ይነግሩናል። እንዲሁም የእኛን የምሥራቁን ነገረ መለኮት "ተማህልሎአዊ" የሚል ሀገራዊ ሥያሜ ይሰጡታል። ይሄም Mystical, Apophatic, Negative Theology የሚባሉት የሚተካ ነው። ተማህልሎአዊ መንፈሳዊነትን እና ምሥጢራዊነትን አስተባብሮ የያዘ መገለጫ ነው። በምናውቀው ምሥጢራዊ እውቀት እና በምንኖረው መንፈሳዊ ሕይወት መካከል ምንም የተሠመረ ድንበር የለም።
ይሄም በሊቁ Viladmir Lossky አገላለጥ ሲገለጥ "The Eastern Tradition has never made a sharp distinction between mysticism and theology; between personal experience of the divine mysteries and the dogma affirmed by the Church."
ተማህልሎአዊ ያሰኘውም እንዲህ ዓይነቱ የነገረ መለኮት ሕይወት ነው። መምህር ግርማ እንዲህ ዓይነቱን ነገረ መለኮት ከምዕራቡ ክርስትና የተሠወረ ነው በማለት በምሥራቅ እና በምዕራቡ የክርስትና ዓለም ያለውን የነገረ መለኮት አቀራረብ(Theological Approach ) ልዩነት በመጠኑ ይነግሩናል።
የኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት(Mystical Theology) ትሑት፥ ተማህልሎአዊ፥ አሉታዊ(Negative)፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፥ ከጥንታውያን የቤተክርስቲያን አባቶች አስተምህሮ፥ ሕይወትና ጽሑፎቻቸው ጋር የተመሳከረ (patristic) እና ባለ ብዙ ምንጭ ነው። በማለት የምሥራቁን የነገረ መለኮት የአቀራረብና የአረዳድ ምሥጢራዊነት ይገልጹታል።
ይሄን Kallistos Ware እንዲህ ይገልጹታል "Orthodox Theology is less systematic and more Mystical in its approach"
የምዕራቡ የነገረ መለኮት አቀራረብ ደግሞ ሳይንሳዊ፥ ፍልስፍና መር፥ አዎንታዊ(cathaphatic) ማለትም ከሰው አቅም በላይ የሆኑትን መለኮታዊ ምሥጢራት ጭምር ደፍሮ የሚበይን እና በአጥኚው ግለሰብና በሚጠናው እውነት መካከል የአጥኚና የተጠኚ ግንኙነት(subject - object relationship) የፈጠረ ነው።
በማለት በሁለቱ የነገረ መለኮት አቀራረቦች መካከል ያለውን ልዩነት ይነግሩንና ከሁለቱ መካከል ኦርቶዶክሳዊ የሆነውንና መጽሐፉም የቀረበበትን ተማህልሎአዊውን ነገረ መለኮት በመግቢያችው በደንብ ያስተዋውቁናል።
የመጽሐፉ የመጀመርያው ምዕራፍ ተማህልሎአዊ ነገረ መለኮት(Mystical Theology) በሚል ርዕስ ይጀምራል። በዚህ ርዕስ ሥር ልክ እንደ ኦሪቱ የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለሀለዎተ እግዚአብሔር (Existence of God) በመናገር ይጀምራል።
"ክርስቲያናዊ ነገረ መለኮት በሀልዎተ እግዚአብሔር ላይ ባለ ፍጹም እምነት ይጀምራል" በማለት በኦርቶዶክሳዊው በነገረ መለኮት ትምህርት ሀለዎተ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ቦታ ይዳስሳል። እንዲሁም በሀልዎተ-እግዚአብሔር ዙሪያ ያሉት አመለካከቶች ማለትም አማኒነት(Theism) ኢ-አማኒነት(Atheism) እና ኢ-ታዋቂነት(Agnosticism) በመጠኑ ይዳስሳል። በተጨማሪ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ "የነገረ መለኮት አረዳድ እና ብያኔ በዘመናችን"ና "ዕውቀት እና ነጽሮተ እግዚአብሔር" የሚሉ ሁለት ንዑሳን ርዕሶች ተዳሰውበታል።
በምዕራፍ ሁለት የነገረ መለኮት ምንጮች(Sources of Theology) በሚል ርዕስ እግዚአብሔር በተለያየ መልክ እና ጎዳና እራሱን ለሰው ልጆች በአቅማቸው ልክ የገለጠላቸውን መገለጦችን የነገረ መለኮት ምንጮች አድርገን የምንጠቀም መሆናችንን የሚዳስስ ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ የእግዚአብሔር መገለጥን (Revelation) በሁለት መከፈላቸውን እነርሱም አጠቃላይ መገለጥ(General Revelation) እና ልዩ መገለጥ(Special Revelation) እንደሚሰኙ ይገልጣል። አጠቃላይ መገለጥ(General Revelation) የሚባሉትን፦ የግዑዙ ዓለም ተፈጥሮ(physical Nature)፥ የሰው ተፈጥሮ(Human Nature) እና ታሪክ(History) እንዲሁም ልዩ መገለጥ(Special Revelation) ተዳሰዋልን። በተጨማሪም የነገረ መለኮት ምንጮች የሆኑትን ትውፊትን(Tradition) መጽሐፍ ቅዱስ(The Holy scripture) የአባቶች ትምህርት ፥ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ውሳኔዎች፥ ሥርዓተ አምልኮ(Liturgy), ፥ ምሥጢራት(sacraments) የሚባሉት የኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ምንጮች በስፋት ታይተዋል።
ምዕራፍ ሦስት በመጽሐፉ ሰፊውን ሥፍራ የያዘ ምዕራፍ ነው። ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሰብእ በሚል ርዕስ ሰው በኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት እንዴት ይታያል የሚለውን እያነሳ በተቀራኒው ያሉትን ፍልስፍናዊ እና ሳይንሳዊ እይታዎችን በምሥራቃዊ የነገረ መለኮት መነጽርነት ይተቻቸዋል። በተጨማሪም ለኦርቶዶክሳዊው ነገረ ሰብእ(Orthodox Anthropology) መሠረት የሆነውን የእግዚአብሔር አርያና አምሳል የሚሉ አሳቦችን ሕሊና አበውን በመጠቀም ኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት የትክክለኛው ሰብአዊ ክብር ምንጭ መሆኑን ይነግረናል። እንዲሁም ነገረ ሰብእ በነገረ ክርስቶስ(Christological Anthropology), ፥ ወላዲተ አምላክና ነገረ ሰብእ(Theotokos and Anthropology)ና ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን እና ነገረ ሰብእ በሚሉ ርዕሶች አማካኝነት ከጥንተ ተፈጥሮ ጀምሮ የእግዚአብሔርን አርአያና አምሳል ይዞ ከመፈጠር፥ በእመቤታችን ምክንያትነት በምሥጢረ ሥጋዌ እንዲሁም በምሥጢረ ጥምቀት እና ቁርባን፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ፍጹም ማንነትን መሠረት በማድረግ ኦርቶዶክሳዊው ነገረ ሰብእ በስፋት እና በጥልቀት ተዳሷል።
የመጨረሻው ምዕራፍ ማኅበራዊ- አከባበያዊ ነገረ መለኮት(socio-Ecological Theology) በሚል ርዕስ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ባለ ምሥጢራዊ ኅብረት እንደጠበቀ ከሰው ጋር እና ከተቀረው ፍጥረት ጋር እንዴት ያለ ጤናማ ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ "ሰው ከሰው" እና ነገረ መለኮትና ሥነ ምሕዳር በሚሉ ንዑሳን ርእሶች አማካኝነት ይዳስሳል። ለዚህ ጤናማ ማኅበራዊ እና ሥነ ምኅዳራዊ ግንኙነት የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ምን ያህል ለሀገር አስተዋጽኦ እንዳደረገና የጋራ የሆነ አገራዊ ስሜትን ከመፍጠር እና በየገዳማቱ ያሉትን የተፈጥሮ ጥበቃዋን እያነሳ የቤተክርስቲያኒቱ ባለውለታነት አሰምቶ
138 viewsMIKIYAS DANAIL, 21:02