Get Mystery Box with random crypto!

መጽሐፉ ርዕስ፦ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ(ከጥንት - 6ኛ ክፍለ ዘመን) ቅጽ 1 የመጽሐፉ አዘ | ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA

መጽሐፉ ርዕስ፦ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ(ከጥንት - 6ኛ ክፍለ ዘመን) ቅጽ 1
የመጽሐፉ አዘጋጅ፦ መምህር ግርማ ባቱ
የመጽሐፉ የገጽ ብዛት፦ 448
የመጽሐፉ ዋጋ፦ 390
የኅትመት ዘመን፦ 2014 ዓ.ም
መምህር ግርማ ባቱ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥነ መለኮት(theology) ሰርተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም(Addis Abeba Institute of Ethiopian Studies) በባህል ጥናት(cultural studies) እና ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደግሞ በሥነ መለኮት (theology) ሰርተዋል፡፡ በሕንድ ሀገር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እያጠኑ(ያጠኑ?) ሲሆን፣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት መግቢያና (Introduction to Theology) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ እኚህ በሁለት እጅ የማይነሱ ታላቅ መምህር በቅርቡ የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ አበርክተውልናል። የኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክ በተለያዩ ዕይታዎች ማለት አውሮፓ ተኮር ዕይታ(Eurocentrism) ፥ አፍሪካ ጠል ዕይታ(Afrophobia) እንዲሁም ግብፃዊ የታሪክ ዕይታ ብዙ ዱላ የበዛበትን ታሪክ እሳቸው መነጽሩን በማስተካከል ወደ በኢትዮጵያ ተኮር ዕይታ(Ethiocentric) በዕይታና የራስን ተልዕኮ በመያዝ የኢትዮጵያን ታሪክ ወተቱን አጥቁረው ላቀረቡልን ምዕራባውያን እና የሀገር ቤት የታሪክ ጻፊዎች "እውነቱ ይሄ ነው" እያሉ በማስረጃና በመረጃ ቁጭ ብድግ እያደረጉ ይሞግታሉ። የኢትዮጵያን የታሪክ ምንጮች የመተርጎም ሥልጣን ኢትዮጵያዊ የታሪክ ዕይታ(Ethiocentric) ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንጂ አውሮፓውያን ወይም ጥሙቅ አውሮፓውያን አይደሉም መሆንም የለባቸውም እያሉ በምሬትና በቁጭት ይነግሩናል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቦቿም ሕዝበ እግዚአብሔር የሆኑ ቅድስት ሀገር መሆኗን ከሕገ ልቦና ወደ ሕገ ኦሪት እንዲሁም ሕገ ወንጌል የተቀበለች በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የመሠረተች መሆኗን የሕገ ኦሪት የአምልኮ ሥርዓት ማሳያዎችን እንደ ታቦተ ጽዮን፥ ግዝረትን፥ የቀዳሚት ሰንበትን አከባበር የምግብ ሥርዓታችንን(የሚበሉና የማይበሉ)ና የሕንፃ ቤተክርስቲያን አሠራራችንን እያነሱ ያስረዱና። ማን እንደተከለው የማይታወቅ "ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለች 4ኛው ክፍለዘመን ነው" እያሉ ብዙዎች ለሚጮኹት ከንቱ ጮኾት በመጻፋቸው "4ተኛው ክፍለዘመን ላይ የተደረገው ለውጥ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት የሆነበት እንጂ የገባበት ተደርጎ ሊነገር አይገባም" እያሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ሦስት ዓበይት ክፍሎች እንዳሉት እነርሱም፦ ክርስትና የተዋወቀበት(የጃንድረባው ባኮስ) ፥ ክርስትና የተደራጀበት(የቅዱስ ፍሬምናጦስ)ና ክርስትናው የተስፋፋበት(የዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት) በማለት አስፍተው አምልተው ምንጭ እየጠቀሱ ክርስትናው ከኢትዮጵዊው ጃንደረባ የሚጀምር መሆኑን ጮኾቱን ከንቱ ያሰኙታል ። እንዲሁም በቤተክርስቲያን መምህራን ሳይቀር ትኩረት ያልተሰጠውን እንዲሁም "በኢትዮጵያ ወንጌልን ሰበኩ ብሎ የሚመካ ሐዋርያ" የለም ተብሎ የተካደውን የቅዱስ ማቴዎስን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መስበኩንና ማስተማሩን በማስረጃ ያስረዳሉ ይሞግታሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ወርቃማው ዘመን ውስጥ የዐፄ ካሌብን ወደ ናግራን ያደረጉትን ዘመቻና ከድል መልስ የተደረገውን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያሰኝ ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር ይዳስሳል። በመቀጠል ለዘመኑ ወርቃማነት ወርቅ ሆነው ስለተገኙት ማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ ፥ ዘጠኙ ቅዱሳንና ዐፄ ገብረ መስቀል አንድ በአንድ በተናጥል እና በጋራ ለወርቃማው ዘመን ያበረከቱትን ከወርቅ የላቀ ሥራና አስተዋጽኦ ይተነትናሉ። በመጨረሻም ስለኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት እና ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዙርያ ስላደረገው ትልቅ አስተዋጽኦ ያትታል። ኢትዮጵያ የምትድነው የራሷ በሆነው ጥንታዊ ትምህርት እና ከሌሎች የተገኘውን ዕሴት ጨምሮ የራስ በማድረግ መሆኑንና ሁሉን መጣልና ሁሉን መቀበል የማይገባ ከዚህ ይልቅ የሚበጀን ወደፊት የሚያስኬደን አስተጻምሮ(synthesis ) እንደሆነ በተዋሕዶ ማክበርን መርሕ የሚከተሉትን ዶክተር እጓለን ጠቅሰው ያስረዱበትና የተረዱበት መጽሐፍ ነው። የመምህር ግርማ ባቱን የታሪክ መጽሐፍ ያነበበ(ወይም በክፍል የተማረ) ሰው የኢትዮጵያን ታሪክ ይረዳል፥ የኢትዮጵያን ታሪክ የራስ ያደርጋል፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ይኮራል፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬያችንን እያየ ይቆጫል፥ ታሪክን ለመድገም ይነሣሣል። መጽሐፉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑን በሚገባ ይገልጣል። ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ዐጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፉቸው የመጀመርያ ገጽ ላይ እውነተኛን ታሪክ ለመጽሐፍ 3 ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ።
1, ተመልካች ልቦና 2, የማያዳላ አእምሮ 3, የጠራ የቋንቋ አገባብ ብለው ይዘረዝራሉ። መምህር ግርማ እኚህን ሦስቱን ያሟሉ እውነተኛ ታሪክ ጸሐፊ መሆናቸውን በመጽሐፋቸው አስመስክረዋል። ነጋድራስ ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ልጃቸውን መምህር ግርማን እውነተኛ ታሪክ ጽፈሐልና እደግ ተመንደግ ብለው ግንባሩን ይስሙት ነበር። አስረስ የኔሰው ዶክተር እጓለ ተመሳሳዩን ያደርጉ ነበር።

እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ መረዳት ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተደረገ የመጽሐፍ ግብዣ መጽሐፉን ያንብቡ ያስነብቡ!
የመምህር ግርማ መጽሐፍ የሌለበት የመጽሐፍ መደርደሪያ ሙሉ አይሆንም መጽሐፉን በመግዛት መደርደሪያዎትን ሙሉ ያድርጉ።

የልጅ ምርቃት፦ መምህር ግርማ ሆይ የኢትዮጵያ አምላክ ግርማ ሞገስ ይስጥልኝ። የጻፈ ያጻፈ ከሚለው በረከት ያድልልን። ብዕርዎት ትለምልም። ሞትህን ከገብርኤልና ከሚካኤል ጋር ያድርገው!

ያለ ሰው ያልተወን የአባቶቻችን የቅዱሳኑ አምላክ የተመሰገነ ይሆኑ!!!