2022-07-07 19:45:07
#ጥያቄ
የት ነው ያለችው
[ኪዳ የገጠር ልጅ_ቅዱስ]
በኦሮሞ ባህል ፣በገዳ ስርዓት
ሴት ያገባች እለት
በእጇ የምትሰጥ ፣ ሲንቄ በትር አላት
ይቺ ሲንቄ ሚሏት ፣ ዘለግ ያለች በትር
የሴት ልጅ ከለላ ፣ ጠባቂ ነች ክብር
እሱን የያዘች ዕለት ፣ማን ደፍሮ ሊነካት
ማንስ ፣ ሊ ያ ስ ፈ ራ ራ ት
በግጭቶች መሀል ፣ ሲንቄዎን ከያዘች
ሁሉም አንገት ደፍቶ ፣ እንዲሄድ አረገች
የሲንቄው በትር ላይ ፣የለም አስፈሪ ጦር
በፍርሀት አርዶ ፣ ወደኀላ ሚያዞር
ታድያ አቅሟ ምንድነው?
(እምነት ብቻ!)
ሲንቄዎን ያዩ 'ለት
ምን ማለት እንደሆን ፣ ልባቸው ያውቀዋል
ስይፍ ካፎት ገብቶ ፣ ፀበኛ ይበተናል
ዱላው እንጨት ሆኖ ፣ ግዑዝ ተሰባሪ
ለእምነት ተምሳሌት ፣ ነው ሁሉን መካሪ
ሙሴ ያንን ባህር ፣ ከፍሎ ህዝቡን ሲያሻግር
በእምነት ሀይል እንጂ ፣ አይደለም በበትር
በትር በራሱ ፣ ባህር አይከፍልም
ያለ ፅኑ እምነት ፣ አያሻግርም
(ያ በትር ነው ሲንቄ! )
ሲንቄዋ የት ሄደች፣በትሯ የታለች
ምነው ከዚህ ትውልድ፣ሸሽታ ገሸሽ አለች
ይኀው በሚሊዮን
በሚቆጠር ገንዘብ
በተስኪያን ይሰራል ፣ መስጅድ ይገነባል
በዋጋ ማይገዙት ፣ የሰው ህይወት ያልፋል
እኮ ለምን?
(ሀይማኖታችን ፖለቲካ ነዋ!)
ስለ ጥበብ ደክመን ፣በዋሻ መንነን
መለኮት ለማጥናት፣ አንሻም ንዲያልበን
ሀይማኖቱ በዛ ፣ህንፃው ሽቅብ ወጣ
ታድያ ከወዴት አለ ፣ከጭንቅ ሚያወጣ?
ለአንዲት ቅርፊት እኮ ፣ አስኳሏ ነው ክብሯ
ታዲያ የሀይማኖት ቤት
ከእምነት ነፃ ሆና ፣ምነው እንዲህ ማማሯ
ቤተስኪያን ሲቃጠል
መስጂድ ሲንበለበል
ደርሰን የምንጮኀው ፣ ለወጣበት ገንዘብ
ወ ይ ስ
ሀጥዕ እና ሀጥያት ፣ ሀላል እንዲናበብ?
አየህልኝ አይደል?
ክርስቲያን ነኝ አትበል
ሙስሊም ነኝም አትበል
የኔም ያንተም እምነት ፣ማህተቡ አንድ ነው
የፖለቲካ እምነት ፣ ጠፍሮ የገመደው¡
የፖለቲካ አምላክ፣አንተ ድረስልን
ታሪክ ባህል እምነት፣አርቀህ ጣልልን
ዘላለም ዝንት አለም
አንተን አስመልከን
አንተን ብለን መጥተን
አንተው አታዋርደን፡፡
ይህ ሆነ ፀሎቱ
ቀረ ትሩፋቱ።
የት ሄደች ሲንቄዋ?
ሰው በመሆን ብቻ ፣ እምነቱ ሳይጎድለን
ጠብ ጠብ ሲሸተን ፣ገብታ ምታረግበን
የት ሔደች?!
የት ሔደች?!
የት ሔደች?!
( ኪዳ የገጠር ልጅ_ቅዱስ )
30/10/2014
@TkYEGITMABIYOT
@TkYEGITMABIYOT
@TkYEGITMABIYOT
2.7K viewsኪዳ የገጠር ልጅ ቅዱስ, 16:45