2022-04-18 17:49:55
1. ሕጽበተ እግር ይባላል።
ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው። ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው። ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡን ኃጢአት እጠብ ሲሉ ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ። / ዮሐ. 13:4-15/
2. የጸሎት ሐሙስ ይባላል።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴሴማኒ ሲጸልይ በመቆየቱ ነው /ማቴ 26:36 ፤ ዮሐ 17:1/
3. የምስጢር ቀንም ይባላል።
ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ በዚህ ዕለት ተመስርቷል። ይኸውም ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ስጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው።
~ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል። የሚቀደሰውን በለሆሳስ /በዝግታ/ ሲሆን እንደ ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም ጽናጽል ነው። ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው።
~ በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም። ሥርአተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል። ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው። በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሀ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል።
4. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።
ምክንያቱም መስዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንሰሳ ደም የሚቀርበው መስዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኀነቱ ዓለም ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው። /ሉቃ 22:18-20/ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን የአዲስ ኪዳን ነው። ከእርሱም ጠጡ በማለቱ ይታወቃል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን።
5. የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው። ራሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ በማለቱ /ዮሐ 15:15/ ከባርነት ነፃ የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ ከእግዚአብሔር ሕይወቱን በቅድስና መምርልት ይኖርበታል። እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናል። /ማቴ 26:17-19/
6. አረንጓዴው ሐሙስ ይባላል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ቦታ ስለ ጸለየ።
#ዕለተ_ዓርብ
* የስቅለት ቀን ስቅለት፣ መስቀል፣ አሰቃቀል ማለት ነው። መስቀል በቁሙ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መሰቀያ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ በማር 8:34 ወጸውዖሙ ለሕዝብ ምስል አርዳኢሁ ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ይጽልአ ለነፍሱ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀለ ሞቱ ወይትለወኒ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው። ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ ይላል።
* ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ /1ኛ ቆሮ. 1:17/ ላይ ወኢኮነ በጥበበ ነገር ከመ ኢንስዐር፤ መስቀሉ ለክርስቶስ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም ይላል።
* ጌታችን በተሰቀለ ዕለት ከስድስት ሰዓት ጅምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። /ፀሐይ ጨለመ/ ፣ እንሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተውም ከነበሩት ቅዱሳን ብዙዎች ተነሱ፤ ከትንሳኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ለብዙዎች ታዩ። /ማቴ 27:51/
* ጌታችን ለዓለሙ ያሰበውን ቤዛነት ሊፈጽም በመስቀል ላይ መሰቀሉ የሚታሰብበት ነውና ለስቅለቱ መታሰቢያ የሚሆን አጎበር ተዘጋጅቶ ከርቤ እየታጠነ ስቅለቱን የሚመለከት ምንባባት ሲነበብና ሲሰገድ ይዋላል። የሰው ልጅ በሙሉ በእግረ አጋንንት ተረግጦ ከፈጣሪው ተጣልቶ ለ5500 ዘመን በጨለማ መኖሩን ለማስታወስም መንበሩ ታቦቱ በዚህ ቀን በጥቁር ልብስ ይሸፈናሉ። ዲያቆኑም በቤተ ክርስቲያን በመዞር የሚያሰማው የቃጭል ድምጽ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅሶ አንድም ዋይ ዋይ እያሉ የተከተሉት የኢየሩሳሌም ሴቶችን ሙሾም ምሳሌ ነው። /ሉቃ 23:31/
* በዕለተ አርብ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ። አንቀጸ ገነት ተከፈተልን፣ ርስተ መንግስተ ሰማያት ተመለሰችልን፣ አባታችን አዳምም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃዶ እያልን የተድላ፣ የደስታ ምልክት ወይም መገለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቆጽለ ሆሳዕና ወይም ቄጤማ ግጫ ይዘን የምስራች እንባባላለን። /ኤፌ. 2:15-15/ ወዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናግሮሙ፣ ያለ ምሳሌ አልተናገረምና እንዳለ /ማቴ 13:34-35/ በኖኀ ጊዜም ርግብ ሐጸ ማየ አይኀ፣ ነትገ ማየ አይኅ፣ የጥፋት ውኃ ጎደለ፣ አለቀ እያለች ቅጠል ዕፅ ዘይት ይዛ ለኖኀ አብስራዋለች። /ዘፍ 8:8-11/
* ርግብ የካህናት፣ ኖኀ የምእመናን፣ ኖኀ እጁን ዘርግቶ ርግብን እንደተቀበላት ካህናትም በየመንደሩ እየዞሩ ክርስቶስ ተመረመረ ዲያብሎስ ታሰረ በማለት ቄጤማ ሲያድሉ ምእመናንም እጃቸውን ዘርግተው መቀበላቸው የዚህ ምሳሌ ነው። ስለዚህ አሁንም ቢገኝ የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየታደልን የምስራች መባባላችን ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣታቸው መታሰቢያ ነው። ይህን ቅጠል ልምላሜ ይዞ ተድላ፣ ደስታ መግለጽ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። ለዚህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ከበጎ እንጨት ፍሬን የሰሌንና የተምር ዛፍ ልምላሜ ይዛችሁ በየ አመቱ ሰባት ቀን ተድላ፣ ደስታ ታደርጋላችሁ ብሏል /ዘሌ. 23:40-44/።
~~~~~~
2. በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ቤተክርቲያናችን የምታደርገው ትውፊት/ የሐዋ.ሥራ 1:13/
* ከሆሳዕና እስከ ቅዳሜ ሥዑር ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ናቸው። ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም። በዚህ ሳምንት ውስጥ ለሚሞቱ ምዕመናን እግዚኦ ሕያዋን ይደገማልና። በሰሙነ ሕማማት መስቀል የለም። ስምንቱ የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ስለሆነ እርስ በእራስ መሳሳም፣ ሰላም መባባልና መልክዐ መልክዕ መድገም የለም። ይኸውም ይሁዳ ክርስቶስን በሰላምታ ስላስያዘው እርሱን ላለመምሰል። /ማቴ 26/
1.6K viewssara mariyam, 14:49