2022-04-18 17:49:49
+++ ሰሙነ ህማማትና ሚስጢራቱ +++
~ ከትንሳኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ህማማት ይባላል። ይኸውም በነቢዩ ኢሳይያስ ነሰአ ደዌነ ወፆረ ህማማነ፣ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል ዕኛ ተፈወስን። /ኢሳ 53:34-36/ ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተነገረው ቃል ተፈጸመ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለድኅነት ዓለም ሲል በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ለማስታወስ የወጣ ስያሜ ነው።
1. በዚህ ሳምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና በእያንዳንዳቸው ዕለታት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን።
ሰኞ
* አንጽሖተ ቤተ መቅደስና መርገም በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው። የሆሳዕና ዕለት ቢታንያ ያድራል። በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ ወበሳኒታ ወፂኦ አምቢታንያ ርኀበ ወርእየ በለስ እምርኁቅ ወባቲ ቌጽለ ወሖረ ይርአይ እመቦ ዘይረክብ ፍሬ በውስቴታ ወበጺሖ ኀቤሃ አልቦ ዘረከበ ዘእንበለ ቁጽል ባህቲቱ እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለበለስ፣ ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ ዓይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳችም ፍሬ አላገኘባትም፤ ወአውሥአ ወይቤላ ለዓለም አልቦ ዘይበልዕ ፍሬ እምኔኪ እንከ፤ ከአሁን ጅምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። / ማር 11:11-12/
*በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት። ፍሬ የተባለች ሃይማኖት ምግባር ናት። ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም። እስራኤል ህዝበ እስራኤል መባል እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት። በመርገም ምክኒያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ድግ ሰው ጠፋባት።
* አንድም በለስ ኦሪት ናት። በዚህ ዓለም ስፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት። እጸ በለስን ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት።
* አንድም በለስ ኃጢአት ናት። የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ኃጢአትም በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት። በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክኒያት ያገኘችን እዳ በደል በእርሱ ካሳነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው።
* ከዚህ በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተጸሎት፣ ቤተመስዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተምስያጥ / የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያግኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው።
* በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምዕመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሰለስት፣በስድስት ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ። በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ። ምክንያቱም የደረሰበትን መከራ ኅዘኑንና /5500/ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ህይወት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው።
#ማክሰኞ
* የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል። ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ስልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና።
* ጥያቄውም ከምድርልውያን ነገስታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ስልጣን ታደርጋለህ ? የሚል ነበር
~ ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። የየሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች ? ከሰማይ ወይስ ከሰው ? አላቸው። እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ? ይለናል። ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፤ እንደ መምህርነቱም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት። እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነግራችሁም አላቸው። ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም። ልቦናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ። ከዚህ የምንማረው የእነሱን ክፉ ጠባይና ግብር መከተል እንደማይገባን ነው።
* በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል። ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው።
#ረቡዕ
* ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል። ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጻሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ቀን ስለሆነ ነው። በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር። ምክንያቱም ወቅቱ የፈሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑ ብዙውን ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጥር ነው። በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል። / ማቴ 26:1-5 ፤ ማር 14:1-2 /
* የሐዲስ ኪዳን ካህናት ምእመናን በዚህ ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከእህልና ውኃ ተለይተው፣ መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው፣ የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ ታሪክ የሚይልወሳውንም በማንበብ እስከ ኮከብ መውጫ በጾም፤ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።
~ ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ቢሆንም እንደ ስሙ ግብሩ አልተገናኘም። ስምና ግብሩ አልተባበረለትም። እኛስ እንደ ስማችን ይሆን ግብራችን ?
* መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል። ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ህይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት ከእንግዲህ በኃጢአት ተጎድቶ ይኖር የነበረውን ህይወቴን እደዚሁ መልካም ሽቶ ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዞ በመሄድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስላቀረበች ነው።
* የእንባ ቀንም ይባላል። ይህም ይህችው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና። /ማቴ 26:6-13 ፤ ማር 14:3-9 ፤ ዮሐ 12:1 / ከዚህም እያንዳንዳችን ልንማር የሚገባን ነገር አለ። ይኸውም የራሳችንን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነው።
#ሐሙስ
* ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት።
1.4K viewssara mariyam, 14:49