2022-07-28 19:08:43
#እንኳን_አደረሳችሁ_አደረሰን
ዑራኤል ማለት ትርጉሙ "የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ (መጽሐፈ ሄኖክ 28፥13)
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ (ዕዝራ 2፥1) ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፦
✟ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡
✟ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ደሙን
ለዓለም የረጨበት ነው፡፡
✟ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና
ሐምሌ 21 ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ
ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡
የሊቀ መላእኩ ቅዱስ ዑራኤል ጥበቃው ምልጃው አይለየን አሜን!!
1.2K viewssara mariyam, 16:08