2021-02-13 20:33:12
ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ቀብሪ ደሀር ፣ ወለጋ ፣ አርሲ እና የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርስቲ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በተገኙበት በሁለተኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን 4ሺህ 311 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ጥቅምት ወር 1ሺህ 409 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል፡፡
ቀብሪ ደሀር ዩኒቨርሲቲም የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና ሌሎች የክልልል እና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 612 ተማሪዎቹን አስመርቋል፡፡
ወለጋ ዩኒቨርሲቲም 3ሺህ 398 ተማሪዎችን በወለጋ ስታዲየም አስመርቋል፡፡
አርሲ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በህክምና ስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 23 ሰልጣኞቹን በመጀመሪያ ዙር አስመርቋል፡፡
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ 2ሺህ 39 ተማሪዎቹን በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት አስመርቋል፡፡
በተያያዘም የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 576 ተማሪዎች ሲያስመርቅ፥ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ሁርካቶ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የአማራ አመራር አካዳሚ ለመጀመሪያ ጊዜ 37 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፥ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አካዳሚው ለዚህ የበቃው በሠራተኞች ድካም በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ነው ብለዋል፡፡
ወቅቱ በአንድ በኩል ትልልቅ እና አስደሳች ውጤቶች የተመዘገቡበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፈተናዎች የበዙበት ሀገራዊና ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ በቀጣይ የምትፈልገውን ከችግር መውጫ መንገድ መቀየስ ወሳኝ መሆኑንም ነዚህ ወቅት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ኢትዮጵያዊነት የማይደበዝዝ ይልቁንም በይበልጥ የሚደምቅና የሚፈካ የጋራ ማንነታችን ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
FBC
4.0K viewsአብርኆት 2021, 17:33