2022-06-20 17:14:20
ከአስተሳሰብህ ከተጣመምክ በስራህ ቀጥ ማለት አትችልም!
===========================
(እ.ብ.ይ.)
ቀናነት ቀና ያለ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ቅንነት በተንኮል ያልታጠፈ፣ በምቀኝነት ያልተቆለመመ፣ በራስወዳድነት ያልተንጋደደ ሃሳብና ምግባር ነው፡፡ የተንጋደደ ማንነት ቀጥ ያለ ሰውነትን አያስገኝም፡፡ ገዳዳ አስተሳሰብ ሕይወትን ያንጋድዳል፡፡ አንዴ ከአስተሳሰብህ ከተጣመምክ በስራህ መቼም ቢሆን ቀጥም ቀናም አትልም፡፡ የጎበጠ ማንነት፣ አንገት የደፋ ሕሊና ቀጥ ብሎ መቆም አይችልም፡፡ በሌሎች የሚዘወር ጭንቅላት የራሱ መሪ የለውም፡፡ በትንሹ ተፈትኖ የወደቅ በትልቁ ሊታመን አይችልም፡፡ ሲያስብ የተሳሳተ ምግባሩም ሆነ ተግባሩ የተሳሳተ ነው የሚሆነው፡፡ ሰው የዘራውን ያንኑ ነውና የሚያጭደው!
ታላቁ የጥበብ ሰው ሩሚ፡-
‹‹የመበላሸትን ወይም የመበከልን ተፈጥሮ ተረዳ፡፡ አንዴ ቁልፍህ ከተጣመመ ወይም ከታጠፈ መቼም ቢሆን ቁልፍህ አይከፍትም፡፡›› ይላል፡፡
እውነት ነው! ራስህን መረዳት ስትጀምር አካሄድህን ታጤናለህ፣ አስተሳሰብህን ትገመግማለህ፣ የምትከተለውን ትመረምራለህ፤ ከፊትህ ያለውን በደንብ ማየት ትጀምራለህ፡፡ መሪህን ትመነጥራለህ፣ ዓላማህን ቀስ ብለህ ትሾፈዋለህ፤ ግብህን ታልማለህ፡፡ መድረሻህን ገና መንገድ ሳትጀምር ወጪና ኪሳራውን ቀድመህ ታሰላዋለህ፡፡ እየተራመድክበት ያለው “የሕይወት መንገድ አዳላጭ ነው፤ ወይስ ወስዶ ወስዶ ከገደል አፋፍ የሚያደርስ ነው” የሚለውን ለማወቅ አንተነትህን፣ መንገድህንና ዓላማህን መረዳት ይጠበቅብሃል፡፡ የመንገድህን መበላሸት፣ የዓየርህን መበከል፣ የአካሄድህ ግራገብነትን የምትረዳው ራስህንና ዓለሙን ስትረዳ ነው፡፡ የመበላሸት ተፈጥሮን ማወቅ ራስን ከብልሽት ማዳን ነው፡፡ የመኪና መነፋነፍ የብልሽት ምልክት ነው፡፡ የአስተሳሰብ መዛነፍም ውድቀትን ጠቋሚ ነው፡፡ ከብልሽቱ ዓለም ለመውጣት አስተሳሰብን መጠገን ግድ ይላል፡፡ ሊሰምጥ ጫፍ የደረሰ ሰውነትን መታደግ ከምንም በላይ አኩሪና አርኪ ነው፡፡ በሃሳብ ባህር ቀዝፎ፤ በህይወት ውቅያኖስ ተንሳፎ፣ በቀና አስተሳሰቡ ታንኳ የሕይወት ወጀቡንና የኑሮ ሞገዱን የሚያልፍ እሱ በአስተሳሰቡ የጠነከረ፤ ከኑሮው ልምድ የቀሰመ ነው፡፡
ከራሱ ጋር የመነጋገር ልምድን ያዳበረ ጠማማ አስተሳሰቡን ተረድቶ ወደቀናው አስተሳሰብ ይሸጋገራል፡፡ ከራስህ ጋር ለመወቃቀስ ከራስህ ጋር መግባባት ይኖርብሃል፡፡ ወቀሳን የሚቀበል ጭንቅላት ካልፈጠርክ የራስህ ከሳሽ ራስህ ትሆናል፡፡ ከወቀሳ ይልቅ ክስ ውጤቱ ጥሩ አይደለም፡፡ ክስ በመጨረሻ ፍርድ አለው፡፡ ወቀሳ ግን ለራስህ ይቅርታ እንድታደርግለት ነጭ ነጩን ነግሮ ምክር ይለግስሃል፡፡ ወቃሹም ተወቃሹም ራስ ለራስ ነው፡፡
የሚዛናዊነት፣ የአስተዋይነትና የብልህነት ቁልፍ ከታጠፈ ደግ ነገር ሁሉ ላይከፈት ተቆልፎ ይኖራል፡፡ ልብ ከተከረቸመ ቀናነትም ይጠረቀምበታል፡፡ አዕምሮ ከተዘጋ መልካም አስተሳሰብም የተዘጋ ይሆናል፡፡ ሕሊና በምክንያት መውደድና መጥላት ካልቻለ እንደጋሪ ፈረስ በማንም ደመነፍስ ይሾፈራል፡፡ ቁልፍ የሌለው ቤት ለሌባ እንደሚመች ሁሉ ቁልፍ አስተሳሰብ የጎደለውም የማንም ግብስብስ ሃሳብ መጫወጫ ይሆናል፡፡
የሕይወት ጋኑን የሚከፍት ቁልፍ ቅን አስተሳሰብና ምክንያታዊነት ብቻ ነው፡፡ ጋኑ አዕምሮ ነው፤ ቁልፉም አስተሳሰብን ይወክላል፡፡ ብዙ ተመሳስለው የሚሠሩ ቁልፎች ወይም ሃሳቦች አሉ፡፡ የቁልፉን ጋን የሚከፍተው ግን አንዱ ቁልፍ ብቻ ነው፡፡ ያ ቁልፍ የሕይወትህን መስመር፣ የአንተነትህን ጎዳና በርግዶ የሚከፍት ነው፡፡ አዎ ቁልፉ ስሪቱ ከአመለካከትህ ነው፡፡ ጥሬ ዕቃው የበሰለ ሃሳብህ ነው፡፡ በቀላሉ በማንም የማይከፈት ቁልፍ ለማድረግ ግን ማስተር ቁልፍ ያስፈልግሃል፡፡ ስትፈልግ የምትከረችመው፤ ሲያሻህ የምትበረግደው፡፡ የአዕምሮህን ቁልፍ በቀላል ሃሳብ ካዋቀርከው የማንም ተመሳሳይ የሃሳብ ቁልፍ ይከፋፍትብሃል፡፡ አንተ የእኔ የምትለው ሃሳብ ስለሌለህ የሌሎች ሃሳብ መኖሪያና መፈንጫ ትሆናለህ፡፡ በራስህ ሃሳብ እንዳትራመድ አንቆ ይይዝሃል፡፡
ብዙዎቻችን የተቸገርንበት ጉዳይ ይሄ ይመስለኛል፡፡ የአዕምሯችንን ቁልፍ ለምናደንቃቸው፣ ለምንወዳቸው፣ ከአኛ በላይ ያውቃሉ ለምንላቸውና በግል ለምናከብራቸው ሰዎች ስላስረከብን እነሱ ሲወድቁ እኛም እንወድቃለን፣ በአመለካከታቸው ሲፍገመገሙ እኛም እንፍገመገማለን፡፡ በክፉ ሃሳባቸው ምክንያት የሃሳብ ጢሻ፣ የሃጢዓት ገደል ውስጥ ሲገቡ እኛም ገደል እንገባለን፡፡ ሲፎክሩ እንፎክራለን፣ ጃስ ሲሉን እንናከሳለን፤ ያዘው ሲሉን እናሯሩጣለን፤ በለው - ቁረጠው ሲሉን እጃችን ለመሰብሰብና አንድ ጊዜ እንኳን ለማሰብ ጊዜ የለንም፡፡ አድርጉ የተባለውን ነገር ለማድረግ አናቅማማም፡፡ ከአመክንዮ ጋር ተጋጭተን ስለምንኖር ለምን እንዴት ብለን አንጠይቅም፡፡ ለራሳችን ሃሳብ ፍሬን አላዘጋጀንለትም፡፡ ለአስተሳሰባችን ቁልፍ የለንም፡፡ ሕይወታችን የሚሽከረከረው በሌላ ነው፡፡ ፍሬኑ እንደተበጠሰ መኪና ወደፊት መብረር እንጂ የዓለምን አራቱንም አቅጣጫ አይተንና አስበን አንሄድም፤ተረጋግተን የሕይወትን መንታ መንገድና መሰናክል አንሻገርም፡፡
ወዳጄ ሆይ… የአንተነትህ ምስል የአስተሳሰብህ ስዕል ነው፡፡ እይታህ የሚወለደው ከአመለካከትህ ነው፡፡ ምግባርህና ማንነትህ የሚታወቀው በስራህ ነው፡፡ ስራህ ደግሞ ተምጦ የሚወለደው ከሃሳብህ ነው፡፡ ሃሳብህ ከተበላሸ፣ የዘራኸው ከመከነ ፍሬህ አይጎመራም፡፡
አዎ! የትዕግስትህ ቁልፍ የደስታህን በር ይከፍታል፡፡ የታጠፈ ወይም የተጣመመ የአስተሳሰብ ቁልፍህ ግን የሕይወት ጋንህን፣ የአዕምሮህን ካዝና መክፈት አይችልም፡፡ የሕይወት ቁልፍህን ቀጥ አድርገህ ትሰራ ዘንድ አስተሳሰብህን አቅና፡፡ የቀና አስተሳሰብ የአዕምሮውን በር ወለል አድርጎ ይከፍታልና፡፡
ቅንነት ለሁሉ የተከፈተ ማንነት ነው፡፡ የደግነት የትየለሌ ትርፉ ደግ ከዋልንለት የበለጠ ለራስ ነው፡፡
ቸር ቅንነት! ቸር መጣመም የሌለበት ማንነት!
ዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ!
2.5K views14:14