2022-11-08 07:21:47
"እግዚአብሔር የሰው ልጅን ያዳነበት መንገድ በዕለተ ዐርብ በመሰቀሉና መከራን በመቀበሉ ብቻ የሚመስለውና ከነገረ መስቀሉ ውጪ ያለው ጉዳይ የሚጠቅም የማይመስለው ሰው ካለ ነገረ ድኅነትን ሙሉ በሙሉ አልተረዳም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በድንግል ማርያም ተፀንሶ ተወልዶ ሠላሳ ዓመታትን መቆየት ሳያስፈልገው ልክ የመጀመሪያውን አዳም እንደፈጠረው የሠላሳ ዓመት የሆነ ሥጋንና ነፍስን ለራሱ ፈጥሮ መለኮቱን አዋሕዶ ሰው መሆን ይችል ነበር፡፡ ይህንን ቢያደርግም ሦስት ዓመታት በምድር ላይ አስተምሮ በጊዜው ተሰቅሎ የማዳን ሥራውን መፈጸም ይችል ነበር፡፡
እርሱ ግን ማዳኑን የጀመረው በማሕፀን ከመፀነስ ነበር፡፡
አረጋዊው ስምዖን ‘ዓይኖቼ ማዳንህን አይተዋል’ እንዳለ ማዳኑንም የጀመረው ሕፃን ሆኖ በመታቀፉ ነው፡፡ ሉቃ. ፪፥፴ የጌታ የማዳን ሥራ ወሳኙ ታሪክ ከመስቀሉ ጋር በችንካር የታሰረበት ብቻ ሳይሆን በድንግል ማርያም እቅፍ በፍቅር የታሰረበት ቅፅበትም ነው፡፡ ክርስቶስ ሊያስታውሰው የማይፈልገው የልጅነት ሕይወት ያለው አይደለምና ስለ ክርስቶስ የሚሰብኩም ሁሉ ይህንን ድንቅ የሕፃንነት ጊዜውንና ያደገበትንሁኔታ ቸል ሊሉ አይገባም፡፡
ክርስቶስን ‘በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ሆኖ’ በሰዎች ልቡና እንዲሣል በመጀመሪያ በድንግል ማርያም እቅፍ እንደተወለደ ሆኖ መሣል ይገባዋል፡፡ ልብህ ውስጥ ሳይወለድ የሚሰቀል ክርስቶስ ካለ ለወለደችው እናቱና ለድንቅ ልደቱ ዋጋ ልትሠጥ አትችልም፡፡
መስቀል መሸከሙ ዘልቆ የሚሰማህ በልጅነቱ ያቀፈችውን ድንግል ማየት ስትችል ነው፡፡ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱ የሚያስለቅስህ ድንግልናዊ ወተትን ካጠባችው እናቱ ጋር አብረህ ስትሆን ነው፡፡ አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ላለው ክርስቶስ በምድር ላይ በቆየበት መዋዕለ ሥጋዌው አልፋው ድንግል ማርያም ስትሆን ኦሜጋው መስቀል ነበር፡፡ የተሰቀለ ቀን ብቻ አይተህ ልታውቀው አትችልም፡፡ ሁለተኛ አዳምነቱ ዘልቆ የሚሰማህ ወደ ልደቱ ስትመለስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቁስልም የሻረው ጌታ ሊወለድ ካለበት ቅፅበት ጀምሮ ነው፡፡
በገነት ዛፎች መካከል አንድ የረከሰ መልአክ እና አንዲት ሴት ተነጋግረው ተስማምተው ያበላሹትን የሰው ልጅ ታሪክ ድጋሚ ሊጽፈው የፈቀደው እግዚአብሔር በተቀደሰ መልአክና በአንዲት ሴት መካከል ንግግር አስጀመረ፡፡
ሰይጣን በምድር ከሚርመሰመሱ አራዊት መካከል
ተንኮለኛውን እባብን መርጦ ሔዋንን በማሳመን የሰው ልጅ ከገነት አስወጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ በሰማያት ከሚያመሰገኑ ብርሃናዊያን መላእክቱ መካከል ከዋነኞቹ አለቆች አንዱን ቅዱስ ገብርኤልን መርጦ ድንግል ማርያምን እንዲያበሥራት ላከ፡፡
ሁለተኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ከመጀመሪያይቱ ሔዋን እጅግ በብዙ ነገሮች ትለያለች፡፡ ሔዋን የተቀደሰው ገነት ውስጥ ተፈጥራ ፈጣሪዋን የበደለች ስትሆን ድንግል ማርያም ግን በእርግማን በረከሰው ምድር ላይ ተፈጥራ የተቀደሰች ናት፡፡
የቀደመችው ሔዋን በገነት መካከል ሥራ ፈትታ የምትመላለስና የእባብን ድምፅ ሰምታ አዳምን ለሞት የምትዳርግ ስትሆን አዲሲቱ ሔዋን ግን ራስዋ ምድራዊት ገነት ሆና አዳምን ያስገኘች ናት፡፡ ከዚህች ገነት ተፀንሶ የተወለደው ሁለተኛው አዳም እንደ ቀድሞው አዳም ተባርሮ የወጣ ሳይሆን ‘ሙሽራ ከጫጕላው እልፍኝ እንደሚወጣ’ ከእርስዋ የወጣ ሙሽራ ነው፡፡
ይህችኛይቱ ሔዋን የሰው ልጅ ቃልዋን ቢሰማ ‘የሔዋንን ቃል ሰምተሃልና የተረገምህ ትሆናለህ’ ተብሎ የሚሞትባት ሔዋን አይደለችም፡ ፡ ይህች ድንግል ቃልዋን ብንሰማ የምንባረክባት ከአንደበትዋ የሚወጣው ቃል እንደ ሔዋን ካለመታዘዝ ፍሬ እንድንበላ ሳይሆን ‘የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ’ የሚል የሚያድን ቃል ነው፡፡ ዮሐ. ፪፥፭
ያችኛይቱ ሔዋን ከአዳም ተገኝታ የተሠራችና አዳም ወደ
እርስዋ እያየ ‘ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ናት’ የሚላት ናት፡፡ ይህችኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ግን ከአዳም የተገኘች ሳትሆን አዳምዋ ክርስቶስ ሥጋው በጅራፍ ግርፋት ሲቆስልና አጥንቶቹ ሲቆጠሩ በጭንቀት እያየች ‘ይህ አጥንት ከአጥንቴ ነው ፤ ይህ ሥጋም ከሥጋዬ ነው’ የምትል ሔዋን ናት፡፡
የቀደመችዋ ሔዋን አዳምዋ በእርስዋ ምክንያት ጠፍቶ ‘አዳም ሆይ ወዴት ነህ?’ ተብሎ ሲፈለግ በዛፎች መካከል ሆኖ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ‘ፈርቼ ተሸሸግሁ’ የሚል አዳም ሲሆን ሁለተኛይቱ ሔዋን ግን አዳምዋን ፍለጋ የምትጨነቅና ወዴት ነህ? ስትለው አዳምዋ ‘በአባቴ ቤት እኖር ዘንድ እንዲገባኝ አታውቁምን’ ብሎ የሚመልስላት ከአባቱ እቅፍ ያልተለየ አዳም እናት ናት፡፡
ለድንግል ማርያም ክርስቶስ ከእርስዋ የተገኘ አዳምዋ ብቻ ሳይሆን በቀናተኞቹ ቃየኖች አይሁድ በግፍ የተገደለባት አቤልዋም ጭምር ነው፡፡ ልዩነቱ የአቤል ደም ወንድሙን የሚከስስ ደም ሲሆን የእርስዋ ልጅ የክርስቶስ ደም ግን ‘ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር’ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ ደም’ ነው"
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 27 2015 ዓ.ም.
ከብርሃን እናት መጽሐፍ ገጾች
1.5K views04:21