2022-08-07 13:30:11
#ሰባቱ_ዓለማት_ግን... ባለሙያዎቹ ቢረግጧቸው አይሻልምን? [ርዕስ መሆኑ ነው]
ሃይማኖት፣ ቤተሠብ፣ ትምህርት፣ መንግሥት፣ ቢዝነስ፣ ሚዲያ፣ አርት እና የመዝናኛ ኢንዱሰትሪ - ዶሚኒየሞች ለመጨበጥና ዓለም ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚመኟቸው ተራራዎች ወይም ደግሞ ዓለሞች ናቸው።
መንግሥትንም ይህን 'ጥበባቸውን' ይግቱታል። እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ የጨለማ ክፍለዘመን የሚባለውን የመካከለኛው ክፍለ ዘመንን [500 - 1500 A.D. አካባቢ] ቤተክርስቲያንን ያስታውሰኛል። ፍርድም እውቀትም፣ ፍትህም ጥፋትም፣ ፈውስም በረከትም ከቤተክርስቲያን በመንግሥት በኩል ለሕዝቡ ይፈስ ነበር።
መካከለኛ ዘመን የሚለው ስያሜ ራሱ ጥበብና ፍልስፍና ከገነነበት ዓለም አንስቶ ሰብዓዊነት [humanism] ብቅ እስካለበት 15ኛው ክፍለዘመን ድረስ የነበረውን ዘመን ነበር። በመሃል ያለው ቤተክርስቲያን ጥበብን ፍልስፍናን ሳይንስን ጠቅልዬ እኔ ካልባረኩት መላም የለው ያለችበት ዘመን ነው። ስለዚህም ጥበብን ወዳጆች መካከለኛው ዘመን ይሉታል እንጂ ምንም የማድረግ ነጻነት ስለሌለ ከቁምነገር አይከቱትም። የሆነ ጥሩ ዘመንና የሆነ 'ብርሃን' ዘመን ያለ መካከለኛ። የተሃድሶ ዘመን ራሱ ለምን እንደደመቀ ፍንጭ ይሰጣል።
እናሳ:-
ዶሚኒየም መጣልሃ! 7 spheres ምናምን እያለልህ። አማኞችን 'ብሪሊየት ስግብግብ' ለማድረግ የሚያነቃቃ ነው። እንደ መካከለኛው ክፍለዘመን ሳይንሱም፣ ፖሊሲውም፤ አርቱም፣ ፖለቲክሱም፤ ፈረንካውም መዝናኛውንም... አንተ ካልቀረጽከው ይህቺ ዓለም መጥፋቷ ነው እያለ ያወራጭሃል።
ወገኔ: - የቄሳርን ለቄሳር መርህን ብትከተል ትህትና ነው። ሃይማኖት ላይ የዶሚኒየኒዝም ጨረር ከምትረጭ ተማር። ሃይማኖት የሰው ልጆችን እኩልነት እንደሚያከብር፣ ጥሎ መነሳትን እንደሚነውር፤... ተማር። ሃይማኖትህን ሌላው ላይ እየሠለጠንክ ሳይሆን ለሌላው እየኖርክ ጠብቅ። የምን ጨረር መልቀቅ ነው።
ማሕበረሰብን ለማቅናት በዓለም ላይ ተፈትነው ለዛሬ ዘመን የበቁ ማሕበራዊ ሳይንሶችን ዩኒቨርስቲ ገብተህ ተማር። ወይም አንብብ። በአዳራሾቻችን የለመድነውን ሁከትና ሠለም የለሽ ምልልስ ይዘህ ማሕበረሰብ ላይ ዶሚኒየም ምናምን ስትል እፈር። ፖለቲኪኛው ፖለቲካ ይማር። የአርቱም ሰው የሙያውን እውቀት ያዳብር። ፈረንካውንም ለኢኮኖሚስቶቹ ተው! ምንድነው ወጧ እንዳማረላት ሴት እየጠቀስኩ ሁሉንም ካላማሰልኩ ማለት?
ታዲያ ቤተክርስቲያን ምን ቀራት? እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥን? ትለኝ ይሆናል። በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ስልጠና ከሌለህ እጅን ማጠፍ ብቻ ሳይሆን 'መቁረጥም' ጥሩ ነው [ከሚፈትንህ]። ቤተክርስቲያንማ ከላይ ያሉት ሁሉ ለሰው ልጆችም ጥቅም በባለሙያዎች ሲሠሩ ፍቅርን፥ አንዱ ለአንዱ አስፈላጊ መሆኑን፣ መታዘዝን፣ ጽድቅን፥ የሰው ልጆች እኩልነትን በመኖርም በመለፈፍም መርህ እንዲሆናቸው ታስተምራለች።
የመድረክ ተረኞች አይነግሩህም ብዬ ነው። እህእ! ዶሚኒየን ስነመለኮት የቤተክርስቲያንን ማንነትና ተልዕኮ ጭቃ ቀቢ ነው። ባ'ላት ሁለት እግር ሰባት የተራራ አናት ካ'ልረገጥሽ እያለ የሚያንጠራውዝ ነው።
አዝናለሁ፦ በምንም ርዕስ ይናገር እዚህ የቅዠት ማዕቀፍ ውስጥ ወንድሜን ሳየው። ለነገሩ መንገድ ጠራጊዎቹ ብዙ ናቸው። አንድ የተጠና ጥናት ነበር - እርሱን ከሼልፍ ማውጣት ሳያስፈልግ አይቀርም።
ተገኝ ሙሉጌታ
609 views10:30