2022-06-26 06:43:18
እንደ ክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ “እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል?” የምንልባቸው አሳሳቢ አገራዊ ጉዳዮች አሉን። በቅዱስ ቃሉ ውስጥ እንደምናነበው፣ እኩይ ተግባር ሕይወታቸውን በድንገት ሲያጨልመው፣ ፍትሕ ሲዛባ፣ ምድር ሁሉ ዐዋቂና ቻይ የሆነ እግዚአብሔር የሚገዛት ሳትመስል ስትቀር፣ “እግዚአብሔር ወዴት ነው? ትድግናውስ ለምን ዘገየ?” የሚሉ የግልና አገራዊ ጥያቄዎችን በማንሣት መልስ ፍለጋ ብዙዎች ታግለዋል።
ዘማሪው አሳፍ፣ ስለእግዚአብሔር ያለውን መረዳትና የራሱን የግል ሕይወትም እንቆቅልሽም ሆነ እስራኤል በወቅቱ የነበረችበን አዘቅትና መከራ ማስታረቅ ስለተቸገረ፦ "እግዚአብሔር ልባቸው ንጹሕ ለሆነ፣ ለእስራኤል እንዴት ቸር ነው! እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣ አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ።" በማለት ስለውስጥ የነፍሱ ትግል ዘምሯል (መዝ 73:1)።
ነቢዩ ዕንባቆም ተመሳሳይ ጥያቄ አስተጋብቷል፤ “አቤቱ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? “ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው . . . እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? . . . ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣ ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ . . . ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤ አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤ ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ? አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ” (1፥1-14)።
ወንድማችን ኢዮብ፣ እግዚአብሔርን አግኝቶ በሙግት መርታት ፈልጎ ነበር። “ነገር ግን ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ፤ ከእግዚአብሔርም ጋር መዋቀስ እሻለሁ። (13፡3)። “ዛሬም ሐዘኔ መራራ ነው፤ እያቃሰትሁ እንኳ እጁ በላዬ ከብዳለች። እርሱን የት እንደማገኘው ባወቅሁ፤ ወደ መኖሪያውም መሄድ በቻልሁ! ጒዳዬን በፊቱ አቀርብ ነበር፤ አፌንም በሙግት እሞላው ነበር።” (23:2-4)።
ዳዊት በመዝሙሩ፣ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳን ከመቃተቴም ቃል ለምን ራቅህ?” (መዝሙር 22፥1) በማለት ያነሣውን ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባሰማው የጣር ድምፅ ወስጥ ተስጋብቷል።
አሳፍ የኋላ ኋላ ግን ዞር በሎ ሲያስውል፡- "ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ" (73:23-24)፣ በማለት የእሮሮውን ምዕራፍ በምስጋና ዝግቶታል። በዚህ ምድር ላይ፣ የእርሱን የሕይወት ጥያቄዎች ጨምሮ፣ ሁነቶች በሙሉ፣ በእግዘአብሔር ሉዓላዊ ማዕቀፍ ውስጥ መያዛቸውን በመረዳቱ ነበር ልቡ ያረፈው። ዕንባቆም ከብዙ ትግል በኋላ መልሱ “ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው” (3:19) የሚል ነበር። ምክንያቱም “እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለና!” (2:20)። ኢዮብም መሻቱን አግኞት ነበር፤ እግዚአብሔርን በሙግት የመርታት ዕድል! ሉዓላዊው እግዚአብሔር “እስቲ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ ልጠይቅህ፣ አንተም መልስልኝ (38:3)። እናም የኢዮብ የመጨረሻ ድምዳሜ፣ “አንተ ሁሉን ማድረግ እንደምትችል፣ ዕቅድህም ከቶ እንደማይሰናከል ዐወቅሁ። አንተ፣ ‘ያለ ዕውቀት ዕቅዴን የሚያደበዝዝ ይህ ማን ነው’ አልኸኝ፤ በእርግጥ ያልገባኝን ነገር፣ የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጒዳይ ተናገርሁ . . . ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ። ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።”። (42:1-6)
ተስፋችን የተመሠረተው በእርሱ ሉዓላዊ ገዥነትና ሁሉን ዐዋቂነት ላይ ነው። በሚታየውና በማይታየው ዓለም ግዛት ላይ፣ እግዚአብሔር "ጌታ" ያለሆነበ አንዲትም አዪታ ክፍተት የለም። እግዚአብሔር ዓለማትን በፈጠረበትና ደገፎ በያዘበት በዚያው የሥልጣኑ ቃል የእኛንም ሕይወት ደግፎ መያዙን ሳናስብ ልባችን ያርፋል። በርግጥ እርሱ በሁሉ ቦታ አለ፦ "እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።" (መዝ. 139:9)።
. . . እናም በዚህ ሕይወት ብርቱ ሰልፍ በሆነባት ምድር፣ ለጥያቄያችን ሁሉ መልሱ ሁሉን ዐዋቂ እግዚአብሔር ሉዓላዊ መሆኑ ብቻ እንጂ፣ የእኛን በአምንክዮ ሞግቶ የሚያሳምን መልስ ማግኘታችን አይደልም። ቢገባን ባይገባንም እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ልባችንም ማረፍ ያለበት በእርሱ ሉዓላዊነት ላይ ብቻ ነው። በግል ሕይወታችን ውስጥ ስላሉት ሰልፎችም ሆነ፣ አገራችንን ጨምሮ ዓለም ዐቀፋዊ የሰላም መረበሽና የፍትሕ ቀውስ እየከረረ በመጣበት በዚህ ዘመን እንደ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው እግዚአብሔርን ነው። በሕይወት የምንኖረው፣ ነገሥታትም፣ እኛም ስለፈቀድን አይደለም። ነገር ግን ከልዑል አምላክ በሚወጣ የምሕረትና መግቦታዊ የቸርነት ቃል ነው። ተስፋችን የተመሠረተው "ምድርና ሕዝቦቿ ሁሉ በሚናወጡበት ጊዜ፣ ምሰሶቿን አጽንቼ የምይዝ እኔ ነኝ።" ባለው ጌታ ላይ ነው። (መዝ 75:3)። የእርሱ መንግሥት ሁሉን ትገዛለችና!
ዓለም በልዑል እግዚአብሔር እጅ እንጂ፣ በሰው እጅ አይደለችም፤ የእኛን የግል ሆነ፣ የዓለምን ታሪክ በሉጋም የያዘ ጌታ ነው የምናመልከው። እግዚአብሔር፣ ጊዜን ሁሉ - ትላንትናን ዛሬና ነገን በአንድ ጊዜ በእጁ የያዘ አምላክ ነው። እርሱ በመገርምም ሆነ በድንጋጤ አይያዝም፤ ነገነም በሥጋት ወይም በተስፋ አይጠብቅም! እርሱ በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ነው፤ ክብር ጐድሎበት፣ ፍጥረትን ክብር አይለምንም፤ በማንም አይደገፍም፤ ለሥራውና ውሳኔው ትክክለኛነት ማንንም አያስፈቅድም፤ ማስተዋሉ ፍጹም፣ ምክርም ማንንም አይጠይቅም፤ ዕውቀት አይጨመርለትም፤ አልገባኝም አስርዱኝ አይልም - ነገሮች ሳይጀመሩ ፍጻሜያቸውን ያውቃልና! አሳቡም አይከለከልም:
ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁና።
በሰማይና በምድር፣
በባሕርና በጥልቅ ሁሉ ውስጥ፣
እግዚአብሔር ደስ ያሰኘውን ሁሉ ያደርጋል። (መዝ. 135; 5-6)
እንግሊዛዊው የወንጌል ሰባኪና ጸሐፊ፣ ዊንክ (1886-1952) እንዳለው - እርሱ ከሁሉ በላይ ነው፤ ". . . God, being infinitely elevated above the highest creature, is the Most High, Lord of heaven and earth. Subject to none, influenced by none, absolutely independent; God does as He pleases, only as He pleases always as He pleases. None can thwart Him, none can hinder Him." (A. W. Wink, The Attributes of God). እናም ውሉ እንደጠፋ የሸማኔ ማግ ውስብስብ ባልብን የአራችንም ሆነ የግል ጉዳያችን፣ እስቲ ለልዑል፣ በቻው ማዳን ለሚቻለው ዕድል እንስጠውና እንረፍ - መውጫውን ያውቃልና!
ከዘማሪ ተስፋዬ ጋር እንዲህ በለን ብንዘምርስ?
“ከአቅምህ በላይ ሆኖ የሚከብድህ
ለመፈታት ከቶ የሚያስቸግርህ
ምን ችግር አለ የሚያዳግትህ
ሁሉን ቻይ የሆንክ ኤልሻዳይ አንተ ነህ . . .”
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ የሆነብንን አሰብ (ሰቆቃው 5:1)፤ አሜን!
ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
507 views03:43