Get Mystery Box with random crypto!

ለሐረር እና ድሬዳዋ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ! በጌታ | ነገረ ወንጌላውያን

ለሐረር እና ድሬዳዋ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች

የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

በጌታ የተወደዳችሁ ሆይ በብዙ ትጋት እና መሰጠት ለእግዚአብሔር መንግሥት እየደከማችሁ ስላላችሁ ስለ እናንተ አምላኬን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፡፡ የምስራቁ የአገራችን ክፍል ለወንጌል አገልግሎት እጅግ ከባድ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ቢሆንም የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲሰፋ እያደረጋችሁ ያላችሁት ተጋድሎ በእውነቱ ድንቅ ነው፡፡ በእናንተም እየደከመ ሰላለው የጌታ ጸጋ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!

ይህን መልእክት እንድጽፍላችሁ ያነሳሳኝ ዐቢይ ምክንያት፣ እንደምታውቁት ከጊዜ ወደ ጊዜ በቤተክርስቲያን ሾልከው የሚገቡ የስሕተት ትምህርቶች ቤተክርስቲያንን እያናወጧት ይገኛሉ፡፡ በየጊዜው የሚገለጡ የስሕተት ትምህርቶች ያሉ እና የሚኖሩ በመሆናቸው፣ እንደ ብርቅ ነገር አንቆጥራቸውም፡፡

ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ቸል የሚሉ መሪዎች የመብዛታቸው ጉዳይ የበለጠው አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ መሪዎች መሪ የሆኑበት ዋና ነገር መንጋቸውን ከተኩላ ለመጠበቅም እንደሆነ ቃለ እግዚአብሔር በስፋት ይናገራል፡፡ ይህንን ጉዳይ ቸል እንዳይሉ በማሰብም ሐዋርያው ጳውሎስ የኤፌሶንን መሪዎች በእንባ አሳስቧል፡፡

ዛሬ ላይ ማንም የነሸጠው ተነስቶ ቤተክርስቲያን ሊያቋቁም የመቻሉ ሐቅ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ ባለ ቤተክስቲያናት ደግሞ ለእውነተኛው አስተምህሮ እና ክርስትና ግድ የሚላቸው አይደሉም፡፡ ትርፍ የሚያገኙ እስከመሰላቸው ድረስ ማንንም በመድረካቸው ሊያቆሙና ወደ ከተሞቻችሁ ሊያሾልኩ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን መርዘኛ አካሄድ ቸል ብሎ መመለከት ለእውነተኞቹ መሪዎች ልከኛ አካሄድ ሊሆን አይችልም፡፡

በመሆኑም ሕዝባችሁ በእውነተኛ ትምህርት እንዲቆምና የሚተባበረውን እና የማይተባበረውን ማኅበር አጥብቆ ማስገንዘብ ይገባችኋል፡፡ በተጠራበት ሁሉ የሚገኝ ምእመን ሊኖረን ጨርሶውኑ አይገባም፡፡ እንደ ወንጌል እውነት የሆነውን ኅብረት እንደምንደግፍ ሁሉ ከወንጌል እውነት ያፈነገጠውን ሐሳዊ ኅብረት ደግሞ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
ከዚህ በፊት የሆሳዕና አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በአንዱ ሐሳዊ ነባይ ላይ የወሰዱት ቅዱስ አቋም በየትም ቦታ ሊተገበር የሚገባው በጎ ተመክሮ ነው፡፡

ከወንጌላውያን አስተምህሮ ጋር ስምምነት የሌለለው ነባይ ወደ ከተማችሁ ሊመጣ እንደሆነ መለከት እየተነፋ ነው፡፡ የጠሩት ሰዎች መጥራት፣ ተጠሪውም መምጣት መብታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እናንተ ደግሞ እግዚአብሔር የሰጣችሁን መንጋ መጠበቅ ግዴታችሁ ነው፡፡ ስለዚህም ለምታገለግሉት ማኅበረ ምእመን አቋማችሁ በይፋ ታሳውቁ ዘንድ ልመናዬን አቀርባለሁ፡፡

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ሥራ 20፡28

መጋቢ ስንታየሁ በቀለ