2022-08-05 06:31:35
+++ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን+++
#መቼ_ትመጣለህ ?
መቼ ትመጣለህ? ነገ ወይስ ዛሬ?በኃጢአት አልክበር ፤ ዕድሜዬን አልጨርስ ፤ አልብላው መንዝሬ።
ንገረኝ ጊዜውን ፤ ቆሜ ልጠብቅህ ፣
ግራ ቀኝ አልባክን ፤ እንዴት ነው አመጣጥህ ?
ትዘገይ እንደሆን ፤ ላትጠራኝ ቶሎ ፣
ከእፀ በለስ ልብላ ፤ ስሜቴ ገንፍሎ ፣
ምክንያቴን አብዝቼ ፤ አግዝፌ ልቆይህ ፣
ሔዋን አስታኝ ነው ፤ ሰይጣን አሳስቷት ፤
መክሯት ነው ልበልህ።
ለሥጋዬ ልስጣት ፤ ሥልጣኑን በሙሉ ነፍሴን ትበድላት ፣
ለጊዜው ትጠቀም ፤ አንተ ከዘገየህ ትሁነው እንዳሻት ።
ጊዜ አገኝ እንደሁ ፤ በተራገምኩበት መመረቅ እንድችል ፣
እስከ ጊዜው ድረስ ፤ ነፍሴ ታንጎራጉር ትንደደው ትቃጠል ።
ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ፤ ይኸው በዚህ ሰሞን ታሪክ ያወራሉ ፣
ያ! ስምንተኛው ሺህ ፤ ከተነገረ እንኳ ቆይቷል እያሉ
ሰዉ ጽድቁን ትቷል ሁሉም በያለበት ሀሜቱን ቀጥሏል ፣
መጋደል መጣለፍ ፤ መቋሰል መቧደን ዝርፊያውም በርክቷል ፣
እንኳን ዳግም ም'ጻት የዓለም ፍጻሜ ስምህ ተዘንግቷል።
መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
ግዴለም ንገረኝ ፤ ልክ እንደኖኅ ጊዜ ዘመኑን አስላና፣
ሃያዋ ብትበቃኝ ለንሰሓ ጊዜ ፤ በመቶው ልዝናና።
ገና አልበረደኝም ሰውነቴ ግሎ ውስጥ አካሌ ዘንቶ፣
ዓለሙን ያስሳል ፤ አንተ ከዘገየህ ለምን ሥራ ፈትቶ።
እበላው እንደሆን የሰበሰብኩትን ፤ ከሌላው ዘርፌ፣
እኖረው እንደሆን እንደማቱሳላ እድሜዬን አትርፌ።
ሺህ ዓመቴን ወስደህ ፤ የአንተን አንድ ቀን ትሰጠኝ እንደሆን ፣
ምናለበት ብዘርፍ ምናለ ብዘሙት ፤ መዘግየትህ ላይቀር ።
ከምድር እሰከ ሰማይ ፤ ተዘርግቶ 'ማያልቅ ለበዛው ኃጢአቴ ፣
ጊዜ ካበደርከኝ እንዲሰረዝልኝ ፤ እንዲፋቅ ጥፋቴ ፣
ልክ እንደ ኢያሱ ፤ ፀሐይን አቁመህ ከጠበቅኸኝ በቃኝ ፣
ዛሬን ልዝናናበት ፤ ኃጢአት ልጨማምር ጨለማ ሳይወርሰኝ ፣
ይኸው ሰዉ ሁሉ ነገሩን ዘንግቶ ፤ ሁሉ ሆድ ብሶታል ፣
"ይዘገያል " አሉ እያለ ያወራል ፤ ኃጢአት ይሸምታል።
እኔም በቀደም 'ለት ፤ ከደጀ ሰላሙ ብዙ ጉድ አይቼ፣
ገዛሁት በርካሽ ፤ ኃጢአትን ከደጅህ ፤ ከቤትህ አግኝቼ።
ግዴለም ንገረኝ ፤ ሃያው ይበቃኛል በሌላውስ ላትርፍ ፣
እንዴት ከሌላው ህዝብ ፤ እኔ ተለይቼ እንደ ጅል ልንከርፈፍ ?
መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
ሌላውን ልበድል ፤ ነገርን ልዶልት ህዝብህንም ልቁጠር ፣
ከድንኳን ደጃፍ ፤ ተቀምጬ ላሹፍ ፤ ዘፈን ላንጎራጉር ።
ጊዜ ከሰጠኸኝ ፤ የምለይበትን ዘፈንን ከመዝሙር ፣
ንሰሐ ገባለሁ ልክ ስትመጣ ፤ ዛሬን ግን ልጨፍር።
ከጥብርያዶስ ባሕር ፤ ኃጢአት ዓሣን ላጥምድ፣
ትዘገይ እንደሆን ምናል ይህን ብትፈቅድ?
ይኸው ሰዉ ሁሉ ፤ ግራ ያጋባኛል ነገር እያማታ ፣
ኃጢአትን አግብቶ ፤ ትዳርን መስርቶ ጽድቅን እየፈታ ።
በክፋት ላይ ክፋት ፤ በዚያ ላይ ስምህን በፍፁም ደርቦ ፣
ጽድቅና ኃጢአትን ባንድ እያካሄደ በደስታ ተከቦ ፣
ጻድቅ ሲሸማቀቅ አንገቱን ሲደፋ ፤ ተመልካችም ሲያጣ ፣
እንዳሻው በመሆን ፤ ኃጥእ ሲዝናናበት ሲስቅ በለበጣ ።
ዘመናት አለፉ ፤ ይኸው ዛሬም የስምህ አጥፊዎች፣
ሥራቸውን ሰደው ፤ በደንብ ተስፋፍተው ዙሪያውን ብዙዎች ፣
ከደሃው ላይ ሰርቀው ፤ ምስኪን አስለቅሰው ለታቦት ሲያገቡ ፣
ወገን ጦሙን አድሮ ፤ ሲበሉ ሲጠጡ ሲያገቡ ሲጋቡ ።
እንኳንስ መምጣትህ ፤ ስምህ ተዘንግቶ አዳሜ ሲጨፍር ፣
እኔስ ምን ተዳዬ ፤ ከዚህ ህዝብ መሃል ተለይቼ ልቅር ?
ይልቅስ ንገረኝ ፤ ትመጣ እንደሆን ፀሐይ ሳትገባ ፣
አሊያም ልደባለቅ ከምድር ወገኖቼ ፤ ከወጣው ወጥቼ ከገባው ጋር ልግባ ።
መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
የበራፌ ጥላ ከበር እስኪከተት ፤ 'ማትመጣ ከሆነ፣
አሸንክታብ ላርዝም ክብሬንም ልፈልግ ፤ ጊዜዬ ባከነ ፣
ዓለሙን ልከተል የዛሬን ልደሰት ፤ ነገ እመለሳለሁ ፣
አንተ ዛሬ ትመጣ ፤ ወይም እንደምትቀር በምን ዐውቀዋለሁ ?
ይኸው በዚህ ሰሞን ፤ ሰዎቹ በሙሉ ታሪክ ያወራሉ፣
እሱ ቀርቷል ብለው፣ ባንተም ላይ ደርበው ጣዖት ያመልካሉ።
ይኸው በዚያ ሰሞን ፤ ሥጋ ቤቱ ደጃፍ ሁሉ ተኮልኩሎ ፣
በሁዳዴ ምድር ቁርጥ ያወራርዳል ፤ መስቀል አንጠልጥሎ ።
እኔስ አያምረኝም ? አንተ እንደው አትመጣ ፤ ብበላ ምናለ ፣
ጠበል እረጫለሁ ፤ ወደፊት ጾማለሁ አንተ ከዘገየህ ፣
እንዲሁ በከንቱ ጊዜ ከሚባክን ፤ ቅዳሴ አስቀድሼ ዳንኪራ ቤት ብሄድ
ጽድቅን እንደሆነ ፤ መቼም አላጣትም ለኃጢአት ብሰደድ ፣
የልቤ ግድግዳ ቢጠቁር በክፋት ፤ ደግሞም ቢበሰብስ ፣
ዛሬ አንተ ካልመጣህ ነገ እታጠባለሁ ፤ ንሰሐ ሳሙና እስካለልኝ ድረስ!
ምናለ ብሳደብ ሌላውን ብጎዳ ፤ ማንም እናዳይነካኝ ፣
ግዴለም ለነገ ግራዬን ቢያጮሉኝ ፤ ቀኜን ሰጣለሁኝ።
እንደ ሕፃን በርሬ ያሻኝ ቦታ ልድረስ ፤ ያሻኝን ልተንፍስ ፣
አኩኩሉ ልበል ፤ በኃጢአት ጫካ እስክትመጣ ድረስ ።
መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
ምናለ እንደ ዴማስ ፤ ይህችን ዓለም ብወድ አንዴ ብተፈቅድልኝ ?
በኋላ መጣለሁ ልክ እንደ ድሮዬ ፤ አገለግላለሁ ቆመህ ከጠበከኝ።
ትዘገይ እንደሆን ፤ በቶሎ ማትመጣ አሊያ የምትቀር ፣
ምናል ሳማ ሰንበት ፤ ብሄድ ለሽርሽር ?
ቢራዬን ገዝቼ ፤ ቱታዬን አጥልቄ ፣
ልክ እንደ ቱሪስቶች ፤ ምግቤንም ሰንቄ ፣
በውጭዎች ፈሊጥ ፤ እየተቀናጣሁ ደርሼ ብመለስ፣
ምናለ ባልጸልይ ፤ ምናል ባላስቀድስ ?
ይኸው ትናንት እንኳ ፤ ትናንትና ማታ
ሰዎች ተኮልኩለው ፤ ከዐውደ ምሕረቱ ፣
አየሁኝ ሲጣሉ ፤ በቡድን ተከፍለው ነገር ሲዶልቱ።
እኔስ ምን አለበት ፤ በነሱ ብጽናና በኃጢአት ባድግ፣
አንተ እንደሁ አትመጣ ፤ ስንት ዘመን ሆነኝ ቆሜ ሳደገድግ ።
ፍጹም ልመሳሰል ከዚህ ዓለም ጋራ ፤ ማንነቴ ጠፍቶ ፣
አንተ ከዘገየህ ፤ ምናል ይህ አካሌ ቢኖር ሕይወት አጥቶ ?
ጊዜዬን ልስራበት ለኃጢአት ልነሣ ፤ ለጽድቅህም ሞቼ ፣
ክርስትናው እንደው መቼም አይቀርብኝ ፤
ነገ እቆርባለሁ በምርኩዝ መጥቼ ።
መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
ይኸውና ዛሬ ሁሉ ቀላል ሆኖ ፤ መፈራትህ ጠፍቶ ፣
የነዲዮስቆሮስ የነጴጥሮስ እምነት ፤ ከኋላ ተገፍቶ፣
ሰው ሰውን እያየ በሥጋ ሲጽናና ፤ አምላክን ረስቶ ፣
ከዐውደ ምሕረቱ አንተ ተሸፍነህ ፤ እኔን ስሙኝ በዝቶ ፣
እምነት እንደፋሽን ራሱን ተኩሎ ፤ ራሱን ቀብቶ ፣
በደፋሮች ጩኸት መቅደስህ ታውኮ ፤ መቅደስህ ሲረክስ ፣
ዐዋቂ አንገቱን በደፋበት መድረክ ፤ ታዋቂ ሲነግሥ።
ነጠላና ቀሚስ የጽድቅ መገለጫ ፤ በሆኑበት ዘመን፣
በስሜት ተነድቶ በስም ብቻ ሲሮጥ ፤ ህዝብህም ሲባዝን ፣
እኔስ ምን ተዳዬ ፤ ለግዜው ብደሰት ?
ሆ! ካለው ሆ ብዬ አብሬው ብዘምትም ፤ ሆሳዕና ብዬ ዛሬ ብዘምርም ፣
ከሳምንት በኋላ በዚያው አንደበቴ ፤ ይሰቀል !ይሰቀል! ማለቴ አይቀርም ።
እምነቱ ባይገባኝ ፤ እኔ ምን አገባኝ ?
ዝም ብዬ ሮጣለሁ
ምን ችግር አለበት አንተ ከዘገየህ ፣ ምስጢረ ሥላሴን ውዳሴ ማርያምን ፤
ቀስ ብዬ እማራለሁ ፣
አንተ እንደ ምትመጣ ፤ ወይ እንደ ምትቀር በምን ዐውቀዋለሁ ???????
660 views𝓜𝓮𝓷𝓽𝓮 ²⁵, 03:31