Get Mystery Box with random crypto!

ሐምሌ 19 ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ ቅዱስ | መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

ሐምሌ 19

ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ

ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ። ይህም ሕፃን ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ከሮሜ አገር ወደሌላ ሀገር እናቱ ይዛው ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኰንን አገኘችው

ሰዎችም ነገር ሠሩባት ወደርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኰንን ሆይ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው

ሕፃኑም ወደአለበት ጭፍራውን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው። ሕፃኑም መልሶ አዎ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ኀዘንና ልቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስከ አስደነገጣቸው ድረስ ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ

መኰንኑም በአፈረ ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው እናቱንም ከርሱ ጋር እንደ እርሱ አሠቃያት እግዚአብሔርም ያለምንም ጉዳት ያነሣቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ

በሕፃኑ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው

ከዚህም በኋላ መኰንኑ በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ሆነ ያን ጊዜም ፍርሀትና የሃይማኖት ጉድለት በእናቱ ላይ ደረሰባት ሕፃኑም ስለ እናቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ

ያን ጊዜ ጌታችን ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አየች ከዚህም በኋላ ጸናች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው ልጅዋንም ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አንተ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው

ያቺ ከኔ የተወለድክባትም ቀን የተባረከች ናት አለች ወደዚያ ወደ ጋኑ ውስጥ በገቡ ጊዜም የውኃው ፍልሐት እንደ ንጋት ጊዜ ውርጭ ቀዘቀዘ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው እንዲጐትቷቸው አዘዘ ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ አዳናቸው መኰንኑም በታላቅ ሥቃይ ያሠቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው

ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው አረጋጋውም። ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቂርቆስና በኢየሉጣ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ