Get Mystery Box with random crypto!

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

የቴሌግራም ቻናል አርማ gedlekidusan — ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints
የቴሌግራም ቻናል አርማ gedlekidusan — ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints
የሰርጥ አድራሻ: @gedlekidusan
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 3.61K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Ratings & Reviews

4.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-08-30 21:52:22
363 views18:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-30 21:52:09 እንኳን ለቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕትና ለታላቁ አባ ቢጻርዮን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት <3

ቅዱሱ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ አረማዊ ሰው ሲሆን ከከሃዲው መክስምያኖስ ወታደሮችም አንዱ ነበር። "ሊቀ መሓዛት" ይሉታል፤ የጐበዛዝቱ አለቃም ነበር። ይህ ሰው ምንም ክርስቲያን አይሁን እንጂ በልቡ ቅንነት ተገኝቶበታል። እንደ አሕዛብ ልበ ድንጋይ አልነበረም።

በወጣትነቱም አንዲት ደመ ግቡ ሴት አግብቷል። ይህች ሴት 'ኤልያና' ስትባል የተባረከች ክርስቲያን ናት። እርሱ ግን አያውቅም። ከተጋቡ ከዓመታት በኋላ ጌታ እግዚአብሔር ስለ ሚስቱ ጸሎት በጐ ጐዳና ሊመራው ፈለገ።

እንድርያኖስ ሁሌም በየቀኑ ክርስቲያኖች ደማቸውን ሲያፈሱ ይመለከታል። የትእግስታቸው መጠንም ይገርመው ነበር። በተለይ አብዛኞቹ በመከራው ደስተኞች ነበሩ። ነገሩ ግራ ቢያጋባው ሃያ አራት ባልንጀሮች ሊገደሉ ወደ ታሠሩበት ቦታ ሒዶ ጠየቃቸው።

"ምን ልታገኙ ነው ግን ይህንን ሁሉ ስቃይ በአኮቴት (በምስጋና) የምትቀበሉት?" ቢላቸው "በሰማይ በክርስቶስ ዘንድ የሚጠብቀንን የክብር ሕይወት ሥጋዊ አንደበት አከናውኖ መናገር አይቻለውም። ዝም ብሎ 'ዕጹብ፣ ዕጹብ' እያሉ የሚያደንቁት ነው እንጂ።" አሉት።

እርሱም ተደላድሎ ተቀምጦ "እስኪ በደንብ አስረዱኝ?" አላቸው። ከዓለም መፈጠር እስከ ጌታችን የማዳን ሥራ አልፎም ስለ ፍርድ ቀን በጥዑም አንደበታቸው አስተማሩት። ቅዱስ እንድርያኖስ በቅጽበት ልቡ ወደ ክርስቶስ ፍቅር ሸፈተ።

በፍጥነት ተነስቶ የራሱን ስም ከሰማዕታቱ ሃያ አምስተኛ አድርጐ አጻፈ። ንጉሡ ይህንን ሲሰማ "አብደሃል?" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የለም! ዛሬ ገና ከእብደቴ ተመለስኩ።" በማለቱ ከሃያ አራቱ ቅዱሳን ጋር ታሠረ። ቅድስት ኤልያና (ሚስቱ) ነገሩን ስትሰማ ፈጽሞ ደስ አላት።

ወደ እስር ቤት ሒዳ "አይዞህ በርታ! ስለ ክርስቶስ የሞትክ ቀን ብቻ እኮራብሃለሁ።" ብላ እግራቸውን አጥባቸው ተመለሰች። በሚገደሉበት ቀንም ልሰናበታት ብሎ ቅዱስ እንድርያኖስ ቢመጣ ቅድስት ኤልያና ቤቷን ዘግታ ገሠጸችው። እርሷ ክዶ የመጣ መስሏት ነበር።

እርሱ ግን የሚስቱን የእምነት ጥንካሬ ተረዳ። ቅዱሱና ሃያ አራቱ ቅዱሳን ለቀናት ብዙ መከራን እየተቀበሉ ሰነበቱ። አካላቸውን እየቆራረጡ፣ ደማቸውን እያፈሰሱ፣ ሆዳቸውንም እየቀደዱ መከራን አጸኑባቸው። በመጨረሻው በዚህች ቀን ሲገደሉ ቅድስት ኤልያና "የእኔን ባል አስቀድሙት?" አለች። (የሌሎቹን አይቶ እንዳይደነግጥ ነው።)

እንዳለችውም የእርሱንና የባልንጀሮቹን ጭን ጭናቸውን እየሰበሩ ገድለዋቸዋል። ቅድስት ኤልያናንም መሣፍንቱ "ካላገባንሽ?" እያሉ ሲያስቸግሯት ተሰዳ ሒዳ ከሰማዕታቱ መቃብር ላይ አለቀሰች። ጌታም ጠርቷት እዚያው ዐረፈች።

<3 ታላቁ አባ ቢጻርዮን <3

ታላቁ ገዳማዊ ሰው የመጀመሪያ መነኮሳት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ሲሆን ዓለምን ንቆ ከመነነ በኋላ ከአባ እንጦንስ ዘንድ መንኩሷል። ከእርሳቸው ዘንድ በረድእነት ለብዙ ዓመታት አገልግሏል። አገልግሎቱን በፈጸመ ጊዜም አስኬማን ተቀብሎ ወደ በርሃ ወጥቷል።

ምንም የራሱን ገዳም ባይመሠርትም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምናኔ ሕይወት እንዲስፋፋ ካደረጉ አበው እርሱ ዋነኛው ነው። በተጋድሎ ዘመኑም የሚታወቅባቸው ነገሮች አሉ።
ከእነርሱም ጥቂት እንጠቅሳለን።
አባ ቢጻርዮን፦
፩.ጾሙም ሆነ ጸሎቱ በአርባ ቀናት የተወሰነ ነበር። ጾምን ከጀመረ ያለ አርባ ቀን እህል አይቀምስም። ለጸሎት ከቆመም የሚቀመጠው ከአርባ ቀናት በኋላ ነው።
፪.ሁሌም በየበርሃው እየዞረ ያለቅሳል። "ምነው?" ሲሉት "ወገኖቼ አለቁብኝ፤ ደሃም ሆንኩ።" ይላቸው ነበር። እንዲህ የሚለው አጋንንት ብዙ ነፍሳትን እየነጠቁ ሲወስዱ ስለሚመለከት ነው።
፫.በየገዳማቱ እየለመነ ለነዳያን ያከፋፍል ነበር።
፬.ሐፍረቱን ከሚሸፍን ጨርቅ በቀር ምንም ልብስ አይለብስም ነበር።
፭.ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላ ነበር።
፮.በባሕር ላይ ተራምዶ ሲሔድና እግሮቹ ሳይርሱ ሲቀሩ አበው ተመልክተዋል።
፯.መርዝነት ያለውን ውኃም ጣፋጭ አድርጐታል።

ቅዱሱ ድውያንን ፈውሶ፣ አጋንንትን ከአካባቢው አሳዶ፣ ብዙ ፍሬ አፍርቶ ገዳም ውስጥ በገባ በሃምሳ ሰባት ዓመቱ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል።

ቸር አምላክ በክብረ ቅዱሳን ይከልለን። ከበረከታቸውም ያብዛልን።

ነሐሴ ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
፪.ሃያ አራቱ ሰማዕታት (ማኅበሩ)
፫.ቅድስት ኤልያና (ሚስቱ)
፬.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ
፭.ቅዱስ ኤልያኖስና እኅቱ አውዶክስያ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
፮.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

"ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእርሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር። በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን። ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።"
(፪ቆሮ ፭፥፲፰-፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራምም እንገኛለን።
t.me/GedleKidusan
374 views18:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 20:52:13
605 views17:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 20:52:03
369 views17:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 20:51:53 እንኳን ለታላላቁ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራና ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ <3

<3 ልደት <3
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል።

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል።

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ.ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ.ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል።

<3 ዕድገት <3
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።

<3 መጠራት <3
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ።

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ።

<3 አገልግሎት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት።
፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል።
፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር።

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።

<3 ገዳማዊ ሕይወት <3
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል።

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል።

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።

<3 ስድስት ክንፍ <3
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር።

የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር።

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦
በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣
በቤተ ልሔም ልደቱን፣
በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣
በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣
በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር።

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ።
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው።

በዚያም፦
የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣
ስድስት ክንፍ አብቅለው፣
የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣
ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣
ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል።

<3 ተአምራት <3
የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው።
ሙት አንስተዋል፣
ድውያንን ፈውሰዋል፣
አጋንንትን አሳደዋል፣
እሳትን ጨብጠዋል፣
በክንፍ በረዋል፣
ደመናን ዙፋን አድርገዋል።

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና።

<3 ዕረፍት <3
ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ.ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል።
626 views17:51
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 20:17:41
"ተአምር ሠሪው ጊዮርጊስ ሆይ! የማስተዋልና የጥበብ መከታ ነህና ደመና ዝናማትን እንደሚያዘንም ፍጹም የሆነ የሕይወት መንፈስ ከፈጣሪ ዘንድ ላክልኝ።"
(መልክአ ጊዮርጊስ)
278 views17:17
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 19:56:40
270 views16:56
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 19:24:27 እንኳን ለሠላሳ ሺህ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት <3

ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ፫፻፭ (፫፻፲፪) ዓ.ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል። ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው (ያደለው) ይቀበለዋል።

ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው። ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል። በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ መናፍቃንን አሳፍረዋል። ምዕመናንንም አጽንተዋል።

በ፬፻፶፩ ዓ.ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም። ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምህርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች።

በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ) ተባሉ። ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" (የውሾች ስብሰባ)፣ "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች ጉባኤ) ተብሏል።

የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም።" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው። በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው ጥርሱንም አርግፈው ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት።
በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ፬፻፶፬ ዓ.ም ዐረፈ።

እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ (ክፉ ሴት ናት።) ድንገት ሞቱ። ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም። በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር። መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን።" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ።

የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው። ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር። ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው። መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር።

ለምሳሌ አውጣኪን (የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው።) አወገዘው። እነርሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም። ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና። የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም። ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር።

አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ። (መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ። እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም።) ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ። ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው።

የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው የሾምከውን ገደሉ። ሌላ ጳጳስም ሾሙ።" ብለው መልዕክት ላኩለት። በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ። ይህን አዋጅ ተከትሎ ሠላሳ ሺህ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ።

ገዳዮቹ ወንድ፣ ሴት፤ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ። ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል።
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ።

ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት። ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት። ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል። ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው።

አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ነሐሴ ፳፫ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ሠላሳ ሺህ የእስክንድርያ (ግብጽ) ሰማዕታት
፪.ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት
፩.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እስራኤል)
፬.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮.አባ ሳሙኤል
፯.አባ ስምዖን
፰.አባ ገብርኤል

"በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም። ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን።"
(፩ጴጥ ፫፥፲፫-፲፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
290 views16:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 22:53:56
438 views19:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ