Get Mystery Box with random crypto!

ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints

የቴሌግራም ቻናል አርማ gedlekidusan — ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints
የቴሌግራም ቻናል አርማ gedlekidusan — ገድለ ቅዱሳን Gedle Kidusan Acts of Saints
የሰርጥ አድራሻ: @gedlekidusan
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 3.61K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ገጽ ስለ ቅዱሳን ክብር ተዓምር ገድል ይናገራል::

Ratings & Reviews

4.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2022-08-27 22:53:30 እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚክያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ <3

ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ።
(ሐዋ. ፲፩፥፳፯)
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ።

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል።
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ።
(ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል።
(ዮሐ. ፬፥፴፮)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል።
(ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ።

አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦
ቅዱስ አዳም አባታችን
ሴት
ሔኖስ
ቃይናን
መላልኤል
ያሬድ
ኄኖክ
ማቱሳላ
ላሜሕ
ኖኅ
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ሙሴና
ሳሙኤል ናቸው።

አራቱ ዐበይት ነቢያት፦
ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
ቅዱስ ኤርምያስ
ቅዱስ ሕዝቅኤልና
ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።

አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦
ቅዱስ ሆሴዕ
አሞጽ
ሚክያስ
ዮናስ
ናሆም
አብድዩ
ሶፎንያስ
ሐጌ
ኢዩኤል
ዕንባቆም
ዘካርያስና
ሚልክያስ ናቸው።

ካልአን ነቢያት ደግሞ፦
እነ ኢያሱ
ሶምሶን
ዮፍታሔ
ጌዴዎን
ዳዊት
ሰሎሞን
ኤልያስና
ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ።
የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።

በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣
ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣
ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ።
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ።

ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፰፻ ዓ.ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው።
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል።

ሚክያስ አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል። ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው። አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው። የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው።

ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር። በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም። ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር። በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ። በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል። ሕዝቡን፣ መሣፍንቱንና ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል።

አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ። ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት።
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል።"

"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም። ወገኖቼን እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና።" አለ።

ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል። በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል።

ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ በመልካም ሽምግልና በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል። ወገኖቹ ቀብረውታል። ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል።

ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን። ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን።

ነሐሴ ፳፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
፬.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፭.አባ ጳውሊ የዋህ

"ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን?.....
ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል። እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ ምሕረትንም ትወድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?"
(ሚክ ፮፥፮-፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
444 views19:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-26 18:18:04
521 views15:18
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-26 18:17:58 እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት፣ ንግሥተ ሳባና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

<3 ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት <3

ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት፣ ምግባር ከሃይማኖት፣ ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት። ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት፣ የተወደደች" ማለት ነው። አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው።

ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ ሉክያኖስ ልጅ ናት። ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም። ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው።

ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግሥት ሠራላት። ማንም እንዳይገባ በዙሪያው አሥራ ሁለት አጥር አጠረበት። ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት።

ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል። እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም። ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል። አንድ ቀን አባቷ ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት።

ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው። አባቷ ይህ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም። አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው። ግን ማንም አያውቅበትም። አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም።

መጀመሪያ በሥነ ምግባር አነጻት። ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት።" እያለ ይጸልይላት ገባ። ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራእይን አየች።

እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች። እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ።

በሦስተኛው ግን ቁራ እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ። ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራእይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምህሯን "ተርጉምልኝ" አለችው።

እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ። የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው፦ ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ ናት። የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ ማኅተመ ጥምቀት (ሜሮን) ነው። ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው።

ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል።" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት።

እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች፦ "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ።" ስትል ለመነች። በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት። የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት።

በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት። "ሦስት ቀን ስጠኝ?" አለችውና ሰጣት። ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው። ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ። በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች።

በዘመኑ ቅዱሳን ሐዋርያት (በተለይ እነ ቅዱስ ጳውሎስ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ። ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት።

በሦስተኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር መርዓተ ክርስቶስ (ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው።" አለችው። አባቷ ደነገጠ። እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ።

በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር። ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኳ ጭቃ አልነካም። አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም። ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም።" አሉ። ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች።

ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ። የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ። የጸሎት ሰውም ሆነ። የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ።

በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግሥት ቀማ። እርሷንም እጅግ አሰቃያት። እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት። እርሱም አለፈ። ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ። በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት።

ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው። በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው።" ሲል አመነ። ከሠላሳ በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ።

ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች። ጌታ አብርቶላት እርሷም አብርታ እልፍ ፍሬን አፍርታ በዚህች ቀን ዐርፋለች። የሐዋርያትንም የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች።

<3 ንግሥተ ሳባ <3

ይህቺ ኢትዮጵያዊት ከሦስት ሺህ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ምኒልክን ወልዳለች። ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች።
(ማቴ. ፲፪፥፵፪)
በስምም "ሳባ፣ አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው።

<3 ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት <3

ይህቺ ቅድስት የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱ፣ የመስቀሉ ወዳጅ፣ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት። ይህቺም ቅድስት የተወለደችው በዚሁ ዕለት ነው።

የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እኅት እናቶቻችንን ከክፋትም፣ ከጥፋትም፣ ይሠውርልን። ለሃገርም፣ ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን። በረከታቸውም ይደርብን።

ነሐሴ ፳፩ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (ስድስተኛ ቀን)
፪.ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት (ሰማዕት)
፫.ቡርክት ንግሥተ ሳባ (ልደቷ)
፬.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት (ልደቷ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪.አበው ጎርጎርዮሳት
፫.አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬.አቡነ አምደ ሥላሴ
፭.አባ አሮን ሶርያዊ
፮.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች። የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና። እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።"
(ማቴ ፲፪፥፵፪)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
531 views15:17
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 18:53:50
592 views15:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-25 18:53:40 እንኳን ለቅዱሳን ሰባቱ ደቂቅ እና ለአቡነ ሰላማ ካልዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱሳን ሰባቱ ደቂቅ <3

እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው። ሰባቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል። ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል። የተቀጠሩትም የቤተ መንግሥቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው።

በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር። እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር፣ በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ።

ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ። አዋጅም አስነገረ። አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ፣ ለጣዖትም ያልሰገደ፣ ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ፣ እጅ እግሩ ለእስር፣ ደረቱ ለጦር፣ አንገቱ ለሰይፍ፣ ቤቱም ለእሳት ይሰጣል።" የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ።

የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ። ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች። የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ ሰባቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ። ንጉሡ እነርሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ።" አላቸው። እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት።

ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል። ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው። ከቀናት በኋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ። ግን አልተሳካለትም። በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ወጣ።

ከመውጣቱ በፊት ግን ሰባቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻችኋለሁ። ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ። ካልሆነ ሞት ይጠብቃችኋል።" ብሏቸው ነበር የወጣው። ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ። ውሳኔንም አስተላለፉ።

ዓለምን ንቀው ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ። አንድ ወታደር (በጐች አሉት።) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ። ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር። ከእነርሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር።

አንድ ቀን ግን ከእነርሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ። ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው። ከዚያች ቀን በኋላ ሰባቱም አልወጡም። በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ። ከዚያች ቀን በኋላ ግን አልነቁም።

ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል።" ብሎ አዘነ። በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና። እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው።

ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው። እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም። ቀናት፣ ወራት፣ ዓመታት ተዋልደው ለሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኙ። አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ።

በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው። እድሜአቸው ግን አራት መቶ ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር። ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ። ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት። ከተማዋ ዘምናለች።

በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል። ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው። እርሱም "አዎ ናት።" ብሎት አለፈ።

ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር። በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል።" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ። (ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው። የነገሠውም በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።)

በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእርሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም ሊቀ ጳጳሱም (አባ ቴዎድሮስ ይባላል።) ተገረሙ። አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው ሲጸልዩ አገኟቸው። ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር። ሰባቱም ለሰባት ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ።

ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሣኤ ሙታን የለም።" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነርሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው። በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃይማኖት ተመልሰዋል። ሰባቱ ቅዱሳን ግን በሰባተኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል። ንጉሡ በሰባት የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል።

<3 አቡነ ሰላማ ካልዕ <3

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮጵያ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፫፻፹ ዓ.ም ነው። በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል። በዘመኑ ጳጳስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ጳጳሳት በቤተ መንግሥት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም።

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ። ቀጥለው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ። አሥራው መጻሕፍትን (ሰማንያ አሐዱን) ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል።

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል። ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም፦
ስንክሳር፣
ግብረ ሕማማት፣
ላሃ ማርያም፣
ፊልክስዩስ (መጽሐፈ መነኮሳት)፣
መጽሐፈ ግንዘት፣
ድርሳን ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ..... ይጠቀሳሉ።

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር። በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ ያጠምቁም ነበር። በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር። መሣፍንቱን፣ ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል።

ጻድቁ አቡነ ፊልጶስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል። በቀደመ ስማቸው አባ ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ (ሁለተኛው) ሰላማ በ፲፫፻፹ ዓ.ም ከአርባ ዓመታት ትጋት በኋላ ዐርፈዋል።
ሲጠሩም፦
መተርጉም (መጻሕፍትን የተረጐሙ)፣
ብርሃነ አዜብ (የኢትዮጵያ ብርሃን)፣
መጋቤ ሃይማኖት ተብለው ነው።

አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን እንዳጸናቸው ያጽናን። ከበረከታቸውም ያድለን።

ነሐሴ ፳ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (አምስተኛ ቀን)
፪.ቅዱሳን ሰባቱ ደቂቅ
፫.አቡነ ሰላማ ካልዕ (መተርጉም)
፬.ቅድስት ሔዛዊ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
፬.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
፮.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት

"በተቀደሰ አሳሳም እርስ በእርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"
(፪ቆሮ ፲፫፥፲፪-፲፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በቴሌግራም t.me/GedleKidusan ላይ ያገኙናል።
601 views15:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 16:33:21
864 views13:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 16:33:15 እንኳን ለቅዱሳን አበው አባ መቃርስ፣ ቅዱስ አብርሃምና ቅዱስ ፊንሐስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ታላቁ ቅዱስ መቃርስ <3

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት፣ የመነኮሳት ሁሉ አለቃ፣ ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ፣ በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ፣ ከሃምሳ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል። በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሣቸው አጥምቀዋል።

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና።) እመቤታችንን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አዕላፍ መላእክትን፣ በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን፣ ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን፣ ማርቆስን፣ ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል። በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልአኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል። በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል።

ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሬ በዓለ ፍልሠቱ ናት።
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦
ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በኋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ። ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ) የኖሩባት ቦታ ናት።
የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው።

በምድረ ግብጽ በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር። መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነርሱ ግን ስለ ፍቅር አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት።

ወደ ሳስዊርም ወስደው ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት። በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ። በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ። በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት።

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ። አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት በነበረበት ዘመን ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ።

ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና። ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላችኋለን።" ብለው ሰይፍ፣ ዱላ፣ ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው።

መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ። መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራእይ ተቆጣው። በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ።

ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው። ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ። ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል። ይህ የተደረገው በዚህች ዕለት ነው።

<3 አባታችን ቅዱስ አብርሃም <3

የሃይማኖት፣ የደግነት፣ የምጽዋትና የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም ደጉ በዚህች ቀን ይታሠባል። በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር።

በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም።" በሚል አናገረው።

"እርቦኛል አብላኝ?" አለው። መልስ የለም። "እሺ አጠጣኝ?" አለው። አሁንም ያው ነው። "ባይሆን እሺ አጫውተኝ?" አለው። ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር። ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዓይን እያለው የማያይ ጆሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር።

ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እርሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል።" ብለውት ሔደዋል። ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ። "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ።" ብሎ ሰባበረው።

ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው። ይህ የተደረገው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው። የመንግሥተ ሰማያት አበጋዝ የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውኃ፣ በነፋስ፣ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል።

<3 ቅዱስ ፊንሐስ ካህን <3

ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ ከነገደ ሌዊ የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው። አባቱም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ነው። ፊንሐስ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕፃን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን አባቱ አልዓዛርና አያቱ አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል።

አንድ ቀን በጠንቅ-ዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እስራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር። ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው።

ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል። ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል። መቅሰፍቱም ተከልክሏል። በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የሦስት መቶ ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።
(ዘኁ. ፳፭፥፯ ፣ መዝ. ፻፭፥፴)

ለአበው ቅዱሳን የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን። ክብራቸውንም በእኛ ላይ ይሣልብን።

ነሐሴ ፲፱ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (አራተኛ ቀን)
፪.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ፍልሠቱ)
፫.አባታችን ቅዱስ አብርሃም (ጣዖቱን የሰበረበት)
፬.ቅዱስ ፊንሐስ ካህን (ወልደ አልዓዛር)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬.አቡነ ሥነ ኢየሱስ
፭.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፦ 'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ። እያበዛሁም አበዛሃለሁ።' ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ። እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በኋላ ተስፋውን አገኘ።"
(ዕብ ፮፥፲፫-፲፭)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
874 views13:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 16:32:18
334 views13:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 16:32:11 እንኳን ለሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ <3

ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ (የተወለደባት) ግብጽ ናት። የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በምግባሩ በትምህርቱ ለምዕመናን ጥቅም ሆኗቸዋል። ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት ሔዷል።

ቅዱስ ጴጥሮስ የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል። ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም ሦስቱ ግን ተጠቃሽ ነበሩ።
፩.ቅዱስ እለእስክንድሮስ (ደጉ)
፪.አኪላስ (ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ)
፫.አርዮስ (የቤተ ክርስቲያን ጠላት)

ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር ነበር። አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ ስለ ምንም የማይጨንቀው ሰው ነበር። ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን በጾምና በጸሎት እየተጋ መምህሩን ቅዱስ ጴጥሮስን ለመተካት (ለመምሰል) ይጥር ነበር።

ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምህሩ ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል። አርዮስ ክዶ ቅዱስ ጴጥሮስ ካወገዘው በኋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር። ነገር ግን የአርዮስን ክፋት ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩን እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው።
"እኔ ከሞትኩ በኋላ አኪላስ ይተካል። ከአርዮስ ጋር ስለሚወዳጅ በስድስት ወሩ ይቀሠፋል። አንተ ግን ከአርዮስ መርዝ ተጠበቅ።" አለው። ይህንን ካለው በኋላ ወታደሮች የቅዱስ ጴጥሮስን አንገት ቆረጡ። ይህ የተደረገውም እ.ኤ.አ በ፫፻፲፩ ዓ.ም ነው።

ወዲያውም አኪላስ ተሾመ። እንደ ተባለውም ከአርዮስ ጋር ስለተወዳጀ በስድስት ወሩ ተቀሰፈ። በዚያው ዓመትም ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ (ግብጽ) አሥራ ዘጠነኛ ፓትርያርክ (ሊቀ ጳጳሳት) ሆኖ ተሾመ።

ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ ተከታዮች ከተገመተው በላይ መብዛታቸው ነው። ቅዱሱ ሊቅ በጵጵስና መንበሩ ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲቆይ ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም።

በዚህ እየጾመ፣ እየጸለየ፣ ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው ይገዛል። በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል ያስተምራል። ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ ለመታደግ በአፍም በመጣፍም (በደብዳቤ) አስተማረ።

ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ አትናቴዎስ እያገዘው አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት። ለእያንዳንዷ የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ ባለፈ አርዮስን ከአንዴም ሁለቴ፣ ሦስቴ በጉባኤ አውግዞታል።

ነገሩ ግን በዚህ መቋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ። እ.ኤ.አ በ፫፻፳፭ ዓ.ም (በእኛ በ፫፻፲፰ ዓ.ም) ከመላው ዓለም ለጉዳዩ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስምንት የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ። ከእነዚህ መካከል ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ።

ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ እለእስክንድሮስን መረጠ። ሊቁም አበው ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን አርዮስን ተከራክሮ ረታው።

በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም።" በማለቱ እርሱን አውግዘው፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው፣ ሃያ ቀኖናዎችን አውጥተው፣ መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው፣ አሥራው መጻሕፍትን ወስነውና ቤተ ክርስቲያንን በዓለት ላይ አጽንተው ተለያይተዋል።
የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ነው።

እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "ወልድ ዋሕድ፣ አምላክ፣ ወልደ አምላክ፣ የባሕርይ አምላክ" መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል። የእምነታችንም መሠረቱ ይሔው ነው። ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት ወምድር፣ የባሕርይ አምላክ፣ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ (ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል)" ብለው ካላመኑ እንኳን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም።

ከጉባኤ ኒቅያ በኋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል። ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን ምሰሶ ይወርድለት ነበር።

ስለ ውለታውም ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ አምስቱ ከዋክብት ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች። ቅዱሱ ሊቅ በ፫፻፳፰ ዓ.ም (በእኛ በ፫፻፳ ዓ.ም) በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል።

ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቅልን። ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን።

ነሐሴ ፲፰ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (ሦስተኛ ቀን)
፪.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫.ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን
፬.አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ (ኢትዮጵያዊ ጻድቅ)

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
፫.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፭.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

"..... ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
(ይሁዳ ፩፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
333 views13:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-24 16:31:09
297 views13:31
ክፈት / አስተያየት ይስጡ