2022-07-21 16:18:50
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
#ቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ
ቅዱስ ኤፍሬም በ306 ዓ.ም በግንቦት 1 ቀን ተወለደ፡፡ ይህም ቅዱስ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ነው፡፡ አባቱም የክርስቶስን አምላክነት የሚጠላ የጣዖት ካህን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም ቅዱስ ኤፍሬም የእግዚአብሔር ቸርነት አነሳስቶት እንዲሁም ለክርስትና እምነት ከልጅነቱ ጀምሮ ዝንባሌ ስለነበረው በአቅራቢያው የነበረ የንጽቢን ኤጲስ ቆጶስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ ሄዶ የክርስትና ሃይማኖት በሚገባ አስተምሮታል፤ በተወለደ በ18 ዓመቱም አጠመቀው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ከተጠመቀ በኋላ ሕይወቱ ኹሉ የምነና፣ የምንኩስና ሕይወት ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአቅራቢያው በሚገኝ ገዳም ሄዶ የገዳሙን ኃላፊ (አበምኔቱን) በማስፈቀድ አነስተኛ ጎጆ ሠርቶ በጾምና በጸሎት ተወስኖ በብሕትውና መኖር ጀመረ፡፡ ለገዳሙ በሚያስፈልገው ከባድ ተግባር ኹሉ የጉልበት ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሕይወቱ ኹሉ ገንዘብ በእጁ ነክቶ አያውቅም፤ የግል ሀብትና ንብረትም ኖሮት አያውቅም፡፡ ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐስራ ስምንት አባቶች ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ያዕቆብ አንዱ ስለነበረ ለኒቅያ ጉባኤ ሲሄድ ቅዱስ ኤፍሬምን አስከትሎት ሄዶ ነበር፡፡ በዚያም አርዮስን አውግዘው ሃይማኖትን መልሰው ከተመለሱ በኋላ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምደር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ፤ ከዚህ ራዕይም የተነሳ አደነቀ፡፡ ይገለጥለት ዘንድ ወደጌታ ቢጸልይ ‹‹ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ባስልዮስ ነው›› የሚል ቃል ከሰማይ ወደ እርሱ መጣ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወድዶ ወደ ቂሣርያ ሀገር ተጓዘ፤ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ በማዕዘኑ በኩል ቆመ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስንም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የኾነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው፡፡ ሦስት ምልክቶችንም እስኪያይ ድረስ ተጠራጠረ፤ ምልክቶቹም እነዚህ ናቸው፦
፨ ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች፤
፨ ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሕሲያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር፤
፨ ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምእመናን ላይ ያድር ነበር።
በኋላም ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡና በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመር። የየራሳቸውንም ቋንቋ ይገለጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልዩ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመነው። በጸለዩ ጊዜ ተገልፆላቸው ያላስተርጓሚ ተነጋገሩ።
ከዚያም ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው፤ ከጥቂት ወራትም በኋላ ቅስና ሾመው፡፡ ከእርሱም ብዙ ቱርፋቶች ተገለጡለትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ኹሉን ተጋደለ። ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱሳት መጻሕፍት ባለው ዕውቀት እንዲሁም ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ባላው ቅንዓትና ለምንኩስና በነበረው ታማኝነት እጅግ የታወቀ ነበር። በ363 ዓ.ም የንጽቢን ግዛት በጦርነት ወደ ፋርስ ግዛት በተዛወረች ጊዜ ቅዱስ ኤፍሬም የሶርያ ግዛትና የክርስቲያን ሀገር ወደ ኾነችው ወደ ኤዴሳ ሄዶ መኖር ጀመረ። ኤደሳም በዚያን ጊዜ ከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል ነበረች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም መንኖ በኤዴሳ ከተማ አጠገብ በምትገኝ አንድ ታላቅ ዋሻ ውስጥ በብሕትውና ይኖር ጀመር። በዚያም ተቀምጦ በምንኩስና ሕይወት ላይ ከሚያደርገው ተጋድሎ ሌላ ብዙ መጻሕፍትን በመጻፍና ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የውዳሴ መዝሙር በመጻፍ ወርቃማ ጊዜ ያሳልፍ ነበር።
ቅዱስ ኤፍሬም እጅግ ብዙ መጻሕፍትን ደርሷል፡፡ ከድረሰቶቹ አብዛኛዎቹ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የአንደምታ ትርጓሜና በመጻሕፍቱ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችና ድርሰቶች ናቸው። እንዲሁም ለክርስትና ሃይማኖት በመከራከር በአይሁድና በአረማውያን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ድርሰቶችን ጽፏል። ስለ መናፍቃንም ብዙ መጻሕፍትን ጽፏል። ቅዱስ ኤፍሬም ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ስለነበረው ስለ እርሷ ብዙ ውዳሴዎችንና ድርሰቶችን ደርሷል። በኢትዮጵያ እጅግ የሚታወቀው በሳምንቱ ቀናት በእያንዳንዱ ቀን ለእመቤታችን የሚቀርብ ውዳሴና ምስጋና የጻፈው ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ከደረሳቸው ድርሰቶች ለኢትዮጵያ ወደ ግዕዝ የተተረጎመው እነዚህ የሰባቱ ቀናት ውዳሴና ምስጋና ሲሆን በሃይማኖተ አበው ውስጥ በኤፍሬም ሶርያዊ ስም አንድ ድረሳን ይገኛል። ቅዱስ ኤፍሬም አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ እስኪል ድረስ ድርሳናትን ደርሷል።
የቅዱስ ኤፍሬም የዕረፍቱ መታሰቢያ ሐምሌ 15 ቀን ነው። በረከቱ በሁላችን ላይ ይሁን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ መድበለ ታሪክ
@EwketBirhan
339 views𓅪ሀገሬ ሰማይ ዘሬም ፍቅር𓅪, 13:18