2022-08-29 09:16:02
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
#ቅዱስ_ቶማስ_ዘመርዓስ
ቅዱስ ቶማስ አስቀድሞ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት የሚተጋ እንዲሁም ለድኆችና ለምስኪኖች የሚራራ ተጋዳይ ቅዱስ አባት ነበር፡፡ በኋላም መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስ ቆጶስ ይሆን ዘንድ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሰቃያቸው ዘንድ ከመኳንንቶቹ አንዱ ቶማስ በተሾመባት አገር (መርዓስ) ደረሰና ቶማስን ወደ እርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሮቹን ልኮ እየደበደቡ በምድር ላይ እየጎተቱ አመጡለት፡፡ መኰንኑም ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት/ለጣዖት ስገድ ቢለው ‹‹ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ለረከሱ ጣዖታት አልሰግድም፤ ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና›› ብሎ መለሰለት፡፡
በዚህም መኰንኑ ተቆጥቶ እጅግ የበዛ ስቃይን እያሰቃየው ለብዙ ጊዜ ኖረ፤ ምክንያቱም የከሃድያኑ ልባቸው እንደ ደንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አይፈልጉምና ነው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስለጸና ማሰቃየቱን ከሃድያኑ በተሸነፉ ጊዜ ስለ ስህተታቸው ስለሚዘልፋቸው በጨለማ ቦታ ጣሉት፤ በዚያም 22 ዓመት ኖረ፡፡ ከሃድያኑ በየዓመቱ ወደ እርሱ እየገቡ ከአካል ክፍሎቹ ውስጥ አንዱን (አፍንጫውን፣ ከንፈሮቹን፣ እጆቹንና እግሮቹን) ይቆርጡ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎችም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስላየች ቦታውን ታውቅ ነበርና በሌሊት ወደ እርሱ ተሠውራ በመሄድ ትመግበዋለች፡፡
ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠበት ድረስ እንዲህ ሲሰቃይ ኖረ፡፡ ይህም ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በወህኒ ቤት ያሉትን እስረኞች ይፈቷቸው ዘንድ በአዘዘ ጊዜ ያቺ ሲጥሉት የተመለከተችው ሴት ሄዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ለካህናቱ ነገረቻቸው፤ እነርሱም አንስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት፡፡ በቤተ መቅደስም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡትና ምእመናን ወደ እርሱ እየመጡ ከእርሱ ተባርከው የተቆረጡትንም ሕዋሳቱን ተሳልመው ይመለሱ ነበር፡፡ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ 318ቱን ሊቃውንት በኒቅያ በሰበሰበ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ አንዱ ነበር፡፡ በኒቅያ ጉባኤ አሪዎስን አውግዘው ከለዩት በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ፣ ሕግና ሥርዓትን፣ ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ በመሄድ ካህናቱንና ምእመናኑን ሁሉ ሰብስቦ በኒቅያ የተደነገገውን ውሳኔ አንብቦላቸው እንዲያስተውሉት፣ እንዲጠብቁትና በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው፡፡ ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን በክብር ዐረፈ፡፡ በረከቱ ደርብን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ ስንክሳር ዘነሐሴ 24 ፣ መዝገበ ታሪክ
@EwketBirhan
493 views𓅪ሀገሬ ሰማይ ዘሬም ፍቅር𓅪, edited 06:16