2022-09-18 09:41:29
#EthiopiaCheck Fact Check
በ4ኛ ክፍል የሂሳብ መፅሃፍ ላይ አለ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ በትክክልም ቀደም ብሎ በትምህርት ቢሮ በኩል ለትምህርት ቤቶች የተሰራጨው ሶፍት ኮፒ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በ4ኛ ክፍል የሂሳብ መፅሃፍ ላይ "የግዕዝ ቁጥሮች ምልክቶች በቀጥታ ከግሪክ ፊደል ቁጥሮች የተወሰዱ ናቸው" የሚል መረጃ እንዳለ የሚገልፁ መረጃዎች በስፋት ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲሰራጩ ነበር። ይህን መረጃም በርካታ ተከታይ ያላቸውን ገፆች ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች ሲያጋሩት ነበር።
ይህን ተከትሎ ዛሬ ማምሻውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "በአንዳንድ አካላት በ4ኛ ክፍል የሂሳብ መፅሐፍ ላይ አለ ተብሎ እየተሰራጨ ያለው ፅሁፍ በመሐሃፉ ላይ የማይገኝና የተሳሳተ ነዉ" የሚል መረጃ በፌስቡክ ገፁ አጋርቷል።
ትምህርት ቢሮው አክሎም "ዛሬ ይፋ በተደረገውና በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት የ4ኛ ክፍል የሂሳብ መጻሕፍት ገፅ 18 ላይ የግእዝ ቁጥርን አስመልክቶ ወጥቷል ተብሎ የተገለፀው ሃሳብ በመፅሐፍ ውስጥ የማይገኝ ሆነ ተብሎ የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ውዥንብር ሊፈጥሩ በሚፈልጉ አካላት የተፈበረከ ነዉ" ያለ ሲሆን ይህም በመንግስት ሚድያዎች እና በበርካታ ሚድያዎች ተዘግቧል።
በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ማጣራት አርጓል።
ኢትዮጵያ ቼክ በመጀመርያ ያናገራቸው በኮልፌ ቀራንዮ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህር "የግዕዝ ቁጥሮች ምልክቶች በቀጥታ ከግሪክ ፊደል ቁጥሮች የተወሰዱ ናቸው የሚለው መረጃ የአመቱ መጀመርያ ላይ ከትምህርት ቢሮ በደረሰን የሶፍት ኮፒ PDF ላይ ይገኛል። የመፅሀፍ ህትመት በወቅቱ ስላልተጠናቀቀ እሱን ተጠቀሙ ተብሎ ነበር የተሰጠን" ብለዋል። መምህሩ ለማስረጃ እንዲሆን ይህንን ፋይል ለኢትዮጵያ ቼክ አሳይተዋል፣ እኛም መረጃው እንዳለ አረጋግጠናል።
ኢትዮጵያ ቼክ በመቀጠል ያናገራቸው ወላጅም ይህ ከላይ ስለ ግዕዝ የተጠቀሰው መረጃ በ PDF እንደደረሳቸው አረጋግጠዋል። "ስለዚህ ዛሬ ምሽት ለትምህርት ቢሮው እንደተባለው የሀሰት ነው ሳይሆን ስህተቱን አስተካክለናል መሆን ነበረበት" ብለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እርሳቸውም ይህንን ልጃቸው ሲማርበት የነበረውን እና ከትምህርት ቤቱ የቴሌግራም ግሩፕ ላይ ያገኙትን የ PDF ፋይል ለኢትዮጵያ ቼክ አሳይተዋል።
ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማምሻውን "የግዕዝ ቁጥሮች ምልክቶች በቀጥታ ከግሪክ ፊደል ቁጥሮች የተወሰዱ ናቸው በሚል የተሰራጨው መረጃ የሀሰት ነው" ብሎ ያወጣው መግለጫ በራሱ የተሳሳተ ነው፣ ምክንያቱም አዲስ የታተመው እና ዛሬ ርክክብ የተደረገበት መፅሀፍ ላይ ማስተካከያ ቢደረግም ቀድሞ ለትምህርት ቤቶች የተሰራጨው ሶፍት ኮፒ ላይ መረጃው ሰፍሮ ይገኛል።
በዚህ ዙርያ ማብራርያ ለመጠየቅ ኢትዮጵያ ቼክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮን የኮሚኒኬሽን ክፍል ለማናገር ቢሞክርም አልተሳካም።
via:- Ethiopia Check
384 views06:41