2022-08-23 07:00:54
አስተውይ
እርሱ አይለወጥም
እንዳስቀመጥነው እናገኘዋለን፣ እንደጠብቅነውም ይሆናል ያልነው ነገራችን ሲለዋወጥብን፣ ተስፋ ያደረግናቸው ሰዎች ፊታቸው ሲጠቁርብን፣ የምናደርገው ነገር ጠፍቶን ግራ ሲገባን፣ ከስፍራው ወደማይታጣው እግዚአብሔር እንመልከት። “ በእርሱ ዘንድ መለዋወጥ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም። ” ያእ 1:16
በማይዋሸው ቃሉ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ካለን በኋላ እኛም ያልጠፋነው ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይነግረናል።
ሁኔታዎች ሲለዋወጡ በማይለዋወጠው አምላክ ላይ ብንደገፍ አንጠፋም።
ዮሴፍ ካየው ህልም በተቃራኒ ነገሮች በህይወቱ ሲቀያየሩ፣ ባልጠበቀው ጊዜና ሁኔታ ራሱን ከአባቱ ቤት ወደ ባርነት ቤት፣ ከዚያም ወደ እስር ቤት ሲገባ ቢያገኘውም፣ ከሁኔታዎች ጋር የማይለዋወጠው እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለነበረ አልጠፋም። ይልቁንም ቁልቁል የሚመስለውን ጉዞ እግዚአብሔር ወደ ህልሙ መፈጸሚያ የሚወጣጣበት መሰላል አደረገለት። እኛም ዛሬ ነገሮቻችን እየተክፋፉ ቢሄዱ ከእኛ ጋር ባለው “እኔ አልለወጥም” ባለን ጌታ ላይ እምነታችንን እናድርግ።
የሰዎች ፊት ሲለዋወጥ በማይለዋወጠው አምላክ ላይ ብንደገፍ አንጠፋም።
ዮሴፍ የገዛ ወድሞቹ ፊት ሲለዋወጥበት፣ በፍቅር ሰላም ይሉኛል ብሎ ሲጠብቅ በቁጣና በንዴት ሲገፈታትሩት፣ አልፎም ወደ ጉድጓድ ሲጥሉት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። “እኔ አልለወጥም” ያለው እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለነበረ፣ አልጠፋም። እንዲያውም እንደዚያ ፊታቸውን ያዞሩበት ወንድሞቹ፣ ጊዜ ተለውጦ በእርሱ እጅ ወደቁ።
እኛም ተስፋ ያደረግናቸው ሰዎች ጀርባቸውን ሰጥተውን ቢሆን፣ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ወዳለን ጌታ ፊታችንን እንመልስ።
ሁኔታዎችና ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም ራሳችን የምንለዋወጥበትና በተለይም ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ለእርሱ ጀርባችንን ሰጥተን በራሳችን ከንቱ የጥፋት መንገድ እየኮበለልን ሊሆን ይችላል። እንዲህም ባለ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እግዚአብሔር ግን አይለወጥም።
ከአባቱ ቤት ድርሻውን ወስዶ የጠፋው ልጅ በሄደበት አጥፊ መንገድ ለአጉል ኪሳራና ውድቀት በተዳረገ ጊዜ፣ “ወደ አባቴ ቤት ልመለስና የእርሱ ባሪያ ልሁን” አለ። የሚገርመው ታዲያ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ፣ አባቱ በስፍራው ነበር። ፍቅሩ አልተለወጠም። ገና ከሩቅ ሲያየው ሮጦ ሄዶ አቀፈው፣ ሳመው። ወደ ቀድሞ ክብሩም መለሰው። በእርግጥም ያልጠፋው ከማይለወጠው ከአባቱ ፍቅር የተነሳ ነበር። ጌታችን ይህንን ምሳሌ የነገረን እኛም እንደዚያ ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ፊታችንን አዙረን ብንሄድ የማይለወጠውን የእርሱን ፍቅር አስበን በንስሃ እንድመለስ ነው።
ከእርሱ ርቀን ቢሆን፣ ዛሬ ወደ እርሱ እንመለስ፣ እርሱንም በስፍራው ላይ እናገኘዋለን። አልተለወጠም፣ አይለወጥምም!
አባት ሆይ፣ በእርግጥም ያልጠፋነው አንተ የማትለዋወጥ አስተማማኝ አምላክ ስለሆንክ ፣ ምህረትህም ለዘላለም ስለሆነ እንደሆነ አስተውለን አሁንም እምነታችን ባንተና ባንተ ብቻ እንዲሆን እርዳን። አሜን።
350 views04:00